አማራን ከአማራነት እሴቶቹ መንቀል የአማራ ህልው ጠላቶችን ነጽሮተ-ዓለም መሸከም እንጂ “ፋኖነት” አይሆንም!
ማሳሰቢያ፦ ይህ ጽሑፍ የእኔ የፋንታሁን ዋቄ የግል ምልከታ እና የኦርቶዶክሳዊ ማያዬ ውጤት እንጂ የማንም ፖለቲካዊም ይሁን ሃይማኖታዊ ማኅበራት፣ ቡድን እና ትምህርት ተቋም ውክልናን የሚገልጽ አይደለም። በዚህ ምክንያት የሚመጣ ስሕተትና ውጤቱ ሁሉ እኔን ብቻ ይመለከታሉ። የፕሮፓጋንዳ ሤረኞች ለሌላ ፍጆታ ሊያውሉት ስለሚችሉ ጥያቄዎችን በቀጥታ ወደ እኔ በመላክ ውይይቶችን መክፈት እንደሚቻል በዚህ አጋጣሚ አሳውቃለሁ። ለትግሉ ስኬታማነት አስተዋጽዖ የሚያደርግ፣ ቅን ውይይት የሚፈልግ፣ እና ከመንጋ የቡድን-ዕሳቤ ባርነት (groupthink slavery) ነጻ የሆነ በዚህ የቴሌግራም ማስፈንጠሪያ በኩል ያግኘኝ @Wakie_EOTCissues
እስከ አሁን ስለ አማራነትና ፋኖነት የተናገርኩትን ለመፈተሽና ከሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ለመጠበቅ የምጠቀማቸው ሚዲያዎቼ ሁሉ የሚከተሉት ናቸው፦
1. ትዊተር፡- https://x.com/fwakie
2. ቴሌግራም፡- @Fantahun_Wakie
3. ዩቲዩብ፡- https://youtube.com/@Orthodoxy-VS-Secularism
4. ዩቲዩብ፡- https://youtube.com/@finoteretuan-2
5. ፌስ ቡክ፡- https://facebook.com/profile.php?id=61576051634449
6. ፌስ ቡክ፡- https://facebook.com/fwakie
7. ቲክቶክ፡- https://tiktok.com/@fantahunwk?_t=8qLqoSRV9Ta&_r=1
8. ብሎግ፦ https://ethiopiaorthodoxchristian.blogspot.com/
ሐምሌ ፲፯ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም.
ተጻፈ ከፋንታሁን ዋቄ
አማራን ከአማራነት እሴቶቹ መንቀል የአማራ ህልው ጠላቶችን ነጽሮተ-ዓለም መሸከም እንጂ “ፋኖነት” አይሆንም! 1
2
መግቢያ፦ 3
የዚህ ጽሑፍ መነሻ መግፍኤ፦ 3
የጽሑፉ ዓላማ 4
ፋኖነትና ታሪካዊ ዳራው ምን ይመስላል? 4
የህልውና አደጋ የተጋረጠባቸው ክፍለ-ሕዝቦች የሚሹት እውነተኛ ፋኖነት እና ጠባብ ልዩ ፍላጎቶችን ለማሳካት መሣሪያ ሆኖ የሚፈጠር ‘ፋኖነት’ ይለያያሉ 6
የህልውና አደጋን ለመቀልበስ የአደጋው መንስኤ የሆኑ አካላትን ብሔርተኝነትና እንግዳ የባዕድ ርዕዮት መዋስ ያዋጣል? 9
በስሙ ወጣቶች የሚሞቱለት አማራ ማነው? 12
አማራነት ለምን ዒላማ ተደረገ? አማራነት ጠላቶቹን ለማሸነፍ ማንነቱን በምን እሴት ቢገልጽ ያዋጣዋል? 12
አማራነት ፖለቲካ-ሥር (ፍጡር) ወይስ የማኅበራዊ፣ የሃይማኖታዊና ታሪካዊ እሴቶች ተፈጥሮአዊ ሂደት ግኝት ነው? 14
የአማራ የአሸናፊነት ምሥጢሮቹ ምንድን ናቸው? 15
አማራነትን በአማራው ደም መፍሰስ የማጥፋት ረቂቅ ሤራ 15
የአማራን ጠላት የሚዋጋ መስሎ አማራነትን ወደ መውጋት ሊለወጥ የሚችል ዕይታ 19
ከአዲስ የደምና አጥንት አማራነት እና ከነባሩ የእሴት አማራነት መካከል የቱን እንምረጥ? ለምን? 19
ፋኖአዊ የአማራነት ተጋድሎን ለፋሽስታዊነት ካጩት ጠላቶች ለመታደግ የምሁራንና ደጋፊዎች ሚና 20
ሕዝብ አክባሪ ፋኖነት መገለጫው በሕዝቡ እሴቶች መመራት እና የመስዋዕትነት ዋጋውን ትርፋማ በማድረግ ላይ ማተኮር ነው 21
በፋኖ ውስጥ ለትግሉ ውጤታማነት እንቅፋት የሚሆኑ አሉታዊ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎችና ቡድኖች ፍላጎት ምንድን ነው? 24
ትግሉን ዘገምተኛና ከተነሳበት ቀዳሚ ግቡ ውጭ ሊያደርጉት የሚያስቡ ሰዎች ንግግርና ድርጊት እንዴት ይታወቃል? 24
የአማራን የህልውና ትግል መሠረታዊ ግቦች የሚቃረን የሐሰተኝነትና የነባር-ጠልነት የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ለምን? 26
ለክቡር ዓላማ ነፍሱን የሰጠን የፋኖ ሠራዊት ከዓላማውና ከዕሤቱ የሚቃረኑ ጮሌዎች እንዴት ሊያታልሉት ቻሉ? 27
መግቢያ፦
የዚህ ጸሑፍ መሪ ቃላት ፪ ናችው፦
፩) የሁላችን ስለነበረችዋና አሁን ላይ ስለተወሰደችብን አገር ተመልሳ የሁላችን እኩል መኖሪያ መሆን በግልጽ እንነጋገር!!
፪) ሕዝብን በቦታና በቋንቋ ተካፍሎ መገልገያና መጠፋፊያ ማድረግ የሚያበቃበት ሰዋዊ ፖለቲካዊ ርዕዮት እናዋልድ!!
የሚሉ ሲሆን --
ጽሑፉ የ፶ ዓመታት የዘር ማጥፋት ሂደትን ለመግታት ባስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ የተወለደውን የህልውናና የፍትሕ ተጋድሎ ጫፍና መገለጫ የሆነውን ክቡር ፋኖነትን መነሻና ማእከል ያደረገ ነው። ምክንያቱም ሌሎች ቀዳሚ ንቅናቄዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የክልልና የሀገር መንግሥት ነን ብለው ያሉ አካላት ሁሉ ተጠቃለው ከሰውነት የሚያስበልጡት ፖለቲካ-ሥር የሆነና ለተለያዩ ማኅበረሰባዊ የባህል፣ የእምነት፣ የታሪክ፣ የአሠፋፈር እና የትርክት መሠረቶች የህልውና አደጋ በመደቀን በሰው ልጆች ክብር ዋጋ አዲሥነትን የሚያቀነቅኑ እንደሆኑ ግልጽ ስለሆነና --- ድጋፍና ምክር የማይቀበሉ ሆነው ላለፉት ፶ ዓመታት ነባርነትን በአፍራሽ ትርክቶችና መዋቅራት ማጥቃት ላይ መጠመዳቸው ስለሚታውቅ ነው።
በተቃራኒው የፋኖነት ማእከላዊ መርሕም ሆነ ታሪካዊ መሠረት ከጎጥ፣ ከዘረኝነት፣ ከታሪክና ሃይማኖት የለሽነት፣ ከአገር አፍራሽነትና ከባእዳን ተላላኪነት የጸዳ በመሆኑ ነው።
ይህ ፋኖአዊ እሴት በአማራ ማኅበረሰብ ውስጥ መቀጣጠሉ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ማኅበርሰቦች፣ እምነቶችና ባህሎች ዋስትና በመሆኑ በቅርበት መጠበቅና ምክረ-ሐሳቦች፣ ግብረ-መልሶችና ተግሳጻት በማቀበል ከሠርጎ-ገቦችና አርቆ አለማየት አስቷቸው ፋኖነትን ወደ ጠባብ ግብ መድረሻ ከሚመሩ ቁማርተኞችና ሤረኞች በመጠበቅ በመጀመሪያ ደረጃ ህልውና አደጋ በግልጽ የተጋረጠበትን ኢትዮጵያዊ-ክፍለ-ሕዝብ ማዳን፤ በሁለተኛ ደረጃ ዘለቄታዊ የህልውና ዋስትና ሁሉም ዜጋ የሚያገኝበትን ሁለንተናዊ አገራዊ አውድ፣ ቀጠናዊና ዓለም ዐቀፋዊ ግንኙነት በማጽናት ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ነው።
የዚህ ጽሑፍ መነሻ መግፍኤ፦
ይህን ጽሑፍ እንድጽፍ ከገፋፉኝ አያሌ ምክንያቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፦
፩) ፋኖነትን ወደ ሽፍትነት፥ ወደ ፋሽስታዊ ብሔርተኝነት፥ ወደ አምባገነናዊ ሥልጣን ጠቅላይነት፥ ብሎም ወደ ጎጠኝነት ለማዝቀጥ ሙከራ እየተደረገ ለመሆኑ የተቀናጀ የማኅበራዊ ሚዲያው መልእክት ፍንጭ መስጠቱ፤
፪) ፋኖነትን እንደ ቀደሙት ማርክሳዊ፥ ጎሣዊ ነጻ አውጭ ነን ባዮች በሴኩላር ፖለቲካ ስም ከባእዳን ጋር እየተነጋገሩ እና በውጭ-ገብ ጸንፈኛ እምነቶች ኅቡዕ እና ግልጽ ጫና፥ እንዲሁም ፋኖነት እንዳያሸንፍ “በእንደጋገፍ” ሽፋን በጎሠኝነት ርእዮታቸው ፋኖነትን ለመበከል የእነርሱን መርዛማ ብሔርተኝነት የሚያለማምዱ አካላትን የሚመስሉ ድምጾች አየሩን መቆጣጠራቸው ብቻ ሳይሆን የአማራ ፋኖ አደረጃጀቶቸን የአንድነት ጉዞ ሲያደነቃቅፉ ማየቴ፤
፫) ፋኖነት ባንዳነት፣ ጊዜአዊ ግራ መጋባት እና ለመፋነን እጅግ አሣሪ ሁኔታዎች ወይንም በአእምሮ አጣቢ የፖለቲካና የትምህርት ብልሽት፣ ምክንያት ከማይረዱት በስተቀር የሁሉም ኢትዮጵያውያን ገንዘብ ሲሆን፣ በአገራችን ፋኖነትን ያዳከሙ ውጭ-ገብ ፖለቲካዊ ርእዮቶች፣ ጽንፈኛ አገር-ጠል እምነቶች፣ ነባርነት ላይ የዘመቱ ሐሰተኛ ትርክቶች አዳክመውታል፤ ይሁን እንጂ እንደመታደል ሆኖ ቀጥተኛ ሁለንተናዊ (አካላዊ፣ ታሪካዊ፣ እምነታዊ፣ ርስታዊ፣ ባህላዊ፣ ማኅበራዊ እና ሰብአዊ ክብር) የህልውና ጥፋት የታወጀበት ኢትዮጵያዊው የአማራ ክፍለ-ሕዝብ ፋኖነትን ሕይወት ዘርቶበት ጥፋትን ለማስቆም በሚያደርገው ዋጋው እጅግ ከፍ ያለ ተጋድሎ ውስጥ ቢሆንም--- ከሚከፈለው ዋጋ እና ከሚፈለገው ታላቅ ግብ አንጻር ሲመዘን እጅግ ያነሱ ጉዳዮችን አጀንዳ በማድረግ የትግሉን ፍጥነት የሚያዳክሙ አስተሳሰቦች፣ መቧደኖችና ፕሮፓጋንዳዎች ስለናኙ፤
፬) በፋኖ ትግል ተብራርቶ የተጻፈ እና ለብዝኃ ፍላጎቶች ግልጽ የሆነ የአቋም ሰነድ፣ ለወደፊቱ አገራዊ የፖለቲካና የአስተዳደር አቅጣጫ፣ የአፍሪካ ቀጠናና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዕሳቤዎች፣ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰቦች የሰላምና የህልውና ዋስትና ማኅቀፎች ባለመኖሩ ምክንያት --- ቀደም ሲል የአገሪቱን ፖለቲካ በዘረኝነትና በቁማርተኝነት፣ በነባር-ጠልነትና በተላላኪነት የተውሶ ርዕዮት ለመምራት ሞክረው ለዚህ ለምንገኝበት ሁለንተናዊ ውድቀት የዳረጉን ቡድኖችና ግለሰቦች እየተሰባሰቡ ፋኖነትና ነባርነትን የሚወክሉ ሐሳቦች በማይገኙበት አውድ መምከር ብቻ ሳይሆን ከባእዳን ድጋፍ ማግኘት የፋኖን ተጋድሎ ድምዳሜ የሚያበላሽ የሥልጣን ነጠቃ ዝግጅት መስሎ ስለሚታየኝ፤
፭) አንድን ሕዝብ በንብረትነት በመቁጠር እኛ ከምንለው ውጭ ማሰብም ሆነ ማለም አይቻልም የሚል የሐሳቦች ሁሉ ሞኖፖሊ ለመያዝ የሚሞክሩ፥ እውነተኝነትንና ሚዛናዊነትን፥ ፍትሐዊነትንና ሰብአዊነትን ከፖለቲካ ጤንነት መሥፈሪያነት በማስወጣት በፋሽስታዊ የደምና አጥንት ቆጠራና ጥራጥ ፋኖነትን ሊበክሉት የሚታገሉ ቡድኖች መታየታቸው --- ናቸው።
እነዚህን መግፍኤዎችና ሌሎች ለፋኖነት ባእድ የሆኑና ህልውናን ከማረጋገጥ ፋኖነት እና ለህልውና ዘለቄታዊ ዋስትናን የሚሰጥ አውድ ከመፍጠር ዓላማ ጋር ፊት ለፊት የሚጣረሱ ምልክቶችን በግልጽ መመልከቴ ለጽሑፉ መነሻ ሆኗል።
የጽሑፉ ዓላማ
ነባርነትን የማያገልል፣ በባእዳን ምክርና እርዳታ የማይመራ፣ ፋኖነትን ከነባር እሴቶቹና ከተፈለገበት ዋና ዓላማው የማያንሸራትት፣ ለህልውና አደጋ መንስኤ የሆኑ አስተሳሰቦች፣ ባእድ ርዮቶችና ፈጻሚ መዋቅራት ዳግም እንዲያንሠራሩና ቀጣይ የህልውና አጀንዳ በማይሆኑበት ደረጃ የሚያወያይ ከፍ ያለ ውይይት በፋኖ አደረጃጀቶች፣ በደጋፊዎችና በቅን ልሂቃን መካከል እንዲንሸራሸር ውይይት መለኮስ፤ ----
አሁን አየሩን የሞላው ግልብ፣ ጠባብ፣ ቡድናዊና ከፋኖነት ዓላማ ያነሰ ሐሳብ ከአጀንዳነት ወርዶ በፋኖነት ልክ ከፍ ያለ፣ አሰባሳቢና አስተባባሪ አጀንዳ እንዲናኝ አስተዋጽዖ ማድረግ ነው።
ፋኖነትና ታሪካዊ ዳራው ምን ይመስላል?
