ወደ ዋና ይዘት ዘለው ይሂዱ

በአማራ ህዝብ ላይ የሚነሱ የተፋለሱ የጭቆና ትርክቶችን ስለመሞገት1 (unknown author) ክፍል 1

 በአማራ ህዝብ ላይ የሚነሱ የተፋለሱ የጭቆና ትርክቶችን ስለመሞገት1

  መግቢያ

 

 በዚህች ጽሁፍ ላይ የማተኩረው በአማራ ማንነታቸው ምክንያት ሰብዐዊ መብታቸው የሚጣስ ሰወች ላይ ያሉ እሳቤወችን ለመሞገት ነው። በግሌ የብሄርተኝነትንም ይሁን የአሃዳዊ አንድነትን ፖለቲካ የምቃወምባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉኝ። የሃገራችንን የፓለቲካ፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ ስሪት የማየው በገጠርና በከተማ የህይወት ተቃርኖ ላይ የተመሰረተ ሃገርበቀል የልሂቃን ቅኝ አገዛዝ እንደሆነ አድርጌ ነው። ይህንን ሃሳቤን በተመለከተ ወደፊትም የምለው ይኖረኛል። አሁን የማተኩረው ግን በዚህ ላይ አይደለም። አሁን የማተኩረው በማንንት ላይ የሚደርሰው ጥቃት የፖለቲካ ጉዳይ ብቻ ተደርጎ በመታየቱ በጥቃቱ ሰለባወች ላይ ብቻ ሳይሆን በመላ ሃገሪቱ ላይ ብሄርተኝነትን ሽፋን ያደረገ ወንጀልና አፓርታይድን የሚመስል የአድልወ ስርአት እየፈጠረ መሆኑን ለማሳየት ነው።

 

በዚህ ጽሁፍ ላይ በምሳሌነት የማነሳውን በአማራ ማንነት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በሌሎች ማንነቶች ላይ ከሚደርሰው ጥቃት ለየት የሚያደርገው ጉዳይ አለ። አማራ የህዝብ መጠሪያ ብቻ አይደለም። ወደኋላ አካባቢ እንደማሳየው፣ ላለፉት 30 አመታት አማራነት የተወሳሰበ ትርጉም ያለው ማንነት እንዲሆን ተደርጓል። ጉራጌም ይሁን ኦሮሞ፣ ትግሬም ይሁን አማራ፣ ገበሬም ይሁን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ቄስም ይሁን ሼክ፣ ኦህዴድም ይሁን ብዐዴን፣ ኢዜማም ይሁን ባልደራስ፣ የኦሮሞን ወይም የትግራይን የብሄር ትርክት ከተቃወመ፣ የኢትዮጵያዊነት ወይም የአንድነት ፖለቲካ አራማጅ ከሆነ ወይም የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ከሆነ ‘ዐማራ” የሚለው ስያሜ እንደየሁኔታው ሊጫንበት ይችላል። ለምሳሌ ፕሮፌሰር አሰፋ ጃለታ በህዳር ወር በጻፉት ጽሁፍ ላይ በአማራ ልሂቃን ተጽዕኖ ይመራሉ ብለው የዘረዘሯቸው የፖለቲካ ሃይሎች ኦህዴድን፣ ኢዜማን፣ ባልደራስን፣ አብንንና የአማራ መንግስትን ያጠቃልላሉ። ይህ የሚያሳየን ከፖለቲካ ውጭ የሆነው ድሃ የአማራ ተወላጆች ከነዚህ የተለያየ የፖለቲካ አቋምና ፍላጎት ካላቸው ሃይሎች ጋር ተደምረው በጨፍላቂነት፣ በነፍጠኛነት፣ በአሃዳዊነትና በዱሮ ስርዐት ናፋቂነት እየተፈረጁ እንደፖለቲካ ጠላት በመቆጠር ላይ መሆናቸውን ነው።

 

ይሄው ምሁር ጠቅላይ ሚንስትሩን ሳይቀር ‘አማራ ሆነዋል ያሉበትን ምክንያት ሲያስረዱ እንዲህ ይላሉ፡ “Abiy’s father is Oromo. But he was raised by his Amhara mother, a fact that he has used extensively. Considering his cruelty against the Oromo who embraced him at the beginning, most Oromos now think that his close affinity with his mother shaped his values, philosophy, ideology, and culture.2 ምሁሩ የሚሉት ‘ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአባታቸው ኦሮሞ ናቸው። ታዲያ በኦሮሞ ላይ ጨካኝ የሆኑት ለምንድን ነው ለሚለው ጥያቄ ብዙ ኦሮሞወች የሚሰጡት መልስ የአብይ እሴቶች፣ ፍልስፍናወች፣ ርዕዮተለአለምና ባህል አማራ በሆነችው እናታቸው በኩል ያገኙት ስለሆነ ነው የሚል ነው። ይህ የሚያሳየን አንድ በኦሮሞ ጥናት ትልቅ ስም ያላቸው ምሑር “most Oromos” ብለው ስለብዙ ኦሮሞወች አስተሳሰብ የሰጡን ሰእል ምን እንደሚመስል ነው፡፡ ይህም፣ ወልዳ የምታሳድግ እናት ሳትቀር አማራ ከሆነች ልጇን በኦሮሞ ላይ ጨካኝ የሚያደርግ እሴት ልታወርሰው ትችላለች ብለው እንደሚያስቡ ነው። በበኩሌ ይህ የልሂቃን እንጅ የተራው ኦሮሞ ህዝብ እምነት ነው ብየ አልገምትም። ሆኖም ይህ አይነት እሳቤ ጋር በተያያዘ የአማራ ማንነት ባላቸው ዜጎች ምን ተደረገ የሚለውን እንይ። ኢሃዴግ በ1983 ዓ.ም. ስልጣን ከያዘ ጀምሮ እስከአሁን ድረስ በአንድ ቦታ ብቻ ሳይሆን በልዩ ልዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የአማራ ማንነት ያላቸው በርካታ ሰወች የአሰቃቂ ግድያ ሰላባ ሆነዋል። ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ሰባዊ ክብራቸው ተደፍሯል፤ ስነልቦናቸው፣ ቤተሰባቸው፣ ስራቸው፣ ተስፋቸው ተሰባብሯል።

 

1  ይህ ጽሁፍ በፍትህ መጽሄት 3አመት ቁጥር 131፣ 2013 በአጭሩ ታትሟል

 

2   https://theconversation.com/what-lies-behind-the-war-in-tigray-150147

 

