ግንቦት 2 ቀን 2007 ዓ .ም.
ዋሺንግተን ዲሲ በተደረገው ትዕይንት ላይ ሊቀርብ እንደተዘጋጀ
ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ።
“ጸርሁ በዓቢይ ቃል”
የታረዱት ነፍሳት ጩኸት
“ርኢኩ ታህተ ምስዋዕ ነፍሶሙ ለእለ ተቀትሉ በእንተ ቃለ እግዚአብሔር ወበእንተ ዘአቀቡ ህጎ። ወጸርሁ በቃል ዓቢይ ወይቤሉ እስከ ማእዜኑ እግዚኦ ቅድስ ወጻድቅ፤ ኢትትቤቀሎሙኑ ወኢትኴንኖሙኑ በእንተ ደምነ እምእለ ይነብሩ ዲበ ምድር” “ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ! እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም? ደማችንንስ በምድር ላይ እስከ መቼ አትበቀልም?” እያሉ ከመሰዊያ በታች ሆነው የታረዱት ነፍሳት በታላቅ ድምጽ ሲጮኹ አየኌቸው (ራዕ 6፡9-10)።
ዓለም በግልጽ ያያቸው በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ በየደረሱበት የታረዱትን ብቻ ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ግን በውስጥም የተገደሉትን ሁሉ የኢትዮጵዮውያ ነፍሳት ሲጮሁ ማየት አለብን።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናችን(ገአረ ኢየሱስ በህማሙ። ወጸርሀ ኀበ አቡሁ. . .ወእንዘ ሀሎ ህየ ጸርሀ ሀበ አዳም ገብሩ፤ ወሀበ ኩሎሙ ደቂቁ(ሰለስቱ ምእት ገጽ 205፡97-99)የሚለውን አንድም ብላ እንዳስተማረችን፤ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሳለ ጮኸ። በአምላክነቱ ለባህርይ አባቱ፤ በሰባዊነቱ ደግሞ ለባህርይ አባቱ ለአዳምና ለወገኖቹ ለደቂቀ አዳም አሰማ። ይህ ድምጽ ለሚድኑት ምልጃና ድህነት ሲሆን፤ ጩኸቱን ሰምተው ለማይድኑት ግን መፈራረጃ ነው። በማይድኑት ላይ የተነጣጠረው ይህ የክርስቶስ ጩኸት መፈራረጃ እንደሆነ፤
የታረዱትን የነዚህን ነፍሳት ጩኸት በመስማት፣ በመንቃት፤ ነቅተንም እንዲጮሁ ያደረጋቸውን ምክንያት ተረድተን፤ ተገቢውን ኃላፊነት በማንወስድ ሰዎች ላይ የሚመጣብንን ክስና ፍርድ ያሳያል።
ከመንደራቸውና ካገራቸው እየበረገጉ በአይሲስ እንዲታረዱ በደቡብ አፍሪካ በእሳት እንዲቃጠሉ ያስደረገው ምክንያት፤ ነቢዩ ዳዊት “ተማሰጡነ ጸላእትነ። ወወሀብከነ ይብልዑነ ከመ አባግእ። ወዘሮከነ ውስተአህዛብ፤ ወመጠውከነ ህዝበከ ዘእንበለ ሴጥ” መዝ 43፡10) እንዳለውም፦ ከየመንደራቸው የበረገጉት በመበርገግም ላይ ያሉት ሁሉ “ሰውን እንደበግ ቦጫጭቀው ለሚበሉን ወደ ተኩላነት ለተለወጡ ሰዎች ተዳረግን” እያሉ ናቸው።