ፋኖ አባቶቻችን እንደሚነግሩን ለፍትሕ፣ ለእውነት፣ ለክብረ-ሰብእ፣ ለክብረ-ሀገር፣ ለሕዝብ-ነጻነትና ሙሉ ክብር ራሳቸውን አሳልፈው ለመስጠት አዝማችና አዛዥ ሳይጠብቁ፣ ሥልጣንና ምንዳ ከማንም ሳይጠብቁ ግባቸውን ስንቅ አድርገው የሚፋንኑ የሀገር ልጆች ባህል ነው። ይህ በእግዚአብሔር የተወደደ በቅዱስ ዳዊት ሕይወት ምሳሌነት የሚተርጎም ነው። ወጣቱ ለንግሥና የተቀባው የእስራኤል እጩ ንጉሥ፣ ሥልጣን ላይ በተቀመጠው ንጉሥ ሳዖል ማሳደድ ሲደርስበት ከፋነነ በኋላ በዱር ሸንተረሩ ራሱንና ተከታዮቹን ሲከላከል ያነሳቸው እሴቶች፦ ፈሪሃ እግዚአብሔር፣ ፍትሕ፣ ሰብአዊነትና ምሕረትን ታጥቆ ተገለጠ። ጠላቱ ንጉሥ እጁ ላይ ወድቆ ሲገኝ አማካሪዎች እንዲሰይፈው ሲመክሩት “እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን አላነሳም” በሚል፣ ሕገ እግዚአብሔር አክባሪነቱን ሲያመለክት በአንጻሩ ጠላቱ እንዲጸጸት በሚያደርግ መልእክት ልቡን ሲከፍለው ታይቷል። ፋኖነት ይህን የቅዱስ ዳዊት ዕሤቶች ከጀግንነት ጋር አዋሕዶ የሚይዝ ነው።
ፋኖነት “ውርደት፣ የግፍ አገዛዝ፣ የርስት መንጠቅ፣ ከፍተኛ ክብር የተሰጣቸው የሃይማኖትና ባህል፣ የሕዝባዊ እና አገር ክብሮች መደፈር ይበቃል!!” ብለው ሕሊናቸውናን እምነታቸውን አማክረው ለእግዚአብሔርና ለሕሊና የሚጀምሩት ለመስዋእትነት መፋነን ነው።
በአገራችን ኢትዮጵያም፣ የፋኖ ታሪክ በተከበረ አገርና ነጻነት፣ ክብርና ፍትሕን ምሰሶ አድርጎ ሺ ዘመናትን የተሻገረ ከዘመናዊ መንግሥት-ቅልብ ዘመናዊ ወታድር ቀድሞ በነጻነት ያኖረን ነው። ለምሳሌ ያክል በዘመነ መሳፍንት አፄ ቴዎድሮስ፣ በጣሊያን ወረራ አነ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ፣ እነ አበበ አረጋይና ኁልቈ መሳፍርት የሌላቸው የኢትዮጵያ ልጆች ነው። መንፈሱ ወደ ካህናትና መነኮሳት አባቶች ተሻግሮ፣ በካቶሊካውያን ተጭበርብሮ ከካደው አጼ ሱስንዮስ ጋር የተዋጉት መነኮሳትና የዘመኑ ጳጳስ፣ ከሮማ ካቶሊክ ጉዳይ አስፈጻሚው የጣሊያን ወራሪ ዘረኛ ጣሊያን ፊት የቆሙት አቡነ ጴጥሮስ እና አቡነ ሚካኤል የጎሬው ያንኑ ነባር እሴቶች ይዘው ለመስዋእትነት ቀርበው ለትውልድ መከፈል የሚገባውን የነጻነት ዋጋ በባህላችንና በነጽሮተ ዓለሞቻችን ውስጥ በደም ቀለም የጻፉልን ናቸው።
ይህ የፋኖነት መገለጫ መልካም ሰብእና ያላቸው የሰው ልጆች ሁሉ የሚደግፉት ስለነበር ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ጥቁር አሜሪካውያንና ላቲኖችን ሳይቀር ወደ ኢትዮጵያ ያጎረፈ፤ የጃፓን ንጉሣውያን ቤተሰቦችን ከኢትዮጵያውያን ጋር ከመተባበር በጋብቻ እስከ መጣመር የጋበዘ፤ የዓለም ካቶሊክ ክርስትና ተከታዮች ካርዲናሎችና የፕሮቴስታንት ፓስተሮች ሳይቀሩ ተባብረው ታንክ ባርከው በኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ላይ እልቂት እንዲፈጸም ቃለ ቡራኬ የሰጡትን የወቅቱን የቫቲካን ፖፕና የሞሶሎኒ የወረራ ፖሊሲ የሚሰብኩትን ካህናት በማውገዝ የፋኖነት ብርሃን ከሩቅ የጠራቸው ናቸው።
ታዲያ ይህ ልዩ ክብር የሚገባው፣ “ፋኖ” በሚል በሁለት ፊደል በሚጠራ “ስም” መገለጥ የሚችለው ስሙን ስለተጠሩበት ሳይሆን የስሙን መነሻና በታሪክ የተገለጠበትን እሴቶች አሟልቶ በተግባር ሲገለጥ ነው።
ፋኖን መደገፍ ከአማራ ሕዝብ ጋር ሳይቀር መዝለቅ የሚችለው ነባር እሴቶቹ ማለትም ክብረ-ሰብእን፣ ፍቅረ-አገርን፣ እውነተኝነትን፣ ፍትሐዊነትን፣ ጀግንነትን፣ ታሪክና ሃይማኖት አክባሪነትን፣ ከሁሉ በላይ ፈሪሃ እግዚአብሔርን መሠረት አድርጎ ሲገኝ ብቻና ብቻ ነው። ፋኖነት ከእነዚህ ዕሤቶች ሲጎድል፣ አዲስ በብልጣብልጦችና አምላክ-የለሾች ርዕዮት ባላቸው መሪና ምሁር ነን በሚሉ በባዕዳን አእምሮ በሚያስቡ ሰዎችና ቡድኖች ሲተረጎምና ሲመራ የአማራነት ህልውና ማጥፊያ የሆነ ቆልማማ ቀስት ከመሆን አያመልጥም።
ፋኖነት በቅድስናው የሚቀጥለው፣ ውጤቱም ለሰው ልጆች ሁሉ ጠቃሚ የሚሆነው በነባር የአብነቶቻችን እሴቶች ላይ ተጣብቆ በባዕድ-ተከል ጸረ-ኢትዮጵያ አስተምህሮ ሳይበከል ብቻ መሆኑ መታወቅ አለበት። በፋኖ ውስጥ እና በውጭ ደጋፊነት የሚገኙ ወገኖቻችን ለጊዜያዊ እና ጠባብ ግቦች ቅድሚያ በመስጠት ፖለቲካ-ሠራሽ ፋኖነትን ለማስተዋወቅ አማራነትን ወደ ፋሽስታዊ ብሔርተኝነት ለመድፈቅ የሚሞክሩ አዲስ የሚቀምሩት ቁማር፣ ሤራ፣ ፖለቲካዊ አስተሳስብ፣ አሠራር፣ ስልት፣ አደረጃጀት፣ ጎጠኝነት እና ከአማራና ኢትዮጵያ ህልውና ጠላቶች የሚዋሱት “ፋኖነት” የአማራና የነባር ኢትዮጵያ ፋኖነትን አይገልጸውም። ጠቃሚ እና ዘለቈታዊ ውጤትም አያስገኙም።
አንዳንድ ሰዎች በእርግጥ ነባር እሴቶችንና ምንጭ የሆኑትን እምነቶች፣ ባህሎች፣ ማኅበራዊ መሠረቶችና ረዥም ታሪክ “ያፈጀ፣ ያረጀ” በሚል ያላዋቂነት ወይንም የጠላት የውስጥ ሠራተኝነት እየሠሩ “ፋኖ ነኝ”፣ የፋኖ መሪና የርዕዮት ምንጭ ነኝ፣ የሚሉ የአማራ ፋኖነትና የፋኖ ደጋፊነት ክብር አይገባቸውም። ከትግሉም መወገድ አለባቸው።
የፋኖ ስሙ የሚከብረው በፋኖነት እሴቶችና በግብሩ፣ በግቡና በአፈጻጸሙ ሲገለጽ እንጂ ዘመናዊ የብዝኃ መገናኛ ዘመቻ በማድረግ ፋኖነትን ከእሴቶቹ፣ ከፋነነበት ዓላማዎቹ በበለጠ ደረጃ ግለሰቦችንና ቡድኖችን በማሰበክ አይደለም። ፋኖነት የሚታወቀው በፋኖ እሴቶች ሲታነጽና በእሴቶቹ ሲፀና እንጂ በገንዘብ ኃይል፣ በኔትዎርክ እና በገንዘብ ኃይል በሚፈጠር ስምና የጭፍን መንጋ ግፊት አይደለም።
ፋኖነት ፈሪሃ እግዚአብሔር፣ ክብረ-ሰብእ፣ እውነት፣ ፍትሕ፣ ነፃነት፣ ፍቅረ-አገር (ሰውን፣ ርስቱን፣ የተቀደሰ፣ ታሪኩን፣ መኗሪያ ሀገሩን፣ ትውልዳዊ ትሥሥርና ሁለንተናዊ ቅብብሎሽን)፣ አንድነት፣ ትህትና፣ መከባበር፣ መተማመን፣ ግልፀኝነት፣ በዕውቀትና በጠራ ግብ መፅናት እና መስዋእትነትን ሁሉ ይጨምራል፡፡
ፋኖነት በተውሶ ርዕዮትና በራስ ወዳዶች (ናርሲሲስቶች) ሲበከል እና ተዋርዶ ተራ ስብስብ ሲሆን የፋኖነት ተቃራኒ የሆኑ ግብሮችና አስተሳሰቦችን የሚያንጸባርቅ ከተገኘበት ማኅበረሰብእ እምነቶች፣ ባህሎች፣ እሴቶች፣ ማኅበራዊ ሥሪቶች እና ዋና የህልውና መረጋገጥ ጋር በመጋጨት፣ በአምላክ-የለሽነት፣ ከፋፋይነት፣ ሤረኝነት፣ ቁማርተኝነት፣ አሉታዊ አግላይ መንደርተኝነት፣ በዘራፊነት፣ በኢሰብአዊነትና ኢፍትሐዊነት፣ ታሪክና ሃይማኖት የለሽነት፣ ሌሎችን እየሰዉ ጠባብ የግል ፍትወት በማርካት ክህደት፣ በማንአኽሎኝነት፣ በባንዳነት፣ በተንሸራታችነትና አጭበርባሪነት ይገለጻል፡፡ እንዲህ ሆኖ የተገኘ ስብስብ “ፋኖ” የሚለውን ስም በአስችኳይ ለአማራ ሕዝብ ወይንም የአማራነት እሴቶችን ለሚጋሩ እና ለዚህ እሴት ለሚዋደቁ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች ማስረከብ ይገባዋል። እነዚህ አዳዲስ ጸረ-ነባር ስብስቦችና ልሂቃን ነን ባዮች ለራሳቸው አዲስ ስያሜ በመፈለግ አማራነትንና ፋኖነትን ለቀቅ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
የህልውና አደጋ የተጋረጠባቸው ክፍለ-ሕዝቦች የሚሹት እውነተኛ ፋኖነት እና ጠባብ ልዩ ፍላጎቶችን ለማሳካት መሣሪያ ሆኖ የሚፈጠር ‘ፋኖነት’ ይለያያሉ
በመጀመሪያ ደረጃ የክፍለ-ሕዝቦች ፍላጎቶችና ሕዝቦችን በራሳቸው ብያኔ እንወክለዋለን የሚሉ ነገር ግን ከመስዋእትነት ዋጋ የራቁ ወገኖች ፍላጎት ይለያያል። በሕዝቡ ስም መሥራት ጥቅሙ የሕዝቡ ልጆችና ወዳጆች ለሕዝባቸው ሀብታቸውን፣ ዕቀታቸውን፣ ውድ አንዲት ነፍሳቸውን ስለሚያዋጡ ጮሌዎችና ለጠላት የሚያገለግሉ ቡድኖች ይህን ሁሉ ስጦታ ለራሳቸው ግብ እንዲጠቀሙበት እድል ይሰጣቸዋል።
የአንድ ክፍለ-ሕዝብ ፍላጎቶች ምንድን ናቸው?