1


ይህ ጥቃት ፖለቲካዊ ምክንያት ቢኖረውም እንደከባድ ወንጀል ተውስዶ አጥፊወች አልተቀጡም፣ ተጠቂወች ፍትህ አላገኙም። ሌላው ቀርቶ የመንግስት ዋና አጀንዳ አልሆነም። ምድሪቱ በአማራ ላይ ወንጀል ፈጽሞ በነጻነት መኖር የሚቻልባት ሃገር ሆናለች። ይህም በፖለቲካ ምክንያት የሚፈጸም ወንጀል ከህግ ቁጥጥር ውጭ ነው የሚል አደገኛ አንድምታ ፈጥሯል። ይህ በአማራ ማንነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እንደምሳሌ ባነሳሁት የአማራ ማንነት ላይ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ሰው ላይ ሊፈጸም የሚችልበትን ቅድመሁኔታ የሚያመቻች ነው። ይህም _ ፖለቲካ _ ራሱ ማንነትን ፈጥሮ፣ እራሱ ወንጅሎ፣ እራሱ ፍርድ የሚሰጥበት አደገኛ ስርአት የመላ ሃገሪቱ የፖለቲካ ባህል ሆኖ ማደጉን ያሳየናል። እንዲህ አይነት ስርአት ብዙ ቦታ ላይ ተከስቷል። በአይሁዶች፣ በጥቁሮች፣ በፍልስጥኤማውያን፣ በደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች፣ በኩርዶች፣ በዳርፉር ሱዳኖች ወዘተ፣ አስከፊ የንጹሃን መብት የተጣሰባቸው ቦታወች ሁሉ ዋና የሚያመሳስላቸው ጉዳይ በማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥላቻና ውንጀላ ሰለባ መሆናቸው ነው። ከሰወች ማንነት ላይ ያልመረጡትንና ያልተስማሙበትን ትርጉም ጭኖ፣ ከሌሎች የሚለያዩበትን የፖለቲካ አጥር ሰርቶ፣ ንጹሃንን የሚያስፈጅና የሚጨቁን ፖለቲካ ከአፓርታይድ አይነት አድሏዊነት እስከ ርዋንዳ አይነት አጠቃላይ ዘር የማጥፋት ወንጀል ድረስ የሚደርስ ክፋት ለመፈጸም አመቺ ነው። ይህን ስራት ልዩ የሚያደርገው በማንነት ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት የፖለቲካዊ ህልውናው ማስቀጠያ እስትንፋስ ሊያደርገው የሚችል መሆኑ ነው። የንጹሃንን ደም ማፍሰስ የፖለቲካ እምነትን ጽናት ማሳያና የራስን ፖለቲካዊ ንጽህና ማስመስከሪያ እስከማድረግ ይደርሳል። በዚህ ጊዜ በማንነት የሚጠቁ ሰወችን በሃሳብ መርዳት ወይም መወዳጀት ሳይቀር የወንጀለኛነት ስሜትን መፍጠር ስለሚጀምር ከፖለቲካ ውጭ ያሉ ሰወች ሳይቀሩ ከተጠቂወቹ ማንነት ጋር የሚያስተሳስራቸውን ነገር ሁሉ መደበቅ፣ መበጠስ ወይም መሸሽ ይጀምራሉ። በሂደትም ተጠቂወቹ ለመጠቃታቸው ምክንያቱ የራሳቸው ጥፋት ነው ብሎ የሚያምን ገዢ የፖለቲካ እሳቤ ያድጋል። ይህን እሳቤ የስልጣንና የጥቅም አከፋፋይ ከሆነው ሃይል ጋር ከተቆራኘ በኋላ በውይይትና በምክክር መቀልበስ የማይቻል ይሆናል።

 

የማንነት ጥቃትን እንደከባድ ወንጀል ለማስተናገድ መደረግ ያለባቸው በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም በዚህ ጽሁፍ ላይ የማተኩረው መደረግ የሌለባቸው ጥቂት ጉዳዮች ላይ ብቻ ይሆናል። ከእነዚህም ውስጥ “አማሮች ላይ የመብት ጥሰት የሚደርሰው በተሳሳተ የታሪክ ትርክት ነው” የሚሉትንና “ግድያው በዜግነት እንጅ በብሄር ማንነት ሊጠራ አይገባውም” የሚሉት ይገኙበታል። ዋናው ክርክሬ እነዚህ እሳቤወች የሰብዐዊ መብትን ጥያቄ ከርዕዮተአለም ጥያቄ ጋር በማደበላለቅ፣ ዘር ተኮር ጥቃትን መደበኛ ወንጀል አስመስሎ በማቅረብ፣ የመንግስትን አለማቀፋዊ ሃላፊነት በማሳነስ፣ ወንጀል የፖለቲካ አላማ ማስፈጸሚያ መሳሪያ ሆኖ እንዲቀጥል ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ። በተጨማሪም አሁን ስራ ላይ ባለው የፖለቲካ አደረጃጀትና መዋቀር ውስጥ ዜግነት ብቻውን ስለማይከበር የአማራ ህዝብ ከህግ ከለላ ውጭ ራቁቱን እንዲቀር ያደርጉታል። በመደምደሚያየም የሃገራችንን እጣ ፈንታ ወደተሻለ አማራጭ ለማምጣት፣ በርዕዮተአለም ሳቢያ በአማራ ላይ የሚደርሰውን የሰብዐዊ መብቶች ጥሰት በስሙ መጥራትና እንደ ከባድ ወንጀል ማውገዝ እጅግ ትንሹ ግን የመጀመሪያው እርምጃ ነው እላለሁ። ብዙ ህዝብ ተፈናቅሎ፣ ተርቦና እየተገደለ ባለበት ባሁኑ ወቅት፣ ተፈጥሯዊ ሰብዐዊ መብትን ከፖለቲካ ርዕዮተአለም የሚለይ የመብት ጥያቄ ቅድሚያ ካልተሰጠውና በመብት ረጋጮች ላይ ህጋዊ ተጠያቂነት ካልተረጋገጠ፣ አግላይና አክራሪ የሆነው የብሄርተኝነት ትርክት ወንጀል፣ የስራቱ የትግል መገለጫ ይሆንና በፖሊሲ ጭምር መገለጹ እንደማይቀር የበርካታ ሃገሮች ልምድ ያሳየናል።

 

 

 

ታሪክ ወይስ ርዕዮተአለም፡- አማሮች የሚገደሉት በተሳሳተ የታሪክ ትርክት ነውን?

 

 

አንዳንድ ሰወች በአማራ ማንንት ላይ የሚደርሰው በደል “‘በተሳሳተ የታሪክ ትርክት” የተፈጠረ ነው ብለው ሲናገሩ ይደመጣሉ።

 

ከዚህ በመነሳትም ታሪክን ለማረም ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ይህ ጥረት መጥፎ ባይሆንም ‘የታሪክ ስህተት’ የሚለው አቀራረብ

 

ችግሩን በቀላሉ ሊታረም የሚችል እንደሆነ አድርጎ ስለሚያቀርብ ገላጭ ምክንያት አይደለም። ምክንያቱም የታሪክ ስህተት ቢሆን

 

ኖሮ የሚፈታበት ቦታ ዩንቨርስቲ ውስጥ ወይም የታሪክ ጥናት ክርክር መድረክ ላይ ይሆን ነበር። ችግሩ የፖለቲካ እምነት

 

(ርዕዮተአለም) ጉዳይ እንጅ የታሪክ አረዳድ ስህተት አይደለም። በታሪክ አረዳድና በርዕዮተአለም መካከል ያለውን ትልቅ ልዩነት

 

ለማስገንዘብ ስለርዕዮተአለም ትንሺ ልበል።

 

 

2


 

