የአንዳንዱ ሰው ምክንያት ደግሞ የማንነት ስነልቦና ቀውስን ለማስቀረት ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ በአማሮች ላይ የሚደርሰው የግድያ አይነት እጅግ የሚዘገንን ስለሆነ ራሱን ‘ጀግና ነኝ’ የሚል ሰው ወይም ‘የኔ ብሄር አረመኔ አይደለም’ የሚል ሰው አገዳደሉ የውርደት ስነልቦናን የሚጭንበት መስሎ ይሰማዋል። ይህ ጥቃት እኔ ላይ ደረሰብኝ ወይም የእኔ ብሄር አደረሰው ብሎ ከሚያስብ፣ ምንም እንዳልተፈጠረ መካዱ ወይም ማድበስበሻውን መቀበሉ አቋራጭ አማራጭ ይሆንለታል። ታዲያ እየቆየ ሲሄድ ይህ እሳቤ የሰው ህይወትን ዋጋ ከብሄር ማንነት በታች አሳንሶ የሚያስቀር ሊሆን ይችላል።
አንዳንዶች “አማራ እንዲህ ሆነ የማንለው ብሄርተኝነትን ላለማስፋፋት ነው” ይላሉ። ይህ ከላይ እንዳልሁት ህግንና ፖለቲካን ከማደበላለቅ የሚነሳ ስህተት ነው። እንደውም የአማራን ሰቆቃ ማደፋፈን የብሄር ፖለቲካን የበለጠ አስፈላጊና ብቸኛ አማራጭ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ለምሳሌ ሰላማዊው የኦሮሞ ህዝብ በአማራ ወገኑ ላይ የሚደርስበትን ጥቃት ተገንዝቦ ድርጊቱን ለማስቆም እንዳይነሳ ያደርገዋል። ይልቁንም፣ ድርጊቱ በጽንፈኞች ብቻ ትርጉም እንዲሰጠው ስለሚያደርግ በሁሉም ዘንድ አደገኛ አማራጮች ተገቢ እየመሰሉ መታየታቸው ይቀጥላል።
አንዳንዶች አማራ እንዲህ ሆነ የማንለው ጉዳዩ እንዲረግብ ለትዕግስት ተብሎ ነው ይላሉ። እኔም ግጭት እንዳይባባስ፣ ዕልቂት እንዳይከሰት የሚደረግን ጥንቃቄ እደግፋለሁ። ግን ሰላማዊና ጠንካራ ጥረት ከተደረገ እኮ የኦሮሞ ህዝብም ሆነ የቤንሻንጉል ወዘተ ውስጥ በድርጊቱ የሚያዝኑና ክፋቱን ለማስቆም የሚፈልጉ ብዙ ሰወች አሉ። እነዚህ ሰወች የሚያሰባስባቸው መድረክና የጋራ አጀንዳ ይፈልጋሉ። በህልውና መብት ላይ የተመሰረተ ንቅናቄ ይህን እድል ሊፈጥር ይችላል። ሰወች በማንነታቸው አይገደሉ የሚል ሃገራዊ ንቅናቄ ካልተፈጠረና የደረሰው ዘግናኝ ሰቆቃ ተቃራኒ የክፋት ትርክቶችን ማሸነፍ ካልቻለ፣ ሃገሪቱን ወደተሻለ ሁኔታ መመለስ ይከብዳል። “አንድ አማራ እስኪቀር ድረስ ኢትዮጵያ ትቀጥላለች” እያሉ አማራነትን የመስዋዕት በግ አድርጎ ማቅረብ ከዚህ በኋላ አዋጭ እሳቤ አይደለም። ኢትዮጵያ የአማራነትን መብት የምትጠብቅ ሃገር እንድትሆን መጣር እንጅ አማራን የምታስገድል ጭራቅ ሆናም ቢሆን መቀጠል የምትችል አድርጎ መሳል አይገባም። የፖለቲከኞች ክፋት ባይጨመርበት ኖሮ አማራነትን ከማንኛውም ማንነት ጋር በተቃራኒ እንዲቆም የሚያደርገው ምንም አይነት ነባራዊ ሁኔታ አይፈጠርም ነበር። የማንንት ግድያ፣ ዘረፋና ማፈናቀል ከባድ ወንጀል ስለሆነ፣ በማለባበስ፣ በስሙ ባለመጥራት፣ እንዲቆም ባለመታገልና እውነተኛ እርቅ ባለመፍጠር ችግሩ አይቆምም። አማራወቹ የሚገደሉት በተሳሳተ የታሪክ ትርክት አይደለም። ትርክቱ ተሳሳተም አልተሳሳተ አሁን የፖለቲካ ርዕዮተአለም ሆኗል። ርዕዮተአለም ደግሞ የሚታረም ስህተት ሳይሆን ብዙ ህይወት የሚበላና በቀላሉ የማይቀየር እንደሆነ ከመንጌ ዘመን ጀምሮ እናውቃለን።