ፍላጎቶች ሁሉ በሕዝብ ስም ፖለቲከኞች ስላቀረቡት ትክክል ሊሆኑ አይችሉም። ፍላጎቶች በድምጽ ብልጫና በቁማርተኝነት ውጤት ስላገኙ ተቀባይነትንም ሆነ ዘለቄታዊነትን ማረጋገጥ አይችሉም። አግባብነት ያላቸውና የሌላቸው የተለመዱ ፍላጎቶች መነሻቸው ይለያያል። ትክክለኛና ክብር የሚገባው፣ በሕግ የሚደገፍ፣ ካልሆነ የሚለወጥ ፍላጎት የመሥፈርቱ መነሻ “ክብር-ሰብእ” ነው። በክብረ-ሰብእ መሠረትነት የሌሎች ፍላጎቶች ፍትሐዊነት፣ ዘለቄታዊ ሁለገብ ጠቀሜታዎችና የህልውና ዋስትና ይበየናል። ክብረ-ሰብእን፣ ፍትሕን፣ እኩልነትን የማይቀበሉ፣ ቡድናዊ ጥቅምችን ማእከል ያደረጉ ፍላጎቶች ለሌሎችና ለራሳቸው የህልውና አደጋ ምንጭ ናቸው። አግባብነት ያላቸውና የሌላቸውን ፍላጎቶች እንደሚከተለው እንመልከታቸው፦
የፍላጎት ዘርፎች ትክክለኛ ትክክለኛ ያልሆኑ ፍላጎቶች
አካላዊ ህልውናን ማረጋገጥ ⇒ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ፣ ያለ ምንም ትርክት መነሻ፣ ያለ አንዳች የንዑስ-ማንነት መሥፈሪያ፦ አንድ ሰው፣ ቤተ-ስብእ፣ ማኅበረ-ስብእ በዚህ ምድር በዓለም፣ በአገሩ፣ በመንደሩ ለመኖር የሚያስፈልጉትን፦
o የተፈጥሮ ሀብትና ውጤቶቻቸውን፤
o ምግብ፣ መድኃኒት፣ መጠለያ፣ ልብስ፤
o ማኅበራዊ መስተጋብርና አጥር፤
o መንግሥታዊ ሁለንተናዊ አገልግሎትና ጥበቃ፤
o ከቦታ ቦታ መዘዋወር፣ መሥራት፣ መዛመድ፤
o የመንፈሳዊና ባህላዊ አገልግሎት መስጠትና መቀበል
o ከአደጋ ራሱን፣ ቤተሰቦቹን፣ ማኅበረሰቡን የሚጠብቅበት አቅምና ክሂሎት
የማግኘት መብቶቹን ለማረጋገጥ ሁለንተናዊ ከጥገኝነት የተላቀቀ አቅም ባለቤት መሆን።
⇒ የህልውና አደጋን በማስወገድ አካላዊ ህልውናን ለማረጋገጥ የሌሎች ክፍለ-ሕዝቦችን አግባብነት ያላቸው ፍላጎቶች በምንም መልኩ የማይጋፋ ፍላጎትን የማሳካት ፍኖት ላይ የሚሄድ ተጋድሎ፤ ⇒ እኛና እነርሱ በሚል ፍረጃ የሽሚያና የቅሚያ ማኅቀፈ-ዕሳቤን መሠረት በማድረግ፣ የሰው ልጆችን እኩልነትና ክብር ዝቅ በማድረግና ፍትሕን በማዛባት፣ በሐሰተኝነትና በቁማርተኝነት ርዕዮት የሚመራ ፍላጎትን የማስከበር -- ልማድና ሙከራ ለሞካሪውም ሆነ ለሚሞከርበት ወገን መጨረሻው ጥፋት ስለሚሆን አግባብነት የለውም፤
⇒ “የእገሌ ሕዝብ ልዩ ጥቅም፣ ልዩ ጥያቄ፣ ልዩ ፍላጎት፣ ልዩ ግብና መዳረሻ” በሚል መነሻ ልሂቃን ፈጥረው በመናኘት የሚጀምሩትና የሚያካሄዱት ፖለቲካዊና ትጥቃዊ ትግል ሁሉ አግባብነት የሌለው የሚያደርገው፦
o የሰው ጠላት በማበጀት ያጠቃል
o የሃይማኖትና የባህል፣ የታሪክና የትርክት ጠላት በማበጀት ተተኪ አጥፊ በመትከል የህልውና አደጋ ያስከትላል።
o የህልውና አደጋን ለማስወገድ “ሌሎች” ተብለው የሚፈረጁትን ዘር ማጥፋት፣ ታሪክ መደለዝ፣ ሐሰት መፈብረክ፣ ማንነት ማስቀየር፤
መንፈሳዊና ባህላዊ ህልውና ⇒ በምንም ዓይነት ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ትርክታዊ ስልት ሳይደገፍ በፍቅር የሚመራ ሃይማኖትን በማስተማርና በተግባራዊ አርዓያነት ማስፋፋት
⇒ በቦታና በጊዜ ጫና ውስጥ ሳይገደብ በእምነቱ አስተምህሮ መሠረት፣ ምንም ፖለቲካዊና ተደራቢ ግብ ለማሳካት አጀንዳ ሳይቀይጥ አምልኮን በነጻነት መፈጸም
⇒ ብዝኃ እምነትና ባህል በትምህርትና በአርዓያነት የሚቃኑ እና የሚመጋገቡ ሆነው መሠረታዊ የሆኑ ልዩነቶች በየልዩ ቦታዎቻቸውና መዋቅራቶቻቸው ከመንግሥት መዋቅርና ሥርዓት ውጭ ተከብረው ያገልግላሉ፤ ⇒ የሌላውን እምነት አኮስሶና አጠልሽቶ ማስተማር
⇒ የሌላውን እምነት ተከታዮች በአግላይነትና አድልዎ ማዳከም፣ ዘመኑ ሲፈቅድ አካላዊ ጥቃትና ማጥፋት መፈጸም
⇒ ቀዳማዊ አሻራዎች፣ ልማዶች፣ ባህሎችና ጥበቦችን ሁሉ እኔን እስካልመሰሉ ድረስ እንደ ጭቆና ይቆጣራሉ ብሎ ፖለቲካዊ መፍትሔ ይሰጠኝ የሚል መንግሥታዊ እና ድንበር ዘለል ዲፕሎማሲያዊ ጫና መሻት
⇒ ታሪክና ትርክት ተገልብጦና ተደምስሶ እኔን ብቻ ያንጸባርቅ ማለት፤
ግላዊና ማኅበራዊ ነጻነት ⇒ ሰው በግሉ ማኅበራዊ፣ ሃይማኖታዊና መንግሥታዊ አውዱ ለዜጎች የሚፈቅደውን ሁሉ መሠረታዊ የየተቋማቱን ወሳኝ የመኖራቸው ምልክት የሆነውን ምክንያት አክብረው መሳተፍ፣ መጠቀም፣ ዘመኑን እንዲዋጁ ሐሳብ ማቅረብና አርዓያነት ያላቸው ምሳሌዎችን ማቅረብ ሙሉ ነጻነት ዋስትና ማግኘት
⇒ በተፈጥሮ የተሰጠው የግል ሰብአዊ ነጻ ፈቃድን በውጫዊ ኃይል በተቀላቀለ ማዕቀብ የማይነጠቅ፣ ዕሳቤዎቹ በቅርብና ሩቅ ፖለቲካዊ ዕቀባ የማይታሠር ሁኔታን ለመፍጠር የሌሎችን ሰብአዊ ክብርና ነጻነት ሳይጋፋ፣ ሰላምና ማኅበረሰባዊ መስተጋብርንና መተማመንን ሳይንድ መፈለግና ማግኘት የሚችልበት አውድ ዋስትና እንዲያገኝ ለማድረግ የሚታገል
⇒ ነጻነትን ከልቅነት፣ መብትን ከመብለጥ፣ ክብርን ከማዋረድ፣ ልህቀትን ከማሳነስ፣ አገርን ከግዴታና ጠቀሜታ ሳይለይ ለወንጀለኝነትና ኃጢአተኝነት ጎሬነት ማቆራኘት የተገባ እንዳልሆነ አውቆ የአሁኑና የነገውን ትውልድ ጥቅም በሚያሰፋና በሚያዘልቅ መሥፈርት ጥቅሞቹ እንዲሳኩ የሚሠራ ⇒ ኃላፊነትና ፍትሐዊነትን፣ ሰብአዊነትን የማያገናዝብ ግላዊ “የእኔ” እና የቡድን “የእኛ” አድሎአዊ ጥያቄ
⇒ የግል ነጻ ፈቃዱን ሌሎችን በሚጎዳ መንገድ መጠቀም እና/ወይንም ለቡድን ልዩ ጥቅም ሌሎች ግለሰቦችና ቡድኖችን አደጋ ላይ ጥሎም ቢሆን መጠቀም ይገባኛ የሚል እይታና ድርጊት
⇒ ነጻነትን ከመለያየትና ኃላፊነትን ከመሸሽ የሚያምታታ፤ መብትን የሌሎችን ህልውና አደጋ ላይ በሚጥል ርዕዮትና ስልት ለመምራት መፈለግ
⇒ መከበርና በሌሎች መዋረድ፣ መበልጸግን በሌሎች ማጣትና መነጠቅ፣ ሕጋዊነትን ከሰብአዊነትና ርትዕ ነጥሎ የቡድን መገልገያ የማድረግ ፍላጎት
⇒ አገርን ለአንዱ ዜጋ ለሌላው ንፉግ እንጀራ እናት አድርጎ መረዳት
⇒ በቀልን ያለ ቦታው፣ ያለ ባለቤቱ በሐሰትና በኢፍትሐዊ መንገድ የፖለቲካ መሣሪያ በማድረግ በጎሣና በቋንቋ ዘውግ ስለ ትናንቱ በዛሬው ትውልድ ላይ ያለ ሕጋዊ ግልጽ ሂደት ቅጣት መበየን
አገራዊና ሕዝባዊ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትና ነጻነት ⇒ አድልዎና ኢፍትሐዊነት ወንጀል የሚሆኑበት እና የዜጎች እኩልነት ዋስትና የሚያገኝበት፦ ትርክታዊ አስተምህሮ፣ ማኅበራዊ መርሖዎችና መዋቅራት፣ ፖለቲካዊ ርዕዮትና ሕጋዊ ሥርዓት፣ ፍትሐዊ ሁለገብ አቅም ማፍሪያ እኩል ዕድሎች የተረጋገጠበት ዳር ድንበሯ የተከበረባት አገር ሙሉና እኩል ባለቤት መሆን፤
⇒ አገርና ሕዝብ የተፈጥሮ ሀብትን ያለ ውጭ አገራት ጣልቃ-ገብነትና ተጽእኖ፣ የቴክኖሎጂና የሙያ ጥገኝነት፣ የገበያና የፖሊሲ ጫና ለዜጎች ጥቅምና ለትውልድ ራስን መቻል የማዋል ሙሉ አቅም
⇒ ሕዝብ በንዑስ-ማንነት ተመጋጋቢ ቁርኝት ወደ ላቀ ተዋሕዶና መተማመን ደርሶ ልዕልና ያለው አገራዊ ማንነት እንዲያዳብር እና ውስጥ ያሉ ብዘኃነቶች መወዳደሪያን መፋተጊያ ሳይሆኑ እንደ አንድ አካል ብልቶች እየተመጋገቡ የጋራ ህልውናቸውን የሚጠብቁበትን አውድ መፈለግ ⇒ ታሪካዊ፣ ትርክታዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ንዑስ-ማንነትን ከሰው ክብር፣ ከአገር አንድነት እና ዜጎች ውሕደት በማቃረን መለያየትንና ግጭትን እንደ ነጻነትና ዝማኔ የማስቆጠር ጥያቄ