ለካህናት ክርስቲያኖች ሲሞቱ መፍታትና ሰማዕታት ብለናቸዋል ማለት ብቻ በቂ አይደለም። ከሚጮሁት ክስና ወቀሳ ነጻ ልንሆን አንችልም። የእግዚአብሔር ዓይንነታችን ካልተሸፈነብን በቀር፤ ከማነንኛውም ምድራዊ ኃይል በፊት ለዚህ የሚዳርጋቸውን ምክንያት አሻግረን ልንመለከትና ቀድመን የማየት፤ አይተንም፤ በአስቸኳይ የሚቆምበትን መንገድ የማግኘት ሀለፊነትና ግዴታ አለብን። ሃላፍነታችንን ለመወጣት ከመጣር ይልቅ፤ ክርስቶስ “ይዘብጥ ይበልእ ይሰቲ ምስለ ሰካርያን . . . . በጊዜ ኢያእመረ ይሰጥቆ እማእከሉ። ወይሬሲ መክፈልቶ ምስለ መደለዋን ሃበ ሀሎ ሀቀየ ስነን“(ማቴ 24፡50)እንዳለው ካሳዳጁ፣ ከበታኙና ካስበርጋጊው ጋራ ባለን ስውርና ግልጽ ግንኙነት ሀላፊነታችን ሳንወጣ ብንቀር መጀመሪያ በተመልካቹና በታዛቢው ህዝብ፤ በመጨረሻም በይግባኝ ሰሚው አምላክ ካስበርጋጊውና ካራጁ ጋራ መፈረጃችን የማይቀር ነው። የታረዱት ነፍሳት ምን እያሉ ነው የሚጮኹት?
“ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ! እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም? ደማችንንስ በምድር ላይ እስከ መቼ አትበቀልም?” እያሉ የሚጮሁት በምድር ባሉት ደማቸውን ባፈሰሱትና ለደማቸው መፍሰስ ምክንያት በሆኑት ሁሉ ላይ ነው።
የእግዚአብሄር መልአክ “ወይከውን ብእሴ ሀቅል፤ እደዊሁ ለዕለ ኩሉ። ወዕደ ኩሉ ላዕሌሁ”(ዘፍ 16፡ 12) እንዳለው፤ ይህም ማለት፦ “እጃቸውን በዓለም ላይ የሚሰነዝሩ የዓለምም እጅ በነሱ ላይ የሚሰነዝርባቸው፤ እረፍት የለሾች፤ ያልተገሩ ፣ አደገ መረቦች፤ ዓለምን የሚረግጡ፤ ዓለምም የሚረግጣቸው ናቸው” በማለት ስለ አይሲሲ አረመኔነነትና የጨለማው ገዥ ሠራዊትነታቸውን፤ የእግዚአብሔር መላክ አስቀድሞ ገልጿቸዋል።
የአይሲስወችን ጭካኔና አረመኔነት መልአኩ ከገለጸበት በላይ ለመግለጽ ምድራዊ ቋንቋ ፈጽሞ ፈጽሞ ፈጽሞ የለንም። “ደማችንንስ በምድር ላይ እስከ መቼ አትበቀልም?” የሚለው የታረዱት ነፍሳት ጩኸት፤ ለመታረዳቸውምክንያታዊ ንክኪ ባላቸው ሁሉ አካላት ላይ ያነጣጠረ ነው።
ምድር ላይ ለሚደረጉ ክፉና ደግ ነገሮች ያለ ምክንያት የሚከሰቱ አይደሉም። መድረሻ እንዳላቸው መነሻም አላቸው። አድራጊ፣ አስደራጊና አደራራጊ ተብለው ተፈርጀዋል። የመጀመሪያው ተከሳሽ በእጁ ተግባሩን የፈጸመው