ታሪክ ውስጥ ጥፋትም በጎነትም ሞልቷል፤ ነገስታቱ መላእክትም ሰይጣናትም አልነበሩም፣ እንደእኛ ሰወች ነበሩ። ሆኖም ፖለቲከኞች ከታሪክ ውስጥ የሚፈልጉትን መርጠው ወይም ፈጥረው የፖለቲካ እምነት ወይም ርዕዮተአለም ይሰራሉ። ርዕዮተአለም ፖለቲካዊ ሃይማኖት ነው። በውስጡ አክራሪም ለዘብተኛም አማኞች ስለሚሳተፉበት እንደመሪወቹ ለዘብተኛም ጽንፈኛም ባህሪ ይንጸባረቅበታል። የርዕዮተአለም አላማ የዱሮውን ታሪክ ለመዘከር ወይም ለመቀየር ሳይሆን መጭውን ጊዜ ለመቆጣጠር የሚያስችል የተደራጀ ሃይል ማሰባሰብ ነው። ይህንን የተደራጀ ሃይል የሚያሰባስብበት ዋናው መንገድ ተከታዮቹን ሊያስተባብር የሚችል የጋራ እምነት በመፍጠር ነው። የምእራባውያንን የፖለቲካ አስተሳሰብ በሚከተሉ ሰወች ዘንድ ይህ የጋራ እምነት የሚፈጠረው የጋራ ጠላት በመፍጠር ብቻ ነው። የጋራ ጠላት ከተፈጠረ በኋላ ተከታዮቹ አንድነታቸውን፣ ቆራጥነታቸውንና ታማኝነታቸውን የሚያረጋግጡት የጋራ ጠላት ያሉትን በመፈረጅ፣ በማግለል፣ ባለመተባበር፣ በማጥላላት፣ በመስደብ፣ በመግደል፣ በማፈናቀል ሊሆን ይችላል። ይህንን የሚያደርጉት በተሳሳተ የታሪክ አረዳድ ሳይሆን በራሳቸው የውስጥ ፖለቲካዊ አንድነትን ለመፍጠር ሆን ተብሎ በተመረጠና በተቀናበረ ትርክት በመመራት ነው። ስለዚህ ታሪካዊ ትርክትን እንደግባት ቢጠቀምም፣ ርዕዮተአለም ተከታዮቹን በስሜት ለማታገል የሚፈጠር የፖለቲካ ሃይማኖት ነው። ዛሬ አማራ ተብለው የሚሞቱት ሰወች ከነገስታቱ ዘመን ጋር የሚያገናኛቸው ምንም አይነት የስልጣን ወይም የኢኮኖሚ ትስስር እንደሌለ ገዳዮቹም አይጠፋቸውም።

 

ከዚህ አንጻር፣ በአማራ ላይ የሚደርሰው ጥቃት የታሪክ ስህተት ሊባል የማይገባበት ብዙ ምክንያቶች አሉ። ከኢሃዴግ የስልጣን ዘመን ጀምሮ፣ የአማራን ህዝብ ብቻ ነጥሎ ከነገስታቱ ዘመን ጋር ያገናኘው የጨቋኝነት ትርክት የብሄር ፖለቲካ ዋና ማደራጃ ርዕዮተአለም አካል ሆኗል። ርዕዮተአለም ደሞ ከላይ እንዳልሁት በባህሪው ከታሪክ ይልቅ ለሃይማኖት ይቀርባል። በታሪክ ትንታኔ አይቀየርም። ምክንያቱም ዋናው አላማው ትናንትን ሳይሆን ነገን ለመቆጣጠር የሚያስችል ስርዐት መፍጠር እንጅ እውነተኛ የታሪክ ዘገባ ማስተጋባት አይደለም። በጥላቻ ላይ የተመሰረተ ርዕዮተአለም ከተፈጠረ በሗላ፣ አማራወች “አጥፍታችኋል” የሚባሉትን ሁሉ አሜን ብለው ቢያምኑ እንኳን፣ ጥላቻው የባህል የፖለቲካና የህግ መሰረት ከያዘ በኋላ ርዕዮተአለሙን ማፍረስ ማለት የተፈጠረውን የሃይል ስብስብ የመበተን ያህል ከባድ ይሆናል። ምክንያቱም በብሄር ማንነት ብቻ የተደራጀ ፖለቲካ የብሄር ጠላት ያስፈልገዋል። በመደብ ማንነት የተደራጀ ፖለቲካ የመደብ ጠላት ያስፈልገዋል። በጥቂት ግለሰቦች ስብከት፣ የታሪክ ማስረጃ በመደርደር፣ ወይም ለችግሩ እውቅና በመንፈግ ሊቀየር አይችልም። የአንድ ፖለቲካ ለዘብተኛነትና አክራሪነት የሚለካው ‘ጠላት’ ብሎ የፈረጀውን አካል በሚያስተናግድበት አግባብ ነው።

 

ከላይ እንዳልሁት ጠላትን በመፍጠርና በማጥቃት ግለቱን ጠብቆ የሚጓዝ ርዕዮተአለም በህይወት ለመቀጠል ሲል የራሱን ለዘብተኛ አባላት ጨምሮ ማንኛውንም ሰው በጠላትነት መፈረጁንና ማጥቃቱን ይቀጥላል።። በዚህ ሂደት መጨረሻም ራሱን በራሱ የሚያጠፋበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። በአክራሪ ርዕዮተአለም ሽፋን የሚፈጸመውን ወንጀል በህግ መዳኘት ካልተቻለ የሚፈሰው ደምና የሚፈጸመው ወንጀል እንደጀግንነትና ድል ስለሚቆጠር የብዙ ሰወችን ጭፍን ድጋፍ ያገኛል። በተለይም በሃገርቤትና በውጭ ወንጀሉን የሚያድበሰብሱ ወይም ምክንያታዊ የሚያስመስሉ ትርክቶች (አሁን እንደሚታየው) ሲሰራጩ መንግስት የርዕዮተአለሙን አክራሪ ባህሪ ከመቀየር ይልቅ የራሱን ባህሪ ለአክራሪወቹ በሚመች መንገድ ማስተካከል ይጀምራል። ለአክራሪወቹ አባላት ስልጣን ማደል ይጀምራል። በሂደትም አክራሪነትን የሚደግፉ ሰወች ስልጣን ላይ ይበዙና በመንግስት ፖሊሲና ተቋማት ውስጥ የአክራሪወቹ አድሏዊ ፍላጎቶች በስውር ብቻ ሳይሆን በግልጽ መንጸባረቅ ይጀምራሉ። ያኔ የጥላቻ ርዕዮተአለም የሙስናና የህገወጥነት ጭምብል ይሆናል። እዚህ ላይ የአለማቀፉ የገንዘብ ስርዐት ባህርይም ለዚህ አስተዋጾ ያደርጋል።

 

ብዙወች የውጭ መንግስታት በሃገራችን የሚፈጸመውን ግፍ ቢያውቁ ኖሮ ይደርሱልን ነበር ብለው ያስባሉ። ሆኖም፣ ላይስሙላ ካልሆነ በቀር፣ የውጭ መንግስታት የድሃ ህዝቦች ህይወት አያሳስባቸውም። የካፒታሊዝም ስርዐት ካፒታል ወይም ካፒታል የሚፈልገው ክህሎት የሌላቸውን ሰወች እንደሸክም እንጅ እንደሰው አይቆጥራቸውም። ለካፒታሊዝም ጥቅም የማይሰጡ ሰወች

 

3


 