መደምደሚያ
ስለሰብዐዊነት የሚናገሩ ሰወች ሰብዐዊነት በቃላት የሚደረደር ትርጉም የለውም ይላሉ። የሰው ልጆች ሰብዐዊነታቸውን የሚያውቁት ሰብዐዊነት በተጣሰ ጊዜ በሚወስዱት እርምጃ ነው። ይህም እርምጃ ሰብዐዊነታቸው የተጣሰባቸው ሰወች ማንነት የእኔም ማንነት ነው በሚል እሳቤ መመራት አለበት። እኛ ግን ሰብዐዊ መብታቸው የተጣሰባቸው ሰወች ማንነት የእኛ ማንነት እንዳይሆን የፖለቲካ ጉዳይ ብቻ አድርገን በማየት ስንሸሽ ነው የኖርነው። በማንነታቸው ስቃይና ሞት የደረሰባቸውን አማራወች ዝም ማለታችን በሰባዊነት ላይ የተፈጸመ ክህደት ነው።
በማንነት ላይ የሚደርስ ጥቃት ሃገራዊና አለማቀፋዊ የመብት ንቅናቄ የመፍጠር አቅም አለው። በብሄር ማንነት ሳቢያ የሚደርስ ጥቃት ካልታወቀና በግልጽ ካልተወገዘ ለአጥፊወቹ የፖለቲካ ትርፍ ስለሚያስገኝ የስርዐቱ ባህሪ ይሆናል፤ ወንጀል መሆኑ ተረስቶ ወደ ፖሊሲ ሊቀየር ይችላል። ጥቃቱ በደም መፋሰስ ምክንያት ከትውልድ ትውልድ ወደሚሸጋገር ጠብ ያመራል። በሁሉም የሃገሪቱ ክፍል በጥልቀት ይስፋፋል። በአማራ ማንነት ላይ የተፈጸመው ጥቃት በግልጽ ባለመታወቁ ለዚህ ውጤት አስተዋጾ አድርጓል።
10
የርዕዮተአለም ትግሉንና የመብት ትግሉን መለየት ይገባል። ብሄር እንደ ርዕዮተአለም ሲታይና ብሄር እንደ ህጋዊ መብት ሲታይ የተለያዩ ናቸው። እንደ ርዕዮተአለም የብሄርን ፖለቲካ አልከተልም ማለት ይቻላል፡፡ እንደ ህጋዊ መብት አላከብረውም ማለት ግን የመብቱን ባለቤት ያለህግ ከለላ ራቁቱን ማስቀረት ነው። በብሄር ማንነቱ የሚገደልን ሰው ሰባዊ መብት ችላ ማለት ከብሄር ፖለቲካ ነጻ የመሆን ምልክት ሳይሆን በተቃራኒው በብሄር ፖለቲካ የመዋጥ ምልክት ነው።
በማንነታቸው ለሚጠቁ መቆም ከእስከዛሬው የበለጠ አስፈላጊ የሚሆንበት ሌላም ነጥብ አለ። ዛሬ የኦርቶዶክስ ሃይማኖትና የእስልምና ሃይማኖት ነባር ፍቅር እንዲበጠስ፣ የሃገሪቱ አዲስ ትውልድ ከዱሮው ባህል እንዲቆራረጥ የሚያደርግ የባህል ጥፋት እየተፈጸመ ነው። ብዙወቹ የሃገራችን ህዝቦች የጋራ እሴቶች “የአማራ ባህል” በሚል ተፈርጀው እንደ ፖለቲካና የስልጣኔ ጠላት እየታዩ ነው። በአንዳንድ ቦታወች ጥምቀትን መሰል በዐላት ማክበር ተከልክሏል። በልዩ ልዩ ቦታ ያሉ የአማራ ተወላጆች በቋንቋቸው እንዳይማሩ፣ የፖለቲካ መብት እንዲያጡ ተደርጓል። ይህ በደል እየባሰ ሄዶ ወደግድያና ወደቤተክርስቲያን ማቃጠል ተሸጋግሯል። ህገመንግስቱ ሳይቀየር፣ በደሉ እየከፋና ወደዘር ማጥፋት እየዞረ ባለበት ሰዐት ለሚጠቃው ብሄር መብት መከበር አልቆምም ማለት ለውድመቱ መቀጠል እተባበራለሁ የማለት ያህል ነው።
በኦሮሞና በትግራይ ብሄርተኞች ‘አማራ’ የሚባሉት የአንድነት ፖለቲካ አራማጆች ለአማራ የማንነት መብት መቆም ኪሳራ ነው
ይላሉ። እነሱ ቢከስሩም የሚከስሩት የፖለቲካ ስልጣንን ነው፣ በብሄራቸው ምክንያት አማራ የሚባሉት ድሆች ግን እያጡ ያሉት
ህይወታቸውን ነው፡፡ የአማራ ማንነታቸው በህጉ መሰረት እንዲከበር ባለማድረግ፣ በአማራ ማንነት የሚደራጁትን በማጣጣልና
በማሸማቀቅ ህዝቡን ለከፋ አደጋ ከማጋለጥ ሊቆጠቡ ይገባል።