⇒ አገርና ሕዝብን ከአገራዊ የፖለቲካ ርዕዮትና አውድ በማስወገድ የግልና የቡድን የፖለቲካ ሉዓላዊነትን እንዲውጠው መጠየቅ፣
⇒ የጋራ ታሪክን ማኮሰስና በንዑስ ማንነት መነጽር በመንደር መሸንሸን፣ በሐስት ትርክት መበከል፣ ከጋራ ታላቅነት ወደ ቡድን ልህቀት ፍለጋ መውረድን መብት ብሎ ማቅረብ
ቀጠናዊና ዓለም ዐቀፋዊ ግንኙነት ⇒ ቀጠናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶች ለጋራ የሁለት ወገን የብዙኃን እኩል ተጠቃሚነት ዋስትና በሚሰጥ የግንኙነት መርሖዎችና ውሎች የሕዝቡን ክቡር እሴት፣ እምነት፣ ባህል እና ትውልዳዊ ጥቅምን ለድርድር የማያቀርብ ሥርዓት
⇒ ለሕዝቡና ለአገሩ ደኅንነት፣ ከሁለገብ ጥግኝነት (የግብርና፣ ቴክኖሎጂ፣ መገናኛ፣ መከላከያ፣ ይለማት ግብዓት፣ የጤን እና የምግብ ሉዓላዊነት) ነጻ በሚያደርግ ተመጋጋቢ ግንኙነትን መመሥረት
⇒ በአባይ ውሃ፣ ከሜድትራንያን፣ ቀይ ባህርና ህንድ ውቂያኖስ ክበብ፣ በጂኦ ፖለቲካ ቁርኝት ባለን ምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የቤተስባዊ ስህነ ምህዳር ልዩ የትብብርና የሀብት የጋራ ተጠቃሚነት የሚያቆም ዲፕሎማሲን ማስለመድ ⇒ ኢትዮጵያን አፍርሶ፣ የተውሶን ቡድን አንግሦ ምሥራቅ አፍሪቃን የመጠቅለል ቅዠታዊ የዘር ስሌትን አርግዞ፣ ኩሽ እና ሴም፣ ደቡብና ሰሜን ብሎ ከፍሎ እንኳንስ የውጭውን የአገር ውስጡን ማኅበረስብ በብሔርና ክልል ከፋፍሎ ለትናንሽ አገራት መፈጠር ሕገ መንግሥት ጽፎ --- እርሱን ለማስከበር ሕዝብ ላይ የሚዘምት መንግሥትን የሚደግፉ ቡድኖች --- ፍላጎት አግባብ አይደልም፤
⇒ ዜጎችንና መጪውን ትውልድ አገር/ርስት፣ ዋስትናና ነጻነት የሚያሳጣ ጉድኝት የሚፈጥር፣ ሕዝብ አፍርሶ የቱሪስትና የውጭ ዘራፊዎችን በኢንቨስትመንት ስም የሚጋብዝን ሥርዓት በመንግሥትነት የመቀበል ፍላጎት ኢሰብአዊና አጥፊ ፍላጎት ነው፡፡
የአማራ ሕዝብ ተጋድሎ ጫፍ ፋኖ እውነተኛ ፋኖነትን ለማንጸባረቅ የግድ አግባብነት ያላቸውን ፍላጎቶች ለማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን አግባብነት የሌላቸውን ፍላጎቶች የማሸነፍ አቋምና ግዴታን መሸከም ይኖርበታል። ትክክለኛ ፋኖ አድሎአዊ፣ ቁማርተኛ፣ ግለሰብና ቡድን አንጋሽ መሆን አይችልም። የፋኖ ትግል ንጉሡ ዓላማውንና ግቡን አሳክቶ አግባብነት ያላቸውን የአማራና የሌሎች ማኅበረሰቦችን ፍላጎቶች በማይቀለበስ ሥርዓት ላይ ማቆም ነው።
ለዚህ ለትግል ውጤታማነት የሚጠቅም የማለባበስ በሽታን አስታቅፎ የሚያንፏቅቅ ንግግርና ፕሮፓጋንዳ አየሩን እንዲበክል ፈጽሞ ዕድል መስጠት አይገባም።
በብልጠት፣ በቁማርተኝነት፣ በግለሰብና ቡድን ጠባብ ዕይታና ፍላጎት አንጻር ፕሮፓጋንዳ መሥራት፣ ትግል ማደነቃቀፍ፣ በገንዘብ ደጋፊ መግዛት፣ ከባዕዳን ጋር በጀርባ መዋዋል በጎሣ ፖለቲካ ከመጣው አጥፊ ማዕበል ታድጎ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከሚናፍቀው ከእረፍት ወደብ አያደርስም። ካደረሰም አያዘልቅም። ከዘለቀም ቀጣይ መጠፋፋትን ይተክላል እንጂ በፍትሕ፣ በእውነት፣ በክብረ-ሰብእ፣ በፍቅርና መተማመን ላይ የተመሠረተ የአንድ ቤተ ሰብእ የሚያኖር ሰላምን ማንበርና ዋስትና መስጠት አያስችልም።
የህልውና አደጋን ለመቀልበስ የአደጋው መንስኤ የሆኑ አካላትን ብሔርተኝነትና እንግዳ የባዕድ ርዕዮት መዋስ ያዋጣል?
ከ፲፱፻፵፪ ወዲህ በኢየሱሳውያን ሤራና በኢትዮጵያዊነት ጠላቶች ተቀርጾ በቀረበ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ያደጉት በአካለ ሥጋቸው ኢትዮጵያዊ በአእምሮአቸውና በልባቸው ምእራባዊ ሆነው የተገኙቱ ምሁራን፣ የጣልያን ወራሪ ጦር ባንዳ ቤተሰቦች ያሳደጓቸው፣ በጊንቢ ሆስፒታል የናዚ ጀርመን የዘረኝነትና የጸረ-ሴማዊነት ክርስትና ወልዶ በየጸሎት ቤቱ ያሳደጋቸው በጥምረት በማርክሲስት ርእዮተ ዓለም ግልብ ንባብ የተፈጠሩት ወጣቶች እና “ኢትዮጵያ የብሔረሰቦች እሥር ቤት ናት፤ የብሔር ጭቆና አለ፣ ጨቋኙ አማራ ነው፣ የጭቆና ፊት መሪና ተጋሪ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት” በሉ ተብለው ትልም የተሰጣቸው አገር አፍራሽና ገንጣይ ነጻ አውጭዎች ተብዬዎች ---- በአገር አእምሮ ማሰብን ፈጽመው የማያውቁ የጠላት አጀንዳ አስፈጻሚ ማኅደሮች መሆናቸውን በመረዳት ---- የአማራነት፣ የኢትዮጵያዊነት፣ የኦርቶዶክሳዊነት፣ የነባር እምነቶችና ባህሎች ውጤት የሆኑ የአስተዳደርና ፍትሕ ሥርዓት እውቀቶች፣ ማኅበራዊ መዋቅራት፣ ነባር የሥነ-መንግሥት ዕሳቤዎች ሁሉ ተጻራሪዎች ናቸው። ስለዚህ ፋኖነትንም ወደዚሁ ባዕዳዊ ዕሳቤያቸው ሊያወርዱት የሚታገሉ ወጣቶችን ማማከራቸውና መደገፋቸው አያስደንቅም።
አማራን ከአማራነት እሴቶቹ በሚቃረነው በጠላቶቹ ነጽሮተ ዓለም እና የፖለቲካ-ሠራሽ ማንነት ለመተካት አማራን ለህልውና አደጋ ከዳረጉት አካላት አስተሳሰብ በመዋስና ስልታቸውን በመከተል አማራን ከአጥፊዎቹ ለመታደግ የሚመኝ ቡድን ፈጽሞ ከአማራነትና ከታሪካዊ “ፋኖነት” ጋር እጅግ የተለያየ አስተሳሰብ ነው። ፋኖነት ተውሶ፣ ቁማር፣ ወደ ዶግማነት ያደገ አግላይ ጎጠኝነት፣ ሤራ፣ ወገንን በሐሰት ፕሮፓጋንዳና በገንዘብ ኃይል፣ ሌላውን በመግደል፣ ታሪክና እምነትን በመካድ፣ ከባእዳን ተዋውሎ የሕዝቡን መስዋእትነት የሚከፈልለት ግብ በግለሰቦችና ቡድኖች ፍላጎት ማርኪያ አንጻር ቀርጸው የሚተክሉት ባዕድ ርዕዮት አይደለም። ፋኖነት በሰብአዊነት፣ ፍትሕ፣ እውነት፣ ግልጸኝነት፣ ነባርነት፣ መተማመን፣ ቃል ኪዳን አክባሪነት፣ መስዋእትነት ምሰሶዎች ላይ የሚቆም የሕዝብ እሴት ነው።
አማራ በእውነት ከህልውና አደጋ ለመዳን የሚያደርገውን ተጋድሎና መስዋእትነት ውጤታማ ለማድረግ ከፈለገ እንዲህ ይበል፦ “እኔን አማራውን የሚያጠፋኝን አካል አጥፊ አድርጎ ያቆመው የእኔ የአማራነት እሴቶቼ መጠላት ነው። ዒላማ የመደረጌ ምክንያትም ይኼው ከደሜና አጥንቴ ልዩነት ሳይሆን ከሰብአዊነት፣ ከባለታሪክነት፣ ከአትንኩኝ ባይነት፣ ከአገር አፍቃሪነት፣ ከእግዚአብሔር ሕዝብነት የተገኘ ማንነቴ እንደሆነ አውቃለሁ፤ ‘ይኽን እያወቅሁ ራሴን ለማዳን አጥፊዎቼን መምሰል የግድ ነው፡፡’ ብዬ ልነሳ ብሞክር የአጥፍቶ መጥፋት መርሕን እንጂ የአማራነትን የአሸናፊነት ምሥጢር ምሰሶዎች፦ የፍትሕ፣ የእውነት፣ የሰብአዊነት፣ የታሪካዊነት፣ የሕዝበ-እግዚአብሔርነትን ነቅዬ በተሸናፊዎቹ ጠላቶቼ ልክ ራሴን ማሳነስ እንደሚሆንብኝ አውቃለሁ። ይህንን ዕውቀቴን፣ እውነቴን፣ የህልውና ዋስትና ማረጋገጫ የኃይል ምንጬን ለማድረቅ አትሞክሩ። የምትሞክሩ ካላችሁ ወዳጅ መሳይ የውስጥና የውጭ ጠላቶቼ እንደሆናችሁ አውቃለሁ።”
ፋኖነትን ጠምዝዘው “የአማራ የህልውና አደጋ ምክንያት የሆኑ እንደ ሕወሓትና ኦነጋውያን ዓይነት ዘረኝነት ካላሰብኩ፣ ፋሽስታዊ ርዕዮት ካልጋትኩትና ጭፍን መንጋ አድርጌ ካልጋለብኩት፣ እና የአማራ ጠላቶች ነጻ እናውጣህ ብለው ነጻውን ክፍለ-ሕዝቦች የባርነት ሥነ-ልቦና ውስጥ በማስገባት፣ በስሜት ነጻነትን ባርነት፣ ባርነትን ነጻነት ብሎ እንዲያምንና በጭፍን መንጋነት የፖለቲካ ልሂቃን ሤራ ማስፈጸሚያ አድርገው ለመከራ እንደ ዳረጉት፣ አማራንም በጠላትነት እንዳስፈረጁት ዓይነት ስልት በመቅዳት አማራን ከነባር ማንነቱ፣ እምነቱ፣ ባህሉና ታሪኩ ነጥዬ ዕቃ ካላደረግሁ አላሸንፍም” የሚሉ ቡድኖች ሁለት ጊዜ ማሰብ ይጠበቅባቸዋል።