አይሲሲ ቢሆ ንም፤ አስደራጊና አደራራጊን ሳንነካ አይሲሲን ብቻ ከሰን የምናልፍ ከሆን እንስሳትን መሆን ነው።
እኛ እግዚአብሔር በአርያው የፈጠረን ሰዎች፤ ከወገናቸው አንዱ ታርዶ በደሙና በፈርሱ ዙሪያ ጮኸው ወደ በረታቸው እንደሚገቡ እንስሳት አይደለንም። ማን አረደው? እንዴት?፣ ለምን ታረደ ብለው አይጠይቁም። እኛ ግን ወደ ኋላ፣ ወደ ፊት፣ ወደቀኝና ወደ ግራ እያየን እንድንራመድ ተፈጥረናልና እንጠይቃለን። እንደ ነቢዩ ዳዊት “ወሥጋሆሙኒ ለጻድቃኒከ ለአራዊት ምድር፤ ወሀጥኡ ዘይቀብሮሙ” በአረመኔዎች የተገደሉት የወዳጆችህ ሥጋ የሚቀብራቸው አጣ። አራዊቶች በሏቸው እያልን፤ “ከአው መዓተከ ላዕለ ሕዝብ እለ ኢየአምሩከ” የሚለውንም እንናገረዋለን።
በጨለማው ገዢ አይነ ልቡናቸውን ሸፍነው ሰው በየሚያሳድዱት ላይ፤ ሳውል በደማስቆ የነበሩትን ክርስቲያኖች በሚያሳድድበት ወቅት “የሳኦልን ዓይን የሸፈነውን ጥቁር ቅርፍት ለመግፈፍ ድንገት በሳውል ዙሪያ ከሰማይ የደፋህበትን የብርሃን ጎርፍ ልቀቅባቸው።” እንላለን። (የሐዋ 9፡3- 18)። በአረመኔነት መንፈስ የገረረውን ህሊና ሰብረህ ከአረመኒያዊና ከአራዊታዊነት ወደ ሰውነት ለውጣቸው። በአርያህ የፈጠርከውን ሰው በማሰር በመደብደብ እያስመረሩ እያስበረገጉ ለበይ ለአውሬ የሚያቀብለውንም ሁሉ አስገድዶ አንተ ያዘዝከውን የሰውን በጎ ፈቃድ እንዲያከብሩ አይናቸውን ክፈት። ይህ ቤተ ክርስቲያናችን የምትናገረው ነው።
የነፍሳት ክስ ባድራጊው ላይ ብቻ አይቆምም። በምድራችን ለሚከሰቱ ነገሮች አድራጊ አስደራጊና አደራራጊ አሏቸውና። ለምን ከመንደራቸው ለቀው ወደ አራጆች አገር ሄዱ? ምን አስኬዳቸው? ማን አሳደዳቸው የሚለውን የማንነካው ከሆ፤ ከመካከላቸው ስለታረደው ወገናቸው ማን አረደው? ለምን ታረደ? ብለው ሳይጠይቁ በፈርሱ ላይ ጓጉረው ከሚበተኑ እንስሳት አለመሻል ነው።
“ወላእለ መንግሥት እንተ ኢጸውአት ስመከ” (መዝሙር 78፡6) ወደ ሚለው እንሻገራለን። አባቶቻችን ይህን ተርጉመው ከነገሩን ጋራ የታረዱትን ነፍሳት ለዚህ የዳረጋቸው ምን እንደሆነ ነፍሷን ይማርና “ካላጡካልተቸገሩ፤ ማን መኖር ይጠላል ባገሩ” በማለት ማን አህሎሽ ዲቦ በእንጉጉሮዋ ነግራን አልፋለች። ከመንደራቸው ካገራቸው እያሸበረ፤ ያስበረገገና በመበርገግ ላይ ሳሉ እየተቀበለ የሚበላቸው አለ። ነቢዩ ዳዊት “ተማሰጡነ ጸላእትነ ከመ ይብልዑነ” እንዳለው “በይና አስበይ ተናጠቋቸው” ካስበርጋጊው እየተቀበለበሚበላው አውሬ መካከልና ባስበርጋጊው መካለል ምንም ልዩነት የለም። ይህንም በተደራጊ አድራጊና አስደራጊ መካከል ያለውን መናጠቅ ቤተ ክርስቲያንችን በግልጽ ተርጉማ አስተምራናለች።