የያዙትን የተፈጥሮ ሃብት ለካፒታል አስረክበው እንዲለቁ ይፈልጋል። ሰወቹን ግን አይፈልጋቸውም። ይህ የካፒታሊዝም ባህሪ አፍሪካ ውስጥ የእርስበርስ ግጭትን (ዋርሎርድ ፖሊቲክስ) ለራሱ መጠቀሚያ ለማድረግ ያልማል። አፍሪካውያን አብዛኛው ህዝባቸው ለካፒታሊዝም የሚጠቅም ስላልሆነ ሰወቹን ከያዙት ሃብት የሚነትልላቸውን ሃይል በግልጽም ባይሆን ይፈልጉታል። ትኩረታቸው የራሳቸውን ጥቅም የሚያስከብር የጸጥታ ፖሊሲ መከተል ሲሆን ለዚህ አላማቸው ከእርዳታ መስጠት እስከ ጦር ሰፈር ምስረታ ድረስ ይሰራሉ። ባራክ ኦባማ በአህጉሪቱ አፍሪኮም በሚል አደራጅቶት የሄደው 36 የጦር ሰፈር የአፍሪካውያንን ሰብዐዊ መብትን ለመጠበቅ አይደለም። በቅርቡ የአለማችን አንደኛ የመሬት ከበርቴ የሆነው ቢልጌት የአፍሪካ ህዝብ መብዛት የአለም ህዝብ የስጋት ምንጭ መሆኑን በግልጽ ሲናገር ሰምተናል። ቻይና የአፍሪካን ጥሬ እቃ እንዳታጣ ለመሪወቹ የፈለጉትን ሁሉ ታደርጋለች። ሰሞኑን ራሺያ 10 የሚደርሱ የጦር ካምፖችን ለመመስረት በመሯሯጥ ላይ ናት። ሌሎችም እንደ ህንድ፣ ቱርክ፣ ሳኡዲ ወዘተ አፍሪካን ለመቀራመት ይሯሯጣሉ። ይህ ሁሉ የሚያሳየን አፍሪካ ዛሬ ያለችው በበርሊን ኮንፈረንስ ዘመን ከነበረችበት የቅርምት ጊዜ ላይ መሆኗን ነው። የሚፈልጉት መሬቷን፣ ውሃዋን፣ ማእድኗን፣ ከህዝቧ ነጻ አድርጎ የሚያስረክባቸው አሽከር መንግስት ነው። በተለይም የሰው ጉልበት የማይፈለግበትና ሁሉንም ስራ በቴክኖሎጂ መስራት የሚቻልበት ጊዜ ላይ ስለደረስን፣ በዚህ ዘመን በህጋዊም ሆነ በህገወጥ መንገድ ድሃውን ህዝብ ከተፈጥሮ ሃብት እየነጠለ መሬቱን ለካፒታል የሚያቀርብ፣ ለትርፍ የተቋቋመ የኮርፖሬሽን አይነት ቅርጽ ያለው ወንጀለኛ መንግስት አጥብቀው ይፈልጋሉ። ይህ መንግስት ቢዝነስ እንዲሰራ የሚፈልጉት ከግል ኩባንያወቻቸው ጋር ነው። ይህን የሚያደርጉበት አንዱ ምክንያት ራሳቸውን ከወንጀሉ ነጻ በማድረግ ለሰብዐዊ መብት የቆሙ ለመምሰልና አገልግሎቱን ሲጨርስ በሌላ መንግስት ለመተካት ነው። ይህንን ዘዴ በኮንጎ፣ በአንጎላ፣ በቻድ፣ በዛምቢያ፣ በናይጀሪያ፣ በሱዳን፣ ወዘተ በግልጽ እየተገበሩት ነው። የእነዚህን አሳሳቢ ሁኔታወች ከእኛ ሁኔታ አንጻር በዝርዝር ለማቅረብ ሌላ ርዕስ ያስፈልጋል። ማለት የፈለግሁት ግን እስካሁን ባለው ልምድ፣ የውጭ መንግስታት ዋና ፍላጎት የራሳቸውን ጥቅም የሚያስከብር ስርዐት እንዲኖር ማድረግ ብቻ ስለሆነ አክራሪ ብሄርተኝነት ከነሱ ጥቅም ጋር ካልተጋጨ በደስታ አብረውት ይሰራሉ። እንደውም የህዝቡን አጀንዳ ከኢኮኖሚ ላይ ሳይሆን ከፖለቲካው ላይ እንዲያተኩር ስለሚያደርግ የብሄርተኝነትን ፖለቲካ ይወዱታል።

 

ከላይ እንደገለጽሁት በማንነት ላይ የሚፈጸም ግድያንና መፈናቀልን የሚያህል ከባድ ወንጀል የለም። መንግስት ለማንነት ጥቃት የሚሰጠው መልስ የራሱን የመንግስትን ማንነትና ባህሪ የሚያሳይ ነው። በማንነታቸው የተጠቁ ሰወች ከአካላዊ ጥቃቱ በላይ በቃላት የማይገለጽ የስነልቦና ስብራትና ውርደት ይሰማቸዋል። የተጠቁት በማንነታቸው ስለሆነ ማንነታቸው ዋጋ እንዳለውና እንደሚከበር የሚያሳይ እርምጃ ካልተወሰደ ዋጋቢስነትና ውርደት ይሰማቸዋል። በተለይ ጥቃቱ ሆን ተብሎ እንደእንስሣ እንደሆኑ በመቁጠር በአሰቃቂ ሁኔታ የተፈጸመ ከሆነ ሰው መሆናቸው እንዲሰማቸው የሚያደርግ አካሚ ድጋፍና እንክብካቤ ያሻቸዋል። መንግስት ይህንን የሚያደርገው የተጠቃው ማንነት የእኔም ማንነት ነው ብሎ ሲያምን ነው። ስለሆነም በማንነታቸው የተጠቁ ሰወችን ጉዳይ ቁጥር አንድ አጀንዳ ካላደረገው የተጠቂወቹ የመኖር መብት በመንግስት አይጠበቅም ማለት ነው። ይህም ተጠቂወቹ ዝቅተኛነታቸውን እንዲቀበሉ፣ አጥቂወቹ ታሪክ ሰሪ እንዲባሉ የሚያደርግ አደገኛ መልዕክት ያስተላልፋል። በሂደትም የመንግስት ስርዐት ዋና ባህሪ ለፍትህና ለህጋዊነት ዋጋ የማይሰጥ ስለሚሆን በዚያው ልክ ዜጎችም ለመንግስትና ለህጋዊነት ዋጋ የማይሰጡ መሆን ይጀምራሉ። በንጹሃን ሰወች ላይ የሚዘገንን ጥቃትን የሚፈቅድ ወይም የሚታገስ ህሊና ያላቸው ባለስልጣኖች ወደፊት የፖለቲካ ወይም የጥቅም ባላንጣወቻቸውን ይቅር ይላሉ ብሎ ማሰብ አዳጋች ነው። እስካሁን ባቀረብሁት ገለጻ አማራነትን በታሪክ አተረጓጎም ስህተት የተፈጠረ ማንነት አድርጎ ከማየት ይልቅ የብሄርተኝነት ልሂቃን የርዕዮተአለም ጠላት አድርገው በመሳል የተከታዮቻቸው ማታገያ ያደረጉት ማንነት መሆኑን በመገንዘብ ለዚህ የሚመጥን ምላሽ ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ይህን ምላሽ ወደፊት ከማየታችን በፊት ለሃሳብ ጥራት ይረዳል የምላቸውን ጥቂት ነጥቦች ላንሳ።

 

በአማራነታቸው የተጠቁ ሰወች ‘ዜጎች’ ናቸው ወይስ ‘አማሮች’?