ጠላቶቻችንን ለማሸነፍ ጠላቶቻችንን እንምሰል ማለት አመክንዮአዊና አዋጭ ከሆነ ይህን የሚያምኑ ሰዎች ለምን ጦር ሜዳ ወረዱ? ለምን ሕዝቡን መስዋእትነት ያስክፍሉታል? ለምን አንደኛቸውን ወሥነው ታሪካቸውን፣ እምነታቸውን፣ አገራቸውን፣ ባህላቸውን፣ ሰብአዊ ክብራቸውን ሁሉ ሊመስሏቸው ከሚጓጉላቸው የሕወሓትና ኦነግ ተቋማት ጋር ተስማምተው አማራ አገር አልባ፣ እምነትና ታሪክ-የለሽ፣ ስደተኛ የአፍሪካ ጅብሲ እንዲሆን ፈቅደው ውይንም ሕወሓት ሁሉንም የትግራይ ክልል በሚለው ድንበር ውስጥ የሚኖሩ ንዑሳን-ማንነቶችን ሁሉ ጨፍልቆ ትግራዋይ፣ ኦነግ/ብልፅግና ኦሮምያ ውስጥና ዙሪያ የሚገኙትን ማንነቶች ሁሉ ጨፍልቆ የኦሮሙማ እምነትና ማንነት ልብስ ሊያለበሰው እንደሚጥረው ሁሉ አማራ ለሁለት ተከፍሎ እንደየቅርበቱ ከፊሉ የፖለቲካ-ሥር ትግራዋይ፣ ሌላው ደግሞ የፖለቲካ-ሥር ኦሮሞ በመሆን ራሱን አያከስምም? አማራ ነባር አማራነትን የህልውና ትግሉ አካል ለማድረግ በማይፈልጉ የፖለቲካና የትግሉ ልሂቃን አየር-ወለድ አዲስ ማንነት ዙሪያ ተሰልፎ መስዋእትነት መክፈሉ ሃይማኖቱን፣ ባህሉን፣ ታሪኩን፣ ኢትዮጵያ ርስቱን ሁሉ የሚተው ከሆን የሚዋጋው “አማራ” የሚባል ከሰው እሴትና ታሪክ፣ ሰብአዊ ክብርና ፍትሕ ጋር ቁርኝት የሌለው የማይጨበጥ መንፈስ ነው ወደሚል ድምዳሜ ያደርሳል። የተምታታ እና ትርጉም የሌለው ርዕዮትም ነው። ፋኖን እንምራ የሚል አንዳንድ ግለሰብ ሕዝቡን እየማገደና መከራውን እያራዘመ የሚያልመው የአማራ ዓይነት ምን እንደሆነ ወጥቶ በግልጽ፣ በተጻፈና በተሰነደ መንገድ ግልጽ ማድረግ ይጠበቅበታል። ከዚህ ውጭ ራሱን ከአጥፊዎች ለመታደግ የወጣውን ሕዝብ እየሰዉ ከዓላማው ውጭ ስለ ግለሰቦች አራት ኪሎ መንገሥ ብቻ እያወሱ ወይንም ወደማይታወቅ ግብና ሁኔታ ማድረስ ወንጀል ይሆናል። ይህ ግልጽ ያልሆነ በፕሮፓጋንዳ ላይ የተንጠለጠለ ሞቅታ ሌላ የከፋ የህልውና አደጋ የሚጋብዝና በእርጋታ ማሰብን፣ ምክክርን፣ ከግለኝነት መላቀቅን፣ በባዕዳን ምክርና ድጋፍ መዋዠቅን ማቆምን ይጠይቀናል።
የአማራ ልጆች የሚዋጉት፣ የሚሞቱትና የሚገድሉት “አማራ” ለሚባል “ሃይማኖት፣ ታሪክ፣ ትውፊት፣ ፍትሕ፣ ባህል፣ እሴት፣ ርስት፣ ሰብአዊ ክብር” ለማያስፈልገው ሆድና ሥጋን ብቻ ከሥልጣን ጋር ለሚያልም ግዕዛኑን ተነስቶ ለመሪዎቹ ባርያ ለሚሆን መንጋ ማንነት አልቦ ሕዝብ ለመፍጠር እንድልሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው። ጥያቄው፦ የአማራ “ህልውና” “አማራ” ለተባለ ስያሜ፣ ለአማርኛ ቋንቋ እና የየጎጡን ራስ-ነገሦች ለአራት ኪሎ ለማብቃት ብቻ ነው ወይስ ሙሉ ሰብአዊ ክብርን እስከነ ርስቱ፣ እምነቱ፣ ባህሉ፣ ትውፊቱና የረዥም ታሪኩ ትርክት ጭምር ነውን? ወይስ አማራን በባዕዳን ፍላጎት፣ በዘረኞች ሕገ መንግሥትና ላለፉት ብዙ አሥርት ዓመታት በመሬት ላይ በትውልድ አእምሮ በተቀረጹት ስሑት ርእዮቶችና ሐሰተኛ ትርክቶች አንጻር በተፈጠረ አደገኛ አውድ ውስጥ አማራን ከርክሞና አሳንሶ በተፈቀደለት ልክ ፖለቲካ-ሥር (politically modified) አዲስ ማንነት አልብሶ ማስቀመጥ? ይኽ ከሆነ መስዋዕትነት ሳይሆን የሚያስፈልገው፦
1) የብልጽግና መንግሥት ወንጀሎቹንና አገር የማፍረስ ፕሮጄክቱን ሕጋዊ የሚያደርግበትን ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ዕውቅና መስጠትና ብያኔውን መቀበል፤
2) ኦነግ/ብልጽግና እና ሕወሓት ከፈጣሪዎቻቸውና ከደጋፊዎቻቸው ጋር አማራን በማግለል የተፈራረሙትን ለታላቋ ኦሮምያና የትግራይ ሪፐብሊክ ምሥረታዎች ዝግጅት የመጀመሪያ እርምጃ ተደርጎ የተቀመጠውን የፕሪቶሪያ ስምምነት መቀበል፤
3) በምሥራቅ አፍሪካ ከሚያሰጋው የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ጽንፈኝነት ያሰጋናል፤ እና የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና በክርስቲያን ላይ የሚፈጸመውን የማጽዳትም ሆነ ትውልዱን ከእምነት የማስወጣት ሂደት ፈጽማችሁ እንዳላያችሁ በማለፍና “ትግላችን ከእምነት የነጻ ሴኩላር ነው በሉ” በተባላችሁት መሠረት መታዘዝ፤
4) የአብይ አህመድን ዘር አጥፊ ወንጀለኛ ሠራዊት ከክልሉ እንድናስወጣላችሁ እናንተም ሕወሓት ካሠመራቸው ድንበሮች ውጭ ያሉትን የአማራ እና የኦርቶዶክስ ማጽዳት ፕሮጄክት ይመለከተናል እንዳትሉ በተባላችሁት መሠረት በመስማማት ካልዓይ ብአዴን ሆናችሁ የጎሣውያን ፌዴሬሽን እንደ አዲስ በሽግግር መንግሥት ስም እንዲመሠረት መቀበል፤
----- የአማራን ኢትዮጵያዊነት መሠረዝ እና ክልላዊነት መቀበል፣ አማራነት እምነት፣ ባህል፣ እሴት፣ እውነትና ፍትሕ የማያስፈልገው የዘር ማጥፋት የ50 ዘመናት ትራፊና ለወደፊቱም የህልውና ዋስትናና ሀገር የማይኖረው በሚያደርግ ብያኔ የምትስማሙ ከሆነ እየተካሄደ ያለው “የህልውና ትግል” እንደ ስያሜው የአንድ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ክፍለ-ሕዝብ በክብር የመኖር ዋስትና ማረጋገጭ ሳይሆን የጥቂት ሰዎች የፖለቲካ ሥልጣን መቆናጠጫና የሃብትና ክብር ማግኛ መሣሪያ ብቻ ነው።
ይህ ካልሆነ እና የአማራ ማኅበረሰብ ሁለገብ መስዋእትነት ከንቱ እንዳይሆን የአማራን ህልውና እስከ ነባር አማራነቱ እና ዋስትና ሰጭ አውድን በምሥራቅ አፍሪቃ በሚፈጥር ርእይ፣ ግብ፣ ስልት፣ መርሕ፣ ሂደት፣ ግልጸኝነት ባለው አቋም የሚመራ ከግለሰቦችና ቡድኖች ያልተገለጹና ያልተነገሩ ፍላጎቶች ነጻ ማድረግ ያስፈልጋል።
የአማራ የህልውና ተጋድሎ ለሰብአዊነት፣ ለፍትሕ፣ ለእውነት፣ ለበዓለአገርነት፣ ለአንድ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ክፍለ-ሕዝብ ሁለገብ የህልውና መሠረቶች ማለትም የታሪክ፣ የሃይማኖት፣ የባህል፣ ማኅበራዊ ደኅንነት፣ የጎረቤትና የሩቅ አገራት ግንኙነት ጤንነት መረጋገጥ ይመለከታል። የአማራ ወጣትም በክቡር ሕይወቱ ተወራርዶ ዱር ቤቴ ያለው ለዚህ ታላቅ ግብ ከሆነ ታላቅ ክብር ይገባዋል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ስለ ትውልድ በክብር መቀጠል፣ ለዓለምም ለመትረፍ ሳይሆን ጥቂት ጠባብ ፍላጎት ይዘው ትልቁን ዓላማ ሽባ የማድረግ አካሄድ ላይ የተጠመዱ ጎጠኞችንና የውጭ ፍላጎት አገልጋዮችን ተከትሎ የሕዝብን መስዋእትነት ከንቱ ማድረግ “ፋኖነት” ተብሎ ክብር እና ድጋፍ የሚሰጠው ሳይሆን ትውልዱ ነቅቶ የሚዋጋው አዲስ የህልውና አደጋ ነው።
ትክክለኛው የታወቀው የኢትዮጵያዊ ነባር ፋኖነት ስለ ግል ነፍሱ መሸሽ ሲቀናው ማባረር እና እየተዋጉ የመሞት ተፈጥሮአዊ ልማድ ሳይሆን ከራስ በላይ ለትውልድ፣ ለእውነት፣ ለፍትሕ፣ ለሰብአዊ ክብር የሚሰጡት የሰማዕትነት ሕይወት ነው። ይህ ልዩ ክብር ይገባዋል። ይሁንና ይህን ክቡር እሴት ጠልፎ የጎጥ፣ የግል እና የቡድን ግብ ማሳኪያ ለማድረግ የሤራ መረብ መዘርጋት በእውነት በሰው ልጆች ህልውና ላይ እንደመቆመር ያለ ወንጀልና ኃጢአት ነው።
በስሙ ወጣቶች የሚሞቱለት አማራ ማነው?