አንድነቶች ኢትዮጵያዊነትን ለከተማ ልሂቃን በሚስማማ አኳኋን ብቻ ተርጉመው የአማራን ህዝብ ጭፍን ደጋፊያቸው ለማድረግ ይሰራሉ። የኦሮሞ ፖለቲከኞችም የአንድነትና የከተማ ልሂቃንን ከድሃው የአማራ ህዝብ ባለመለየትና እንደጠላት በመፈረጅ የአንድነቱ ሃይል ደጋፊ አካል አድርገው ያዩታል። ብዙወቹ ብሄርተኞችም ሆኑ አንድነቶች ለብዙሃኑ ድሃ ህዝብ መብት በተለይም ለገጠሩ ህዝብ ህልውና የሚጨነቁ አይመስልም። ለዚህ ማሳያ ምሳሌ የሚሆነን ህወሃት መሩ ኢሃዴግ እንዲወድቅ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ የመሬት ወረራ ነበር። በሺህ የሚቆጠሩ የገጠር ይዞታ ባለቤቶች መሬታቸውን በልማት ስም አጥተዋል፤ አሁንም እያጡ ነው። እንደዜጋም ሆነ እንደብሄር የእነዚህ ሰወች ከመሬት መነቀል እንዲቆምና መሬታቸው እንዲመለስላቸው በቆራጥነት የተከራከረ ፓርቲ የለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደስልጣን እንደመጡ ጋዜጠኞችን በተደጋጋሚ ሲያነጋግሩ የገበሬውን የማዳበሪያ፣ የመሬት እጦትና የዋስትና ችግር ጉዳዮች አንስቶ የጠየቀ ጋዜጠኛ እንኳን የለም። ይህ የሚያሳየን የልሂቃን ፖለቲካ ከድሃው ህዝብ ህይወት የተነቀለ መሆኑን ነው። ለህዝብ ህይወት እቆማለሁ የሚል ፖለቲካ በቅድሚያ ከብዙሃኑ ህይወት ልምድና ፍላጎት ውስጥ ራሱን መትከል አለበት።
የልሂቃኑ ፖለቲካ ራስ ወዳድነት መገለጫ የሆነ በቅርቡ አንዳንድ የአንድነት ፖለቲካ አራማጅ ነን የሚሉ ሰወች የሚያራግቡት መፈክር አለ። ይህም "ብቻየን እስክቀር ድረስ ኢትዮጵያ ትቀጥላለች" የሚል ነው። "ብቻየን እስክቀር ድረስ ኢትዮጵያ ትቀጥላለች" የሚሉይ ልሂቃን የግላቸውን ህይወት እንደ ኢትዮጵያ እያዩ፣ የሚፈራርሰውን የህዝብ ህይወት ግን እንደመስዋዕትነት የሚቆጥሩ፣ በሃገር ወዳድነት ስም ራሳቸውን ብቻ የሚወዱ ሰወች መሆናቸውን የተረዱት አይመስልም። ይህ አባባል “ኢትዮጵያ ወንጀለኞች የሚፈነጩባት፣ ህጻናትና ሴቶች በዘግናኝ ሁኔታ የሚታረዱባትና ሚሊዮኖች ተፈናቅለው ሜዳ ላይ የተጣሉባት የገሃነም ምድር ብትሆንም እኔ እስካለሁ ድረስ በህይወት አለች” የሚሉ ሰወች አባባል ነው። እነዚህ ሰወች ለለውጥ መስዋእትነት ከሚከፍሉ ይልቅ ህዝብ ቢያልቅ የሚመርጡ ይመስላሉ። የህዝብን የህይወት ህልውና ጥያቄ ለማዳፈን አጀንዳውን ወደ ሃገር ህልውና ጥያቄ ይቀይሩታል። ከኢትዮጵያ ታላቅ ባህሏ መርከስ፣ ከህዝቦቿ መረበሽ፣ በደም ከጨቀየ ምድሯና፣ በእንባ ከሚታጠብ አካሏ ሁሉ በላይ ጎልቶ የሚታያቸው የራሳቸው ሰላምና የብልጽግና ህልም ነው። "ብቻየን እስክቀር ድረስ ኢትዮጵያ ትቀጥላለች" ማለት ኢትዮጵያ ብትሞትም እኔ ብቻየን በአስከሬን ምድር ላይ እኖራልሁ እንደማለት ነው። አባቶቻችንና እናቶቻችን ጥንት ይሉ የነበረው
ግን እንዲህ ነበር፦ “እኔ እስካለሁ ድረስ አንድም ኢትዮጵያዊ አይሞትም፤ ምክንያቱም እኔ በህይወት ቁሜ ኢትዮጵያውያን እያለቁ በማየት ብቻየን መኖር አልሻምና”።
እንደአባቶቻችንና እናቶቻችን ለማለትና ለመሆን ያብቃን!!
አስተያየቶች