 

 

ሰብዐዊነት የተፈጥሮ ስጦታ ነውና ሁሉም ሰው በሰውነቱ እኩል ነው። መንግስት የተፈጥሮ መብቶችን ለያንዳንዱ ግለሰብ የሚያስጠብቅበትን ህግ ታሳቢ በማድረግ በተለምዶ ‘የዜግነት መብት’ ብለን እንጠራቸዋለን። ዋናው ቁምነገሩ ሰው በተፈጥሮ

  

 

ያገኛቸውን መብቶች መንግስት የመጠበቅ ሃላፊነት አለበት የሚለው ነው፡፡ ይህን ሃላፊነት የሚወስድ መንግስት የሌላቸው ሰወች፣ ዜግነት አልባ (ስቴትለስ) ሊሆኑ ይችላሉ። በማይንማር 600000 የሚደርሱ ሮሂንጋ የሚባሉ ጎሳ አባላትን መንግስት የእኔ ዜጎች አይደሉም ስላላቸው ዜግነት አልባ ሆነዋል።

 

ወደሃገራችን ስንመለስ በህግ “ኢትዮጵያዊ አይደለህም” የተባለ ስለሌለ በማንነት የሚጠቁ ሰወች ችግር ለጊዜው የዜግነት ችግር አይደለም። አማራም ይሁን ትግሬ፣ አፋርም ይሁን ኦሮሞ ወዘተ ሁሉም ዜጎች በሁሉም የሃገሪቱ ቦታ ያለዐድልዎ የመኖር መብት እንዳላቸው በህገመንግስቱ ተደንግጓል። ሆኖም ወደተግባራዊነቱ ስንመለስ፣ ይህ የግለሰቦች መብት ከብሄሮች ሉዐላዊነት ስር ወድቋል። ህገመንግስቱን ተከትሎ በተደራጀው የብሄርተኝነት ርዕዮተአለም ሳቢያ፣ በአማራ ህዝብ ላይ እንደዜጋ ሳይሆን እንደአማራነት የተፈጠረ ማፈናቀልና ግድያ ተፈጥሯል። ግድያው አንድ ወቅት ብቻ የተከሰተ ሳይሆን፣ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ፣ እጅግ ዘግናኝ ግፎች የተፈጸሙበትና በበርካታ ቦታወች የተከሰተ ነው። በበደኖ፣ በአርባ ጉጉ፣ በገለምሶ፣ በጋራ ሙለታ፣ በወተር፣ በሃብሩ፣ በአጋሮ፣ በአሰቦት፣ በሸቤ፣ ወዘተ በገደል በመወርወር፣ በቢላዋ በመታረድ፣ በእሳት በመቃጠል፣ በጥይት በመደብደብ አማራ ማንነት ባላቸው ላይ አሰቃቂ ግፍ ተፈጽሟል። የአገዳደል ዘዴው ራሱ በማንኛውም ንጹህ ዜጋ ላይ የሚፈጸም የተለመደ አይነት ወንጀል አይደለም። የነፍሰጡር ሴትን ሆድ ቀዶ ልጁን በማውጣት ለእናት መስጠት፣ በእሳትና ዱላ ደብድቦ መግደል፣ ህጻናትን ማረድ፣ አስከሬን ጎዳና ላይ መጎተት የመሳሰሉ የጭካኔ ድርጊቶች እንደተፈጸሙ ማስረጃወች ያስረዳሉ። ከግድያው ጀርባ በአማራነት ላይ የተዘራውን ጥላቻ ምክንያታዊ የሚያስመስሉ የትምህርት፣ የጥናት፣ የሃይማንኖት፣ የሃውልት፣ የስነቃል፣ የሙዚቃና የትጥቅ እንቅስቃሴወች አሁንም አሉ። በዚህ አውድ የሚፈጸምን በደል ‘በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርስ በደል’ ብሎ መጥራት የመሳለቅ ያህል ነው። እዚህ ላይ አንዳንድ ሰወች በየዋህነት ‘ግን ምን ችግር አለው ዜጋ ቢባሉ” ስለሚሉ አንዳንድ ነጥቦችን ማየት ያስፈልጋል።

 

አንዱ ምክንያት በብሄር ማንነታቸው የሚገደሉ ሰወችን ባልተገደሉበት ምክንያት ዜጋ ብሎ መጥራት ማለት ገዳዮቻቸው ተራ የግድያ ወንጀል የፈጸሙ እንጅ የዘር ጥቃት ያደረሱ እንዳልሆኑ የሚያደርግ ከለላ መስጠት ነው። የሰብአዊ መብት ድንጋጌወች ሁሉ የዘር ተኮር ጥቃትን ከዜጎች ተራ ጥቃት የተለየ ትኩረት የሚሰጧቸው ብሄርተኝነትን ለማስፋፋት ፈልገው አይደለም። ጉዳዩ ከተራ ወንጀል በተለየ መልኩ አለማቀፍ ትኩረትና መፍትሄ ስለሚያስፈልገው ነው፡፡ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ከተገደለ በኋላ ሁኔታውን አጣርቶ የኢትዮጵያ ሰብዐዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው ዘገባ ላይ ግድያውን በሰብዐዊነት ላይ የተፈጸመ ከባድ ወንጀል እንደሆነና የዘር ማጥፋት ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል ያለውን ስጋት አስታውቋል። ይህ አይነት ወንጀል አለማቀፍ ወንጀል ነው። ወንጀሉ በኢትዮጵያዊነት ላይ ካለን የአመለካከት ልዩነት ጋር አይያያዝም። ወንጀሉ አንድን ማንነት የፖለቲካ ጠላት አድርጎ በመሳል፣ ከፖለቲካ ውጭ የሚኖሩ ድሃ ገበሬወችን ለግልጽ ጥቃት የሚያጋልጥ፣ ሰላማዊ ዜጎች በወገኖቻቸው ላይ ግፍ እንዲፈጽሙ የሚያነሳሳ ኢ-ሰብአባዊነት ነው። ምንም አይነት አላማ ቢኖረው፣ ይህ አይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሰላማዊ ሰወችን ማጥቃት በጀመረበት ሰአት ከፖለቲካ አውድ ወጥቶ ወደአሸባሪነትና ኢሰባዊነት አውድ እየተሸጋገረ ነው ማለት ነው። ይህ የአሸባሪነት የሽግግር ሂደት ዝም ከተባለ፣ በገዳዮቹና በተገዳዮቹ ብቻ የሚቆም የዜጎች ጠብ ሳይሆን ኦሮሞና አማራ በሆኑ ሰወች መካከል ሁሉ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ጥላቻን የሚያሰራጭና፣ የህዝቦችን ተስፋ እስከመጨረሻው ከንቱ ሊያስቀር የሚችል አደገኛ መርዝ ይሆናል። ይህን ወንጀል ለማስቆም የመጀመሪያው ተግባር የወንጀሉን የፖለቲካ ጭምብል አውልቆ አረመኔያዊ ድርጉቱን ለህዝብ በግልጽ ማሳየት ይሆናል። ከዚያም የመገናኛ ብዙሃን የጥቃቱ ሰለባ የሆኑትን ሰወች ታሪክ ለህዝብ በክብር በማሳወቅ፣ ሽማግሌወችና የሃይማኖት መሪወች የእርቅና ምክክር ስራቶችን በህዝብ ፊት እንዲፈጽሙ በማድረግ፤ የህዝብ ለህዝብ ውይይት በመክፈት፣ በመንግስት በኩል አጥፊወችን በህግ በመቅጣት፣ ተጎጅወችን በማቋቋምና በመካስ፣ እንዲሁም እርዳታ በማሰባበር የተጎዱትን ለማቋቋም ጠንክሮ መስራት አለበት። ይህ ጥረት በሃገሪቱ የሰላምና የትብብር ተስፋ መፍጠር ይቻላል። ይህን ካላደረገ ግን ጥቃቱን ይደግፈዋል ወይም አይቃወመውም ማለት ነው።