በስሙ ወጣቶች የሚሞቱለት አማራ ማነው? የሚለውን ጥያቄ እንደሚገባና ተቀባይነት ያለው አማራን የመተርጎም ሞራላዊ፣ ታሪካዊ፣ አመክንዮአዊና ፖለቲካዊ መብትና ሥልጣን ያለው እገሌ ነው ብሎ ለመበየን ቡድንና ግለሰብን ከመጠቆም የሚቀድመው መሥፈርቱ ምንድነው የሚለው ነው። በዚህ መሠረት ለክርክር የማይቀርበው መሥፈርት ወቅታዊና ቡድናዊ ብያኔ የሚሻ አይደለም፡፡
የማያከራክረው ቀላሉ ትርጉም “አማራ” ጥፋት የታወጀበት የኢትዮጵያ ክፍለ-ሕዝብ ነው። ዝርዝሩን ለመተርጎም ለጥፋት እንዲመረጥ ያደረጉት፣ አማራነትን ለጥፋት የመረጡት ጠላቶቹ ደምና አጥንቱን መርምረው፣ ዘረ-መሉ (Gene) ልዩ ነው ብለው አይደለም። አማራን በጠላትነት ያስፈረጀው ማንነቱን የገነቡት እሴቶቹ፣ እምነቱ፣ ታሪኩ፣ አገር ወዳድነቱ እና የዓለምን ዘረኛ ቅኝ ገዥነትን የሚያበረታታ አስተምህሮ፣ እምነቶችና ባህሎችን ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ያስቻለ እርሱ አማራው፣ በስሙ የነበሩ ነገሥታትና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት ብለው ያመኑ የአድዋ ድል ቁስለኞች ናቸው።
በአትንኩኝ ባይነት ሥነ-ልቦናው፣ ዓለም አቀፍ የዘረኞችን ስሑት ነጽሮተ ዓለም የሻረና ለግፉአን ከላቲን አሜሪካ እስከ ጃፓንና ደቡብ አፍሪካ የነጻነት አብሪ ፋና የሆነ፣ ባሪያ አሳዳሪና ቅኝ ገዥዎችን ያሸበረ መንፈስ ያለው ሕዝብ ስለነበረም ነው። ይህ ሌሎች ኢትዮጵያዊ ጎሣዎችና ባህሎች የተባበሩበት የጋራ ኢትዮጵያዊ ልዩ መልክ ነው ብንልም ጠላት ግን ያተኮረው በአማራ ላይ ነው። የጠላት ፍጡሮች ሕወሓትና ኦነጋውያን፣ የሁለቱ ድቅል ፍሬ የብልጽግና ወንጌል እምነት መንግሥትም ዒላማዎቹ አማራነትና ኦርቶዶክሳዊነት ነው። ይህን ለመካድ መድከም ከበደኖ እስከ ማይካድራና ደብረ ኤልያስ ገዳም የፈሰሰውን የአርዓያ ሥላሴ ደም ሁሉ መካድ ነው።
አማራነት ለምን ዒላማ ተደረገ? አማራነት ጠላቶቹን ለማሸነፍ ማንነቱን በምን እሴት ቢገልጽ ያዋጣዋል?
አማራ የሚያሸንፈው ነባር ማንነቱን የቀረጹ የእምነት፣ የባህል፣ የረዥም ታሪኩ ሥነ-ልቦናዊ ሥሪቶችና እሴቶቹን ይዞ ነው ወይስ ጥሎ? የሚለው ጥያቄ ላይ መግባባት ለመኖሩ እርግጠኞች አይደለንም።
አንዳንድ የአማራ ፋኖ የአካባቢ አፈቀላጤዎችና የማኅበራዊ ሚዲያ ባለቤቶች እንደሚነግሩን ከሆነ “አማራ” እና “አማራነት” አሁን በአንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች እንደ አዲስ የሚፈጠር ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ ነው። ይህ አዲስ ፍጡር ያስፈለገው አማራን አንድ ወጥ ጠንካራና ለትግሉ ድል አድራጊነት አማራጭ የሌለው ምርጫ ሲሆን “ያፈጀና ያረጀ” ተብሎ የሚታሰበው ኦርቶዶክሳዊና ነባሩ ሙስሊም፣ የማኅበረሰቡ የሺ ዘመናት የሥነ-መንግሥትና የእምነት ቁርኝት ትርክት፣ ባህልና እሴት ሁሉ ተፍቀው የሚደመሰሱበት ነው።
በሌላ በኩል አማራንም ሆነ ኢትዮጵያን አሸናፊና ነጻ አድርጎ ያቆያት ነባር ሁለገብ ትርክት፣ እምነት፣ ባህል፣ ሥነ-መንግሥታዊ የረዥም ዘመናት ልማድ ሲሆን፣ አማራን ለህልውና አደጋ የዳረገው ከ60ዎቹ ትውልድ ፖለቲካዊ ርዕዮት ለአገር-ፈለቅ ዕውቀት፣ ትውፊት፣ እምነቶችና ባህሎች፣ እሴቶችና ማኅበራዊ መዋቅራት ተጻራሪ መሆን የሚል ወገን አለ። በዚህ ብያኔ መሠረት “አማራ የአማራነት መሠረታዊ እሴቶች ጠላት በመሆን የዘመቱበትን አስተሳሰቦችና አካላት የሚያሸንፈው ነባር አማራነትን አጠንክሮ በመያዝና የበለጠ በማጉላት ነው” ብለው የሚከራከሩ አሉ።
በሁለተኛው የድል ፍኖት አማራጭ ሙግት መሠረት አማራነት በደምና አጥንት ቆጠራ የተወሰነ ዘረኝነት ሳይሆን በነጻነት ያኖረው እሴቱ ነው። ይህ እሴት “ጥቁር ቆዳ ያላቸው ሰዎች እንደ በሬና አህያ ሁሉ ነጭ ቆዳ ላላቸው ሰዎች እንደ ተፈጥሮ ሃብት መገልገያ ናቸው” እስከ ማለት የደረሱ ዘረኞችን ፍልስፍና እና የበርሊን የአፍሪካ ቅርምት ፕሮጄክትን ያመከነ ነው። በዚህ እሴት የተገለጠው ሕዝብና ያስገኘው ድል ለመላው ዓለም የሰው ልጅ ነጻነትና እኩልነት ምስክር በመሆኑ ዘረኞች ተባብረው የሚጠሉትና በአገር ውስጥ ጠላት ያበጁለት እና “አማራ” የሚለውን አስፈሪም ተጠዪም ያደረገ ስም ነው።
ኦነግና ሕወሓትም ይህን ስም አስፈሪ ያደረጉትን እሴቶች ለማጥፋት ውል የቋጠሩትና በተላላኪነት የሚያገለግሉት በቀለኛ የውጭ ጠላቶችን በመወከል እንደሆነ የታወቀ ነው። አማራን “ነፍጠኛ” እና ኦርቶዶክስ ክርስትናን “የነፍጠኛ” ሃይማኖት በሚል መሪ ቃል ተስማምተው ሁለገብ ጦርነትን ማካሄድ ከጀምሩ ሃምሳ ዘመናት አስቆጥረዋል። ሤራው እጅግ የተራቀቀ በመሆኑ የተማሪ ንቅናቄ መሪ እንዲሆኑ በጠላት የተዘጋጁ የ60ዎቹ ተማሪዎችና ልዩ ልዩ ንቅናቄዎች፣ ደርግና አገርን መገንጠል “ነጻነት ነው” ብለው እንዲያምኑ አእምሮአቸው ታጥቦ ኤርትራን፣ ትግራይን፣ መካከለኛውንና ምሥራቁን የሀገራችንን ክፍሎች ለመከፋፈል የተሰለፉት ሁሉ በአንድነት ጠላት የሚሉት አማራን እና ኦርቶዶክስን ነበር። አሁንም የብልጽግና ወንጌል እምነት ላይ የተመሠረተውና ቀዳሚ ንቅናቄዎች የጀመሩትን መንገድ አጠናክሮ የቀጠለው የብልጽግና ሥርዓት ጠላቶቼ የሚላቸው፦ አማራን፣ ኦርቶዶክስ ክርስትናን፣ ማንኛውንም ነባርነት ያለው እሴቶችን ለነጽሮተ ዓለማቸውና ለማንነታቸው መገለጫነት መሠረት ያደረጉትን ወገኖች ሁሉ ነው።
“አማራ የዘረኝነት ፕሮጄክትን ዓለም አቀፋዊና ዘለዓለማዊ ለማድረግ ህልም የነበራቸው አካላትን ያደነቃቀፈ መንፈሳዊ፣ ባህላዊ፣ እምነታዊና ታሪካዊ መሠረት ያለው ሕዝብ ነው” በሚል ሀልዎት አመንጭተው ያመኑ አካላት በአብዛኛው የሚገፏቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ጂኦ-ፖለቲካዊና ስትራቴጂካዊ ጥቅሞች እንደሆኑ ይታወቃል። እነዚህን ጥቅሞች በዘለቄታዊነት ለማሳካት ኢትዮጵያን ነጻ አገር እንድትሆን ካስቻሏት ምሰሶዎች መካከል እምነትን፣ የሺዎች ዘመናት ትርክትን፣ የዜጎቿ በብዝኃነት ውስጥ አሐዳዊ የአንድነት እሴቶችና ነባር ማኅበረሰባዊ ቋንቋ-ዘለል ኢትዮጵያዊ ማንነትን መደምሰስ ቁልፍ እንደሆነ አምነውበታል።
ይህ እምነታቸው በከንቱ መላ ምት የመጣ ሳይሆን በእርግጥ የአድዋ ድል ቁስል ጥዝጣዜ የሚመሰክርላቸው ሐቅ ነው። በሌላ በኩል የዚህ ጠንካራ እሴታዊና ማኅበራዊ አንድነት መነሻው ነባር እምነቶች፣ ባህሎች፣ እና የሥነ-መንግሥት ዕሳቤዎችና ቅርጾች እንደሆኑ ተገንዝበዋል። ከሁሉ በላይ የነባሮች ነባር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና ሚና የላቀ በመሆኑ ጠላት ትኩረት ያደረገባት መሆኗ ከአህመድ ግራኝ ፈጣሪዎች እስከ ቫቲካን የጣሊያን ወራሪዎች ባራኪ ድረስ በመጽሐፍ ብቻ ሳይሆን በተግባር ፍጅት በመፈጸም አሳይተዋል።
የነባር እና አሸናፊ እሴቶቻችንን ዒላማ ያደረጉ የውጭ ጠላቶች ለብዙ ዘመናት አቅደውና ለፍተውበት ዛሬ ላይ የሚወክላቸውን አገር-በቀል ጠላት በማደራጀት ለመንግሥትነት አድርሰዋል።