የእሳት ቃጠሎ ድምጽ ሰምቶ እሳቱን ለማጥፋት ይረዳ ዘንድ ድንገት የደረሰ ጎረቤት መሆን ተገቢ አይደለም። እሳቱ በላያችን ላይ የነደደብንና ቤታችን፣ ንብረታችን የተቃጠለብን ሰዋች ነን። ሊረዳ የመጣ ጎረቤት እሳቱን በውሀም ባፈርም ለማጥፋት ከተራዳ በኌላ ወደ ቤቱ ይመለሳል። የተቃጠለ ያራል። ቤቱና ንብረቱ የተቃጠለበት አመድ ላይ ይቆማል ። እኛ ትኛው ነን? ጩኸት ሰምቶ ሊረዳ የመጣውን? ወይስ በሰውነቱ ላይ እሳት የነደደበትን? ይህንም እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካህናት አብራርተን ለሚመለከተው ሁሉ ህብረተ ሰባዊ አካል፤ ማለትም:- ለታጣቂው ወታደር፣ ለባለ ሀብታሞች፣ መናገር አለብን።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ካህናት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት ባረመኔዎች ለተገደሉ ነፍሳት እንደ ተስፋ ቢሶች በምሾ አውራጅነትና በአስለቃሽነት ላይ ብቻ አናተኩርም። “እመሰኬ ለከፎ ርኩስ ወስዑበ ነፍስ ኢይረኩስኑ እምዝንቱ” ተብሎ በነቢዩ ሀጌ በኩል እግዚአብሄር የተነገረውን እንድናስታውስ አባቶቻችን ያስተማሩንን ልንዘነጋ አይገባም። ይህም ማለት፤ “ባፋችን በሚጎረስ እንጀራና ወጥ ይቅርና በሳንቲም ድቃቂ ካድራጊውና ካስደራጊው ጋራ ንክኪ እንዳይኖረን፤ ቢኖረን አገልግሎታችን ክህነታችን እንደሚረክስ” ተነግሮናል።
“ወይእዜኒ ሐልዩ በልብክሙ ዘእምቅድመ ቀዳሚት ዕለት ወዘእምቅድሜሃ” (ሐጌ 2፡ 16)እንግዲህ ከዛሬ ጀምራችሁ ከናንተ በፊት የነበሩትን አስቡ እንደተባለው ከኛ በፊት የነበሩትን በተመሳሳይ ወቅት የልብሳቸውን ዘርፍ ሳያነካኩ ያለፉትን ካህናት አባቶቻችንን እንድናስብ ይህ ወቅት ያስገድደናል።
“ይባእ ቅድሜከ ገአሮሙ ለሙቁሀን፤ ወበከመ ዕበየ መዝራእትከ ተሠሀሎሙ ለደቂቀ ቅቱላን” (መዝ 78፡10፡11)። “የታሰሩት ሰዎች ጩሀታቸውን ተቀበልልን፤ ሊገደሉ የተፈረደባቸውንም ታደግልን። የሚለውን ዳዊት መድገም የምንችለው ከገዳዮች እና ካስገዳዮች ንክኪ ስንርቅ ብቻ ነው።
ይህን በግልጽ የማይመሰክር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ካህን፤ ቤተ ክርስቲያንን በነፍሳት ላይ የሚደርሰውን መከራና ስቃይ እንዳታይ ዓይኗን ለመጋረድ፤ እንዳትሰማ ጆሮዋንም ለመድፈን፤ እንዳትናገር አፏን ለማፈን ሆን ብሎ ሰርጎ የገባ ነው። ቤተ ክርስቲያናችን ካልታፈነች በቀር ለወታደሩ ለባለ ሀብቱ የምትናገረው ቃል አላት።