 

የማንነት ጥቃትን በስሙ አለመጥራት የምንከተለው ስርዐት ለመብት የማይመች መሆኑ ታውቆ አስፈላጊ መሻሻሎች እንዳይደረጉ ያደርጋል። መቸም በህይወት ከመኖር መብት የሚበልጥ መብት ያለ አይመስለኝም። የመንግስት ዋና ሃላፊነት ህይወትን መጠበቅ

ነው። የህገመንግስቱ አቀራረብ ብሄርተኝነትን እንደሉዐላዊ የጋራ መብት ስለሚቆጥር፣ መንግስት የግለሰብ መብትን አስከብራለሁ የሚለው በብሄርተኝነት መዋቅር ውስጥ አልፎ ነው። ይህ የቱንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆንም የመንግስትን ሃላፊነት ግን አያቀልለትም። መንግስት የተፈጥሮ መብት በብሄር ልዩነት እንዳይረገጥ የማድረግ አለማቀፋዊ ግዴት አለበት። በማንነት ላይ የሚፈጸም ጥቃትን በስሙ የማንጠራው ከሆነ ግን ይህንን ግዴታ ከመንግስት ትከሻ ላይ እናወርድለታለን። ጉዳዩ የስርዐት ችግር ወይም በፖለቲካ ስም የሚፈጸም ከባድ ወንጀል ሳይሆን የጥቂት ሰወች ህገወጥነት ችግር ብቻ ተደርጎ እንዲታይ ይሆናል። ይህ ደግሞ በሌላ አባባል የብሄር ፌደራሊዝሙ አተገባበር የፖለቲካ ወንጀልን ከህግ ቁጥጥር ውጭ አድርጎ እንዲቀጥል ያደርጋል:: ከዚህ በዘመናዊ የጦር መሳሪያ ከተደራጀ ገዳይ ሃይል በስተጀርባ ማን እንዳለም ለማወቅ አይቻልም። የአሜሪካን ጨምሮ በርካታ መንግስታት ከተጠያቂነት ለመሸሽ ህገወጥ ቡድኖችን አስታጥቀው ብዙ ወንጀል ስለሚያስፈጽሙ፣ ህዝብ መንግስትን እንዳይጠራጠር ከተፈለገ ጥርት ያለ መረጃ መስጠትና ቁርጠኛነቱን በተግባር ማሳየት አለበት።

 

የማንነት ጥቃትን በስሙ አለመጥራት ጽንፈኝነትን የበለጠ ያባብሳል። ዘር ተኮር ጥቃት በአለማቀፍና ሃገራቀፍ ደረጃ በስሙ ካልታወቀ መንግስትም ይሁን ጽንፈኞች እርምጃቸውን ለማስተካከል የሚያስገድድ ጫና እንዳይደርስባቸው ምክንያት ይሆናል። እንደውም በተቃራኒው ጽንፈኞች ያለማንም ተከራካሪ ትርክታቸው ትክክለኛ የፖለቲካ ምክንያትና የህዝብ ድጋፍ እንዳለው አድርገው ለማቅረብ ነጻ እድል ያገኛሉ። ዘርንና የፖለቲካ እምነትን በሚያደባልቅ ሁኔታ ኦሮሞም ይሁን ጉራጌ፣ ትግሬም ይሁን አማራ ብቻ የኢትዮጵያዊነት ወይም የአንድነት ፖለቲካ አቀንቃኝ የሆኑትን ሁሉ ‘አማራ’ በሚል ስም በመፈረጅ፣ ለጠላታቸው የብሄር ማንነት በመስጠት፣ የራሳቸውን የብሄር ትግል በህዝቦች የማንንት ልዩነት ላይ ይመሰርታሉ። የጥቃታቸው ሰለባ የሚሆኑትን ሰላማዊ ሰወች ከፖለቲካ ጠላቶቻቸው ጋር አንድ ማንነት እንዳላቸው አድርገው ከፈረጁ በኋላ ወንጀልን የተቀደሰ የነጻነት ትግል አካል አድርገው ለማቅረብ ይመቻቸዋል። ይህ ሰላማዊ ህዝቦችን ለከባድ ወንጀል የሚያጋልጥ አሰራር በግልጽ ካልተነገረና የህዝብ ተቃውሞ ካልገጠመው በሃገር ብቻ ሳይሆን በውጭም ብዙ አድማጭ ያገኛል። ምክንያቱም አብዛኛው የአለም ህዝብ አፍሪካውያንን የብሄር ዘረኞች አድርጎ ስለሚያይ የኢትዮጵያን ነባር ገጽታ በቀላሉ ወደሌላው የአፍሪካ የጎሳ ዘረኝነት ታሪክ ለመቀየር ከባድ አይሆንበትም።

 

በማንነት ላይ የሚፈጸምን ጥቃት በግልጽ አለመታገል የፖለቲካ ትርፍ ማግኛ እንዲሆን ያደርገዋል። በዜግነት ወይም በኢትዮጵያ አንድነት እናምናለን የሚሉ ልዩ ልዩ ፖለቲከኞች ከፖለቲካ ተሳትፎ ውጭ የሆነው የአማራ ህዝብ በነሱ የፖለቲካ አቋም ምክንያት የሚደርስበትን ጉዳት ተገንዝበው በማንንት ላይ የሚፈጸምን ወንጀል ከፖለቲካ በመለየት ለአለም ለማሳወቅ ሲጥሩ አይታዩም። ይባስ ብለው በአማራ ማንነት የሚደርሰውን የሰብዐዊ መብት ጥቃት በግልጽ ባለመናገር ራሳቸውን ከብሄር ፖለቲካ የነጹና ገለልተኞች የሆኑ አድርገው ለማቅረብ ሲሞክሩ ይስተዋላሉ። ይህም በማንንት ላይ የሚፈጸመው ወንጀል የህግ ሳይሆን የፖለቲካ አጀንዳ ብቻ ሆኖ እንዲጥል አስተዋጾ ያደርጋል። እነዚህና ሌሎችም ምክንያቶች በማንንት ላይ የሚፈጸም ወንጀልን እንደፖለቲካ መሳሪያ የሚጠቀም ባህልን ያጠናክራሉ። ይህ ሁኔታ ወደፊት ከቀጠለና በማንነት ላይ የሚደርሰው ወንጀል እንደተድበሰበሰ ከቀረ፣ መንግስት ራሱ በአክራሪነት የተፈጠረውን የፖለቲካ ሃይል የራሱ አጀንዳ ማስፈጸሚያ ያደርገዋል። በዚህም ምክንያት ሃገሪቱ የከፋ የአድልወ ስርዐት ውስጥ ልናገኛት እንችላለን። ይህንን ሁኔታ ለመቀነስ በተለይም ከመንግስት የሚጠበቀው የመጀመሪያው እርምጃ በማንነት ሳቢያ የሚደርሰውን ግድያና መፈናቀል በስሙ በመጥራትና፣ በህግ እንዲዳኝ እንጅ የፖለቲካ ትርፍ ማግኛ እንዳይሆን ማድረግ ነው።

 

በማንነት ላይ የሚደርስ ጥቃት በስሙ መገለጽ ያለበት ከተጠቃው ማንነት ጋር የሚያያዝ መፍትሄ ስለሚያስፈልገው ነው። በአማራ ማንነት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በስሙ አለመጥራት የሚጠቃውን የአማራ ማንነት ለመታደግ ምንም ነገር እንዳይደረግ ያደርጋል። በህይወት የመኖር መብት ከሁሉም መብቶች ስለሚበልጥ የመንግስት ቀዳሚ አስፈላጊነት ይህንን መብት ማስከበር ነው። መንግስት የሰወችን በህይወት የመኖር መብት አሁን ባለው የብሄርተኝነት መዋቅር ውስጥ ማረጋገጥ ካልቻለ፣ ያለው ብቸኛ አማራጭ ከግለሰቦች ጋር እንደብሄር የፈጸመውን ህገመንግስታዊ ጋብቻ አፍርሶ እንደዜጋ መዋዋል ይሆናል። (እርግጥ ይህን እሚያደርግ ከሆነ የዜግነት መብቶች የብሄር መብትን እንዳይረግጡ ማድረግም ይኖርበታል)። ያኔ ሰወች በብሄር ስማቸው ቢገለጹ

 

ወይም ባይገለጹ ላያከራክር ይችላል። አሁን ግን ዜግነት በራሱ በቂ ሆኖ በማይከበርበት ሁኔታ፣ የብሄር ጥቃትን በስሙ አለመጥራት፣ አማራወችን ያለህገመንግስት ከለላ ራቁታቸውን ማስቀረት ይሆናል። መርሳት የሌለብን እውነታ፦ የተጎጅወቹን ጥቃት የብሄር ማንነታቸው ምክንያትየደረሰ ነው ብሎ አለመጥራት ህይወታቸውን ከብሄር ፖለቲካ ነጻ አያደርገውም። ይልቁንም፣ በህይወታቸውና በኑሯቸው ላይ የተፈጸመው ወንጀል የፖለቲካ አጀንዳ ማራገቢያ ሆኖ ይቀጥላል። (በነገራችን ላይ ዜግነትም ይሁን ብሄርተኝነት ከባዕዳን የቀዳነው ትርከት እንጅ ከሃገራችን ህዝብ ባህልና ልምድ የወረስናቸው ሃሳቦች አይደሉም። ሁለቱም ሳይኖሩ ኢትዮጵያ ለብዙ ጊዜ ኑራለች)

 

አንዳንዶች አማራወች ተበደሉ ብሎ መናገርን ለአንድ ብሄር መቆም እንደማለት አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ ይህ አተያይ ግን የተበዳዮቹን ሰብዐዊ መብት በራስ ርዕዮተአለም ብቻ ከማየት የሚነሳ ስህተት ነው። የዘር ፖለቲካን አልቀበልም የሚለው እሳቤ ችግር የለበትም፡፡ በእኔ እምነት የብሄርም ይሁን የአንድነት ፖለቲካ ከህዝብ ውስጥ በፈለቁ ፍላጎቶችና እሳቤወች ካልተመራ አብዛኛውን ድሃ ህዝብ አያገለግልም። ያም ሆነ ይህ፣ ፖለቲከኞች የአንድነትም ይሁን የብሄርተኝነት ፖለቲካን የማራመድ መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከሰላማዊው የአማራ ህዝብ ጥቃት ጋር ተያይዞ እየተነሳ ያለው ጥያቄ የርዕዮተአለም ሳይሆን የመብትና የገሃዱ አለም ጥያቄ መሆኑን ማስታወስ ይገባቸዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ትግሬም ይሁን አማራ፣ ኦሮሞም ይሁን ኮንሶ እንደዜጋ ብቻ ሳይሆን፣ እንደብሄር ማንነቱም እንድንቆምለት የሚያስገድድ ሁኔታ ተፈጥሯል። የቱንም አይነት የተለያየ የፖለቲካ እሳቤ ቢኖረን፣ የማንነት መብት የፖለቲካ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የህግ ጉዳይ ስለሆነ ይህ መብት ሊከበር ይገባል። ይሁን እንጂ፣ ህገመንግስቱ የብሄር ማንነትን በህግ መከበር እንዳለበት መብት አድርጎ ከደነገገ በኋላ አፈጻጸሙን ግን አማራነትን ተከባሪ ሳይሆን ተጠቂ እንዲሆን በሚያደርግ የፖለቲካ አውድ ላይ ጥሎታል። መንግስት ይህ የፖለቲካ አውድ የህግ መብትን እንዳይጥስ የማድረግ ግዴታ አለበት። ይህን ካላደረገ መንግስት የአማራን ማንነት በህግ የፈጠረው ለማስከበር ሳይሆን ለማስጠቃት አልሞ ነው ብሎ ለመናገር ያስደፍራል።

 

ለማጠቃለል፣ የአማራም ይሁን የአፋር፣ የትግሬም ይሁን የኦሮሞ፣ የጉራጌም ይሁን የኮንሶ ማንኛውንም ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት በሚፈጸምበት ጊዜ በኢትዮጵያ አንድነት አምናለሁ የሚል ሰውየማምነው በዜግነት እንጅ በብሄር አባልነት አይደለም በማለት ወይም በሌላ ምክንያት ጥቃቱን ተራ ጥቃት አድርጎ መመልከት የለበትም። በብሄርተኝነት የሚያምንም ሰው “የማምነው በብሄርተኝነት እንጅ በዜግነት አይደለም” ብሎ ጥቃቱን ዝም ሊል አይገባውም። ይህንን ማድረግ ፖለቲካ ከህግ ቁጥጥር ውጭ እንዲሰራ መተባበር ነው። በማንነት ላይ የሚፈጸም ጥቃት ከፖለቲካ አጀንዳነቱ በፊት ከፍተኛ የሆነ አለማቀፍ ወንጀል ነው። የማንነት ውንጀላ በህግ ካልታረመ ማንኛውንም ሰው በሰበብ ባስባቡ ሰለባ ስለሚያደርግ ማህበረሰባችንን በፍርሃት አስሮ የሚያኖር ሰንሰለት ይሆናል። “ያንተ መብት በእኔ የፖለቲካ እሳቤ ካልተቀረጸ አያገባኝም” ማለት ከሰው ህይወት የራስን ርዕዮተአለም ማስቀደም ይሆናል። በሌላ አባባል የወንጀሉን ግዝፈት ተቀብሎ በስሙ መጥራትና ማውገዝ የመፍትሄ ፍላጎት ምልክት ነው።

 

12

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ገድሎና አስገድሎ ብፁዕ እየተባሉ መኖር የተፈቀደላቸው ጳጳሳትና ቆሞሳት እንዳይረሱ