ዛሬ ላይ የምንገኝበትን በአገር ውስጥ መከፋፈልን በመፍጠር አማራን ሀገር-በቀል ጠላት አፈሩለት። ጠላትነታቸው “አማራነትን” የሚገልጹ እምነቶችን፣ ትውፊቶችን፣ መንግሥታዊ ታሪካዊ ትርክቶችን የሚጨምር ነው። አንዳንድ የፋኖ የሐሳብና የጦር መሪ ካልሆንን ሞተን እንገኛለን የሚሉ የናርሲሲስት ባሕርያት ተጠቂዎችና ጭፍን ተከታዮቻቸው ሊያሰፍኑ የሚሞክሩት ዕሳቤ “አማራ በደሙና በአጥንቱ ልዩ” የሆነ፣ ጠላቶቹንም የሚያሸንፈው በዚህ “በፍጥረት ልዩ ነኝ” በሚል ፋሽስታዊ፣ እነ ሂትለር ራሳቸውንና ሕዝባቸውን ባዋረዱበት መንገድ መጓዛቸው አደገኛነቱ ታውቆ በእንጭጩ ሊጋለጥ ይገባዋል። ይህ መንገድ የአማራነት ጠላቶች ቀምረው ወደ ትግሉ ያሠረጉት የመሸነፊያና የመዋረጃ መንገድ ነው።
የተገፋው አማራ ከሚመስለው ወገኑ ጋር ተደራጅቶ መታገሉ ተገቢ ቢሆንም፣ “በደምና አጥንት ልዩ ነኝ” በሚለው ሐሳብ መሠረት “የአማራ ብሔርተኝነት” በሚል ስም ነባር ማንነቱን በማስጣል ጠላት-ሠራሽ አርቲፊሺያል ማንነት ለአማራ ማላበስ አማራን ለዘላለም ተሸናፊና ጠፊ እንጂ ህልውናው የተረጋገጠና ለዓለም ተገፊዎች ኢትዮጵያን ፋና ያደረጋትን እሴት አያስቀጥልም። አማራነት በታሪክም በተግባራዊ ሕይወትም ሊነገር ብቻ ሳይሆን ሊኖር የሚችልና የቻለ ሰዋዊ ማንነቱን የሙጥኝ ብሎ የእሴት ጠላቶቹን ለማሸነፍ የጀመረውን ፋኖነት ከክላሽ ተላላኪዎች በንቃት እየጠበቀ ተጋድሎውን ከግብ ማድረስ አማራጭ የለውም።
አማራ ጠላቶቹን ለማሸነፍ በአንዳንድ ልሂቃንና ታጋይ ነን በሚሉ የባእዳን የአእምሮ ባሮች አንድ አዲስ ተጠፍጥፎ ሊሠራ የሚያስፈልገው ፖለቲካ-ሠራሽ ፍጡርነት መቀበል አማራጩ ሊሆን አይችልም።
የሀገር ምሶሶ የነብሩ ሃይማኖት፣ ዘውዳዊ ሥርዓት፣ ርስት፣ ነባር ትርክትን የማጥፋቱ እቅድ በሮማኖ ፕሮቼስካም ተደርሶ በብዙ ቋንቋ ተትርጉሞ ለጥፋት መርኆ ፍኖት ሆኗል።
ይህን አዲስ ፖለቲካ-ሥር አማራ ለመፍጠር የሚሹ አካላት አማራን ከአሸናፊው ነባር አማራነት ነቅለው፣ ልክ ሕወሓትና ኦነጋውያን በጭፍን መንጋነት እየተከተለ ለማያቋርጥ ሃምሳ ዓመታት አገርና ሕዝብን ሲያዳክም እንደኖረው የትግራይና የኦሮሞ የነጻ አውጭዎች የስህተት አእምሮ፣ ባሪያ ትውልድ ለመፍጠር የሚሻ አንድም የፈተናው ውስብስብነት እና የችግሩ ጥልቀት ያልገባው፣ ወይንም የሕዝብን ንቅናቄ ጠልፎና አዋርዶ በራሱ ልክና ፍላጎት የሚሰፋ፣ ወይንም የማሰብ ነጻነቱን ያሥነጠቀ የኢትዮጵያ ጠላቶች ያደሩበት መገልገያ ብቻ ነው።
አማራነት ሳይለውጡት በራሱም አሸናፊ ነው! Amaraness does not need any modification of its original sources of identity just to win the enemies of Truth, Humanity, Justice and human unity. It does not need to be modified in to any type of ethnicity, racism or exceptionalist identity as some are trying to impose. Amara will win falsified identities that turned to be the enemy of Amaraness and became existential threat. Remaining Human and Truthful under the oath of God-given eternal values livid for at least two millennia is a winning identity that Amhara Fano protects and wins.
አንዳንዶች በ”ብሔርተኝነት” ተብዬ አደናጋሪና በታሪክ ከፋሺዝም አምልጦ የማያውቅ የዘር ንዑስ-ማንነት፣ በግልጽ ሳይተረጉሙት የታወቀውን “የተከበረ አማራነት” አልብሶ ለማዋረድ ጥረት መታየቱ ተቃውሞ ሊገጥመው የሚገባው ነው። ማን ይቃወመው? ብንል በመጀመሪያ “አማራነት” የገባቸው አማሮች እና ለክብረ-ሰብእ፣ ለፍትህ፣ ለእውነት፣ ለማኅበረሰቦች ሰላማዊ ውሕደትና አንድነት የቆሙ፣ እና ለህልውና አደጋ ዋና መንስኤ የሆነውን የማንነት ፖለቲካ የሚቃወሙ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ናቸው።
የተቃውሞው ፋይዳ ጎሣ-ዘለልና ከሀገር አልፎ ለዓለም ሁሉ የሚተርፍ በመሆኑ አማራነትን አዋርደው ለማሳየት እስከ ዛሬ አገራችንን ለማዳከም ክፍፍልን እንደ ዋና መሣሪያ በመጠቀም የመጨረሻ ድል አግኝተው በዓለም ታሪክ ረዥም ታሪክ ያላትን አገር “ኢትዮጵያንና ማኅበረሰባዊ እሴቶችን” ከዓለም የታሪክ መዝገብ እንዳይፋቅ በአድዋ ያሸነፋቸውን የጠላቶቻችንን አጀንዳ የሚሸከሙ የፋኖ የውስጥ ሰርጎ ገቦችን በጽኑ ሁለገብ ተጋድሎ ማስቆም ጊዜ የማይሰጠው ነው። አማራ ሊያሸንፋቸው ተነስቶ ደሙን የሚከፍልለትን ሰዋዊነት በዘረኝነት ሊያፍኑት እና የአማራነት እሴቶች ጠላቶች የዕሳቤ ሰለባ ቡድኖችን መዋጋት የህልውና ዋና ተጋድሎ መሆኑ ሊሠመርበት ይገባል።
አማራነት ፖለቲካ-ሥር (ፍጡር) ወይስ የማኅበራዊ፣ የሃይማኖታዊና ታሪካዊ እሴቶች ተፈጥሮአዊ ሂደት ግኝት ነው?
በዘመናችን አማራነት ሲተረጎም ቀላሉ ትርጉም በታሪካዊ የእሴት ማንነቶቹ ላይ ተመሥርቶ ከዓለም ጋር ኢትዮጵያ በነበራት ነጻነት ላይም የተመሠረተ ግንኙነትና ተጋድሎ ምክንያት ጥፋት የታወጀበት ኢትዮጵያዊ ክፍለ-ሕዝብ ማንነት ነው። የአማራ ማንነቱን በባእዳን ትምህርት ቤት ውስጥ ከሚሰጣቸው ትምህርት ውጭና በላይ በማያስቡ ዘመናውያን ልሂቃን ከብሔራውያን ሊቃውንት በመቃረን ለአማራ ጊዜያዊ መሰባሰቢያነት ብቻ በማስላት "አማራነት" እንዲተረጎም እያካሄዱት የሚገኘው በአማራነት ጠላቶች ቀመር አንጻር የሚተረጎም የተሸናፊዎች ርዕዮት አይደለም፡፡ ተሸናፊው የናዚ ጀርመን፣ የቅኝ ገዥዎች ከፋፋይ ዘረኝነት፣ ነጻነትን በመገንጠልና በመለያየት ጠባብ ኢሰብአዊና ኢፍትሐዊ ትርጉም በመስጠት አገራትን ሲከፋፍሉና ሲያዳክሙ እንደኖሩት፣ ቅኝ ገዥዎች በሐሰት ትርክት የፈጠሩት የቱትሲና ሁቱ ጠላት-ሥር ዘረኝነት፣ የሕወሓትና የኦነግ የጎሣ ጠባብ የናዚ ፓርቲ-መሰል ዘረኛ ርዕዮትና ሕሰተኛ ትርክቶች ፍኖትን ምሳሌ የሚያደርጉ አንዳንድ ፋኖ እና ደጋፊ ነን የሚሉ ቡድኖች ከወዲሁ አማራን ከአማራነት ነጥለው እንዲሸነፍ አውቀው በሤረኝነት ወይንም በጭፍን ገልባጭነትና መንጋነት ልማድ የተባለውን ሁሉ የሚያምኑ ናቸው።
አማራ “ህልውናዬን?” ብሎ ሲነሳ ጠላቶቼን ልምሰል ብሎ አይደለም። ግብግቡ የሚካሄደው ከአካላዊ ጠላቶቹ ብቻ ሳይሆን ስሑት ዕሳቤዎቻቸው፣ አጥፊ እሴቶቻቸው፣ ከተፈበረኩ መርዛማ የሐሰት ትርክቶቻቸውና ዘር በማጥፋት ላይ ከተሰለፈው መዋቅርና ሥርዓት ጋር ነው።
አማራን ለህልውና ተጋድሎ ያሥነሳው ውስጣዊ የኃይል ምንጭ ነባር እሴቶቹና ዒላማ ያስደረገው በታሪክ ውስጥ ጎልተው ያበሩ የልዩ ማንነቶቹ እሴቶች ናቸው ወይስ ልሂቃንና የትግል መሪዎች ነን የሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ያለበሱት አዲስ ፖለቲካ-ሥር የማንነት ካባ ያመነጨው ተአምራዊ ኃይል ነው?
የመነሳቱ ምክንያት ነባር ማነንቱን ያቆሙ ሁለ-ገብ እሴቶቹ ከሆኑ፣ ለምን በራሱ የተነሳውን ሕዝብ በማሳሳት ጠላቶቹ በሚመሩበት ተሸናፊ አስተሳሰብና ርዕዮት አምሳል ሊመሩት የሚፈልጉ ሰዎችና ቡድኖች በትጋት ይንጫጫሉ?
ከነባር ማንነትህ ነቅዬ ልቀይርህ የሚሉ የዘመኑ ልሂቃን ነን ባዮች አንዳንድ ቡድኖች ምክንያታቸው ምንድነው? ወይስ ከአማራ የህልውና ግብ የተለየ አጀንዳ ያላቸው ሰዎች መሪና ደጋፊ ሆነው መደመጥ ጀምረዋል?
ብሎ መጠየቅ ለትግሉ ወደ ጠቃሚና ዘለቄታዊ መደምደሚያ መዳረስ ቁልፍ ጉዳይ ነው።
የአማራ የአሸናፊነት ምሥጢሮቹ ምንድን ናቸው?