ለወታደሮች
በሀገራችን ንብረት የተዘጋጀውን የወታደር ልብስ የለበሳችሁ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች። የለበሳችሁት
ልብስ፤ የታጠቃችሁት መሳሪያ የኢትዮጵያን ልጆች ለመታደግና ድንበር ሰብሮ ከሚገባ ጠላት የሚደርስባቸውን
መታረድ ለመከላከል እንጅ፤ በይና አስበይ እንዲናጠቋቸው ከተወለደቡት ከመንደራቸው እየደበደባችሁ
ለማስበርገግ ለማሳደድ እና ለአይሲሲዎች ቢለዋ ለመዳረግ አይደለም። ያስደራጊውን ትእዛዝ እየሳማችሁ ወገናችሁን
ለአራጁ ለአይሲሲ ማቀባላችሁን አቁሙ! እያለች ቤተ ክርስቲያናችን ትጮሀለች።
ባለሀብቶች
“ኦ አብእልት ንዑ ይዕዜኒ ወብክዩ እንዘ ትግእሩ ላዕለ ህርትምናክሙ። ብእልክሙኒ ነቅዘ ወአልባስክሙኒ ቆንቆነ። ወርቅክሙኒ ወብሩርክሙኒ ዝህለ ወዛህሉኒ ስምአ ይከውን ላዕሌክሙ። ወይበልኦ ለሥጋክሙ ከመ እሳት በእንተ ዘገበርክሙ”(ያዕ 5 ፡1-3)። ሲል ቅዱስ ያዕቆብ እንደተናገረው፤ ማለትም፦ “እናንት ሀብታሞች እንግዲህስሙ! ዘግይቶ ስለሚደርስባችሁ መከራ አታልቅሱ ዋይ ዋይ አትበሉ!ሀብታችሁ ሻግቷል። ልብሳችሁንም ብል በልቶታል፤ ወርቃችሁና ብራችሁ ዝጓል፤ ዝገቱም በእናንተ ላይ ይመሰክራል፤ ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበለዋል”
ይህ አስፈሪ ማስጠንቀቂያ የተሰነረው ካስደራጊው ጋራ ባላቸው ንክኪ በህዝባቸው ላይ የሚደርሰውን መከራና ግፍ እንዳያዩ አዕምሯቸው ለፈዘዘባቸው ህሊናቸው በጭካኔ ቁልፍ ለተዘጋባቸው ለስስታምና ስግብግብ ሀብታሞች ነው።
ይህን ለማስረዳት ቀደም ብለው የተጻፉትን የተአምራት መጻሕፍት መግለጽ አያስፈልገንም። ለየወሀን ልብ ቅርብ የሆነው አምላክ በዘመናችን የፈጸመውን ገና በስንክሳራችን ያልተመዘገበውን ተአምር መጥቀስ እንችላለን።
ተአምር
ለክፉም ለደግም እንድንማርባቸው በሥጋዊና በመንፈሳዊ በኩል ተአምር(ምልክት) ከመስጠት እግዚአብሄር አላቋረጠም።
ለክፉው፦ ነፍሳቸውን ይማርና በሥጋዊ አመራር አቶ መለሰ፤ በመንፈሳዊ አመራር አቡነ ጳውሎስ ባንድ ወቅት ካንድ መንደር ተጠራርተው መጥተ ህዝቡን ከፋፍለው ለ 20 አመታት ሲያስለቅሱ ከቆዩ በኋላ፤ አንዲት ጥይት ሳይተኮስ እርስ በርሳቸው ተጠራርተው በሞት ኢትዮጵያን እንዲለቋት እግዚአብሔር መፍቀዱ ትልቅ ተአምር ነው። ቤተ ክርስቲያን በመሬት ከተዘረጋችበት ጊዜ ጀምሮ በስንክሳራችን ከተጻፉት ቀደም ብለው ከተከሰቱት ትንግርቶችና ተአምራት ይህ በዘመናችን የተከሰተው ተአምር አንዱ ነው።