ከጥር 27 ጀምሮ በተለያዩ የኦሮምያ ከተሞች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና ውጭ የተሾሞና በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዘው የተለዩ አካላትን ወደ ቤተ ክርስቲያን እናስገባለን ባሉ የመንግስት የጽጥታ አካላት በተትኮሰ ጥይትና ሕገ ወጡ ቡድን ባደራጃቸው ወጣቶች ተደብድበው የተገደሉና የቆሰሉ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህናትና ምእመናን።።   1)  ሻሸመኔ ከተማ   I.   የተገደሉ 1.  አያሌው ተረፈ ●   በሻሸመኔ የደብረ አስቦ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ማህደረ ፃድቃን ሰንበት ትምህርት ቤት አባል ●  ጥር 27 ዓ/ም በሻሸመኔ ከተማ በጸጥታ ሃይሉ በሚመራ የጨፍጫፊ ቡድን በደረሰበት ከፍተኛ ደብደባ ወደ ሆስፒታል ገባ ●  በአላቲዮን ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገለት ሕይወቱን ማትረፍ አልተቻለም ●  በ ጥር 30 2015 ዓ/ም  ሰማዕትነትን ተቀብሏል       2.  ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ሐረገወይን ●  የሻሸመኔ ደብረ ስብሐት ቅዱስ ሚካኤል አገልጋይ የነበሩት ●  በሻሸመኔ በሕገወጦች በጸጥታ አካላት  በበግፍ በዱላ ተቀጥቅጠው በጭንቅላታቸው በእጅና በእግራቸው ላይ በደረሰባቸው ድብደባ በሀዋሳ ሕክምና እያሉ አርፈዋል። ●  ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት ተመትተው  በያኔት ሆስፒታል ሕክምና ሲደረግላቸው ቢቆዩም ሕይወታቸውን ማትረፍ አልተቻለም። ●  በዛሬው ዕለት ጥር 30 2015 ዓ/ም  ሰማዕትነትን ተቀብለዋል።     3.  ዘማሪ ፍቃዱ ደጉ ●  የቅዱስ ሚካኤል ከሣቴ ብርሃን ሰ/ትቤት አገል...

ኢትዮጵያ የተገዳደሯትን ሁሉ ቅኝ ገዥወች የተከላከለችባቸው፣ የተዋጋችባቸውና ነጽነቷን ያስከበረችባቸው እሴቶች; በቀሲስ አስተርአየ ጽጌ

የጽዋዕ ማህበራትና ሰንበቴ ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋራ የተሳሰሩት የጽዋ ማሕበራትና ሰንበቴወች ናቸው፡፡  ኢትዮጵያ የተገዳደሯትን ሁሉ ቅኝ ገዥወች የተከላከለችባቸው፣ የተዋጋችባቸውና ነጽነቷን ያስከበረችባቸው እሴቶች  ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ  nigatuasteraye@gmail.com  ሚያዚያ ፳፩ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም.  (April 28, 2025)  መግቢያ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናችን ኩለንታዊት ቀዳማዊት ደኀራዊት፡ ዘመናዊት ናት ስትባል እም ኀበ አልቦ አይደለም፡፡ በብዙ እሴቶቿ ነው፡፡ ኩለንታዊት ከምታደርጋት ከብዙ እሴቶቿ መካከል የጽሑፌ መነሻ የሆኑት ከቅድስት ድንግል  ማርያም ጋራ የተሳሰሩት የጽዋ ማሕበራትና ሰንበቴወች ናቸው፡፡ ስንበቴ በቀጥታ ከእግዚአብሔር የታዘዘች ናት፡፡ የጽዋ ማኅበርም እንደ ሰንበቴው ቀጥታ ከግዚአብሔር ባይሆንም፡ በዮቶር በኩል ለሙሴ የደረሰው የግዚአብሔር ምሪት ናት፡፡ የጽዋ ማሕበርና ሰንበቴ የትርጉማቸው መነሻ፡ መድረሻና የመጨረሻ ዋና ዓላማቸው ሰባዊ ክብርና ነጻነት ነው፡፡   ኢትዮጵያ የተፈታተኗትን ሁሉ ቅኝ ገዥወች ከተከላከለችባቸው ከተዋጋችባቸውና ነጽነቷን ካስከበረችባቸው ዋናወቹ እሴቶቿ ውስጥ የጽዋ ማሕበራትና ሰንበቴወች ናቸው፡፡ በቅኝ ገዥወች ሲቀጠቀጡ ከኖሩት ካጎራባች አገሮች ልዩና የነጻነት ምሳሌ ያደርጓትም የጽዋ ማህበርና ሰንበቴ ናቸው፡፡ የጽዋ ማኅበራትና የሰንበቴ ድርጅቶች እንዴት ተመሰረቱ? ለኢትዮጵያ ምን ጠቀሙ? ትሩፋታቸው ምንድነው? የደርግንና የወያኔን ዘመናት እንዴት ተሻገሩ? በብልጽግና ዘመንስ እንዴት ናቸው? እንዴት ይቀጥሉ ? የሚሉትን ጥያቄወች ለመመለስ ከጽዋ ማኅበር እንጀምር፡፡   የጽዋ ማኅበር መነሻ...

ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን እና ቋንቋና ማንነት ተኮር እንቅስቃሴዎች

  ኦ ርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን እና ቋንቋና ማንነት ተኮር እንቅስቃሴዎች   ፩ . ቋንቋን በተመለከተ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮና ትውፊት ከሰው ልጅ መበደል በፊት ፍጥረት ሁሉ የሚግባባው በአንድ ቋንቋ ነበር፡፡ “ ምድርም ሁሉ በአንድ ቋንቋና በአንድ ንግግር ነበረች” እንዲል፡፡ ዘፍ. 11፡1 በኃጢአት ምክንያት ግን ሰውና መላው ፍጥረት በአንድ ቋንቋ መግባባታቸው ቀረ፡፡ ኃጢአት እየበዛ ሲሄድ የሰው ልጅ ቋንቋም በባቢሎን ተደበላለቀ፣ አንዳቸው ከሌላቸው ጋር የማይግባቡ ብዙ ዓይነት ቋንቋዎችም ተፈጠሩ፡፡ በበደል የመጣውን ሁሉ ሊያስተካክልና ሊያድን በመጣው በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት ያ የቀደመው ጸጋ ስለ ተመለሰልን በበዐለ ሃምሳ ሰዎች በልዩ ልዩ ቋንቋ አንድ ዐይነት የእግዚአብሔርን መልእክት ሰሙ፡፡ በዚህ ጸጋ የተጠቀሙና የበቁ ቅዱሳን የእንስሳትን ቋንቋ እስከ ማወቅ ደረጃ ይደርሳሉ፡፡   የክርስትና ጉዞ ወደ ቀደመው በአንድ ቋንቋ መግባባት መመለስ ነው፡፡ ወደዚያ ለመድረስ ደግሞ ሰው የእግዚአብሔርን ቃል በሚሰማው ቋንቋ መማር አለበት፡፡ በበዐለ ሃምሳ ጊዜ ለቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ብዙ ቋንቋ የገለጠላቸው ሰውን ሁሉ የእግዚአብሔርን የማዳን ጸጋ በሚሰማው ቋንቋ እንዲያስተምሩት ነው፡፡ ሆኖም ቋንቋ መልእክት ማድረሻና መግባቢያ እንጂ ከዚያ ያለፈ ሰዎችን በሆነ መደብ ለመመደብና የልዩነት አጥር ለመሥራት እንደ መሳሪያ ሊሆን አይገባውም፡፡ ይህ ከክርስትና ዐላማ ጋር ተቃራኒ ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ወደ ዐለም ሁሉ ሲልካቸው ሰዎች የሚቀበሏቸው በሚያስተምሩት ትምህርት መሠረት ነበር እንጂ በትውልድ፣ በብሔርና በመሳሰለው መስፈርት የእኛ ናቸው/አይደሉም በሚል አልነበረም፡፡ የቤተ ክርስቲያ...