አማራ ነባር አሸናፊ አማራነቱን ሳይለውጥ ተነሳ ! ሊያከራክር የማይችለው እውነታ አማራን ለመታደግ ራሳቸውን ለወገን ለመስዋእትነት ያቀረቡ የአማራ ልጆችና የእሴቱ ተጋሪዎች የተገኙት ከአማራነት ነባር እሴቶች እንጂ አገር ሲያምሱ፣ ንጉሥ ሲገድሉ፣ ጳጳስ ሲሰቅሉ፣ እምነታቸውን በነጠላ የባዕዳን ትምህርት እየለኩ ሲክዱ በነበሩ ከንቱ ልሂቃን እና የጎሣ ፖለቲካ ልሂቃን ምሪት አይደለም።
ፋኖነትም ከአማራነት ነባር እሴቶች የሚፈልቅ እንጂ ጥቂቶች ቀምረው ለሕዝቡ ልጆች ያደሉት የልሂቃን አእምሮ ውጤት አይደለም። ዓላማውም አንዱን በሌላው ላይ የማንገሥ ወይንም አንዱን ክፍለ-ሕዝብ አሳንሶ ሌላውን ከፍ ለማድረግ፣ ወይንም ራሳቸውን በሕዝብ ደም አሻጋሪነት ለመንግሥታዊ መንበር አብቅቶ በተረኝነት መገዛዛት አይሆንም። ስለዚህ ፋኖነት የሚባለውም እሴት የቁማርተኞችና የብልጦች ፍጡር አይደለም። ፋኖነት በተግባራዊ ሕይወት ፈተናዎች ጊዜ የትድግና ማንነት መገለጫ እና የአማራነት ነባር የነጻነት መንፈስ ነው።
ፋኖነትን የተቀላቀላችሁ ወጣቶች በትክክል በአማራነት ነባር እሴቶች ላይ እስከቆማችሁ ድረስ የትግላችሁ ታላቅ ግብ ክቡር ከመሆኑ የተነሳ ሙሉ ሰብእና ባላቸው የሰው ልጆች ሁሉ የሚደገፍ በእግዚአብሔርም የሚወደድ ነው። ይህ አባባል ሳይሆን ለዓለም ቅኝና ባሪያ ለተደረጉ ጥቁርና ቢጫ ሕዝቦች ሁሉ ብርሃን በሆነ የአድዋ ድልና የአምስት ዓመቱ የእናት አባቶቻችን አርበኝነት ተግባራዊ ምስክርነት ያለው ነው።
አማራነትን በአማራው ደም መፍሰስ የማጥፋት ረቂቅ ሤራ
ጎጠኝነትና ጎሠኝነት የማሰብ አድማሳችሁን ያደከመባችሁ ወገኖች ከቀደሙት ፋኖዎች መካከል የጥቂቱን ስም ላስቀምጥላችሁና ደማቸውና አጥንታቸውን፣ እሴታቸውንና ሃይማኖታቸውን ለዩልኝ እና ራሳችሁን ፈትሹ፡፡ የጎሣ ሥብጥራቸው፣ የትውልድ ጎጣቸው፣ ቋንቋቸው ሳይሆን ድል አድራጊ ፋኖነታቸው የጋራ እሴታቸው ነበር። የዛሬ ፋኖ ቁመቱ ከፍ የሚለው በእነዚህ ትከሻ ላይ ቆሞ፣ የመስዋእትነታቸውን ምክንያት አውቆና አክብሮ እነዚያን ወልዶ ለነጻነት ያፋለማቸውን ከዘረኝነትና ራስወዳድነት የጸዳ ፋኖነት መከተል ነው። ብልጠትና የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ፣ የባእዳን ምክር፣ እና በብር መቸብቸብና በሥልጣን ፍቅር መናወዝ ፋኖ አያሰኝም። ፋኖ ለመሆን ፋኖ የሆኑትን የእናት አባቶቻችንን ታሪክ በመጠኑ የሚጠቅሰውን “የሀገር ባለውለታዎች ቅጽ አንድ” ሰንድ እንድትመለክቱ እነዚህን መቶ ፋኖዎች ስማቸውን ብቻ አስቀመጥኩላችሁ፦
1. ሁንዴ ቡልቶ (ልጅ)
2. ሐዋርያ ክርስቶስ አየለ (አለቃ)
3. ሐጎስ ብዙነህ (አቶ)
4. ኃይለ ማርያም ማሞ (ልጅ)
5. ኃይለ ማርያም ቸሬ (ፊታውራሪ)
6. ኃይለ ማርያም አላምረው
7. ኃይለ ማርያም
8. ኃይለ ማርያም ወልደ ገብርኤል
9. ኃይለ ማርያም ጎሹ
10. ኃይሉ ባሕታ (ባላምባራስ)
11. ኃይሉ አባፈርዳ (ቀኛዝማች)
12. ኃይሉ ከበደ (ደጃዝማች፣ ሌተና ጀነራል)
13. ኃይሉ ወልደ መድኅን (ደጃዝማች)
14. ኃይሌ ሸንቁጥ (ልጅ)
15. ኃይሌ አባ መርሳ (ቀኛዝማች)
16. ለማ አባ ኢሬ (ሻምበል) (ባላምባራስ)
18. ላቀ ተሾመ (ልጅ)
19. ላቀው ይፍሩ
20. መለስ ገብረ እግዚ (ፊታውራሪ)
21. መላኩ በያን (ዶክተር)
22. መልአከ ፀሐይ ኢያሱ (ንጉሠ ነገሥት)
23. መሐሪ ተክሌ
24. መርሶ አያሌው (ፊታውራሪ)
25. መርሻ ወልደ ማርያም (አለቃ)
26. መሸሻ ተወንድ በላይ
27. መሸሻ ወልዴ (ደጃዝማች)
28. መሸሻ ገብሩ (መቶ አለቃ)
29. መንገሻ ይልማ
30. መኩሪያ ነገዎ (አቶ)
31. መኮንን ብርዬ 4
32. መኮንን ደምሰው (ቢትወደድ)
33. ሙሉጌታ ይገዙ (ራስ)
34. ሚካኤል (አቡነ) - ሰማዕተ ጽድቅ
35. ማትያስ ገመዳ (ሻለቃ)
36. ማኅተመ ወርቅ እሸቴ
37. ምትኬ ደስታ
38. ሞገስ አስግዶም
39. ሣህሌ ዕንቊ ሥላሴ
40. ሥዩም ሀብተ ማርያም (የመቶ አለቃ)
41. ሥዩም ቀጭኔ
42. ሥዩም ገብረ ሕይወት
43. ሥዩም ወንዳፍራሽ (አቶ)
44. ሰለባ ወልደ ሥላሴ (ቀኛዝማች)
45. ሳሙኤል ይገዙ (ሻምበል)
46. ስምዖን አደፍርስ
47. ስብሐት ጥሩነህ
48. ሮማነ ወርቅ ኃይለ ሥላሴ (ልዕልት)
49. ሽመልስ ሀብቴ (ፊታውራሪ)
550. ሽፈራው ገብረ ማርያም (ልጅ)
51. ቆስጠንጢኖስ ኃይለ መለኮት (ልጅ)
52. በላሁ (የመቶ አለቃ)
53. በላይ ኃይለ አብ (ሌተና ኮሎኔል)
54. በላይ ቦጋለ (ልጅ)
55. በልሁ ደገፉ (ቀኛዝማች)
56. በቀለ ወልደ ጊዮርጊስ
57. በኩረ ወልደ ትንሣኤ (ሻምበል)
58. በኩሩ ተስፋት (ደጃዝማች)
59. በየነ መርዕድ (ደጃዝማች)
60. በየነ ወንድማገኘሁ (ደጃዝማች)
61. በየነ ጉደታ
62. ባሕሩ ካባ (ካፒቴን)
63. ባልቻ ሳፎ (ደጃዝማች)
64. ባሻህውረድ ሀብተወልድ
65. ባያብል ደስታ (ቀኛዝማች)
66. ብንያም ወርቅነህ (ኢንጂነር፣ካፒቴን)
67. ተሰማ ባንቴ (ፊታውራሪ)
68. ተሰማ ወልደ ጊዮርጊስ (ፊታውራሪ)
69. ተስፋዬ ገብረ ሕይወት (ቀኛዝማች)
70. ተክለ ብርሃን ደሳለኝ (የመቶ አለቃ)
71. ተድላዬ ወልደ ሥላሴ (ቀኛዝማች)
72. ተፈሪ ያዘው 303
73. ታደሰ መሸሻ (አቶ)
74. ታደሰ ተፈራ (ልጅ)
75. ታደሰ ገነሜ (ፊታውራሪ)
76. ታፈሰ ወልደ ትንሣኤ (ቀኛዝማች)
677. ነጋሽ (ፊታውራሪ)
78. ንጉሤ አስፈዳይ
79. አሰፋ ባሕታ (ቀኛዝማች
80. አሰፋ ተድላ (ሻምበል)
81. አሰፋ አድማሱ (ሻለቃ)
82. አሰፋ ወልደ ሰማዕት (ምክትል መቶ አለቃ)
83. አስካለ ሥላሴ መታፈሪያ (ወይዘሮ)
84. አስፋወሰን ካሣ (ደጃዝማች)
85. አስፋው ወልደ ጊዮርጊስ (ልጅ)
86. አበራ ከተማ (ፊታውራሪ)
87. አበራ ካሣ (ደጃዝማች)
88. አበራ ግዛው (ግራዝማች)
89. አበበች ይግለጡ (ወይዘሮ)
90. አብርሃ ደቦጭ
91. አንዳርጌ ደስታ (ልጅ)
92. አንዶም ተስፋ ጽዮን (ደጃዝማች)
93. አየለ ቁንጬ (ፊታውራሪ)
94. አያና ብሩ (ሻለቃ፣ ኢንጂነር)
95. አፈወርቅ ወልደ ሰማዕት (ደጃዝማች)
96. ኤልያስ ይግለጡ
97. እምሩ ግዛው
98. ኦሊቃ ድንግል
99. ዓለማየሁ ጎሹ (ፊታውራሪ)
100. ዕንቊ ሥላሴ ባንትይዳኝ (ደጃዝማች)
በሐሰት ራሳቸውን “ፋኖ” ብለው የሚጠሩ ነገር ግን የአማራነት ሙሉ እሴቶችን በተግባር የሚቃረኑ ስብስቦች እንደ አማራ ጠላቶች ማለትም እንደ ኦነግና ሕወሓት ራሳቸውን “እገሌ” የሚባል ‘ዘር' እና ‘የእገሌ ነፃ አውጭ' ነን ብለው የሚከተላቸውን መንጋ መፍጠር እስከቻሉ ድረስ መቀጠል መብታቸው ነው። ነገር ግን የሐሰት ፋኖነትን ተላብሰው የሕወሓትና የኦነጋውያን አምሳል ወራሽና የኢትዮጵያ ጠላቶች ተላላኪነታቸውን በአማራ ደም መፍሰስ ራሱን የአማራን ማኅበረሰቡንና ዒላማ ያስደረገውን ታሪካዊ የማንነቱ መሠረቶችን እንዲያጠፉ ሊፈቀድላቸው አይገባም። በአማራ ወጣቶች ደም የአማራ ተቃራኒ ግብ ለማሳካት መንቀሳቀስ ወንጀል ይሆናል።
አማራነትን ያቆሙ እሴቶችን በጠላቶቹ ዕሳቤና የፈጠራ ነባር-ጠል ትርክት በመቀየር አማራነትን በሁለንተናው ደምስሶ በጠላቶቹ ዓይነት ጥፉ እሴቶች በመቀየር የማያስብ ዘረኛና ፋሽስታዊ መንጋ በመፍጠር አይተኬ ነገሥታት ለመሆን የሚንቀሳቀሱ ሰርጎ ገቦች መርዛማ ሐሳቦቻቸው ለጋ ወጣቶችን ሳይበክል መገታት አለበት።
እነዚህ የአማራነት ጠላት “አማራዎች” ራሳቸውን ከመጋለጥ የሚከላከሉባቸው --- ስልቶችና አነጋገሮች ከወዲሁ ይፋ መሆን ስለሚገባቸው --- ጥቂቶቹን እዚህ እንጠቅሳለን፦
(1) “ስለ አማራ የሚያገባን እኛ ራሳችንን የሾምነው ብቻ ነን” ስለሚሉ የሚቀርቡ ሐሳቦችን ከመሞገት እየሸሹ ሐሳብ የሚያመነጩ ቡድኖችንና ግለሰቦችን “አያገባችሁም” በሚል የመንጋ ጫጫታ ዝም ሊያሰኙት ይሞክራሉ፤ በቅርበት ካገኙት ያሥራሉ፣ ያስፈራራሉ ይገድላሉ፤
(2) አማራ ከነባር የአማራነት እሴቶቹ ተነጥሎ የእነዚህ ሤረኛ ቡድኖች የአእምሮ ባሪያ ሆኖ ልክ የትግራይና የኦሮሞ ወጣቶች ዘረኛ ነጻ አውጭዎች ነን ባዮቹን ቡድኖች አዝለው ለእኩይ ቡድኖቹ አገር የማፈራረስ፣ አማራና ኦርቶዶክስን የማጥፋት ግቦችን ለማሳካት እንደተጋለቡት፣ ከአማራ