ለመልካም አርያ፦ “አርአያሃሰ አኀዊነ ለትዕግስተ ተጽናስክሙ ብክሙ ነብያት እለ ተናገሩ በቃሉ ለ እግዚአብሔር።”(ያዕ 5፡10)እንዳለው ቅዱስ ያዕቆብ፦ እምነታቸውን ሳይለቁ በአይሲስ የታረዱት ራሳቸውን እየፈቱ ለሰማዕትነት በሱዳን ሰይፍ የመረጠችው ቅድስት እህታችን፤ በጅማ በሸሻ በስበርጋጊው የተገደሉትና በመገደል ያሉ ሁሉ ምልክቶች ናቸው።
እነዚህ ተአምር የተከሰተባቸው ሰማእታት ራሳቸውን ፈተዋል። ዓለም በሰማእታትነት ሰይሟቸዋል። “የመልካቸው ደም ግባት ድንቅ ነበር። እግዚአብሔርን ስለ አመለኩት ሞትንም ስለአልፈሩት ከሁሉ የምትበልጥ የልቡናቸው ደም ግባት ናት” (1ኛ መቃ 2፡12)። ተብሎ እንደተጻፈላቸው “ናሁ ናስተብጽዖሙ ለእለ ተአገሱ” እንላቸዋል። የነዚህ ሁሉ ነፍሳት ጩኸት ብቻ አይደለም። ያለምንም ፍርሀትና ይሉኝታ “ይባ ቅድሜከ ገአሮሙለሙቁሀን” እያልን ታራሚዎች እየተባሉ በየቦታው በግፍ የታሰሩትን ሁሉ ጩኸት፤ ለፈጣሪና ለዓለም የማሰማት ሀላፊነት አለብን።
በመጨረሻም፦ “አሌ ለ ክሙ ጸሐፍት ወፈሪሳውያን መደለዋን እለ ተሀጽብዎሙ ለጽዋዕ ወለጻህል እንተአፍሀሆሙ ወእንተ ውስጦሙሰ ምሉእ ሀይድ ወአመጽ ወትእግልት። ቅድመ ህጽቦ ለጻህል ወለ ጽዋዕ እንተውስጡ፤ ከመ ይኩን ንጽሀ እንተ አፍአሁ”(ማቴ 23፡25)ሲል በተናገረው አጠቃልላለሁ። ይህም ማለት፦
“እናንተ ሞኞች ንጹህ ውሀ ለመጠጣት። የምትጠጡበትን ጽዋ ውስጡ የጸዳ ይሆን ዘንድ አስቀድማችሁ ውስጡን እጠቡት እንዳለው፤ የተደረገውን አሰቃቂ መከራ ደግመን ላለማየት፤ መጀመሪያ ካስደራጊነትና ካደራራጊነት መንፈሳችንን ልባችንን አካባቢያችንን ቤተ ክርስቲያናችን አገራችን ለማጽዳት ሙሉ ልብ እምነትና ሞራል ሊኖረንይገባል።
እስካሁን የተጓዝንበትን መንገድ እንደሆነ ለሁላችንም ግልጽ ነው። ይህን የተሳሳተ መንገድ ርግፍ አርገን ትተት የጋራ ኃይላችንን እውቀታችንን ሀብታችን በማስተባበር የችግሩ መነሻ በሚደርቅበት ላይ እናውለው። ይህን ብናደርግ ከእንግዲህ የሚታረዱና የሚቃጠሉ ወገኖች አይኖሩም፤ ራሳችንንም ከታረዱትና ወደፊትም ከሚታረዱት ነፍሳት ክስ ነጻ እንሆናለን። ይህ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ድምጽ ነው።
ይህን ሰምተን በተግባር እንዳናውለው የታረዱት ነፍሳት ክስ ተቀባዩ አምላክ ይርዳን።
አሜን!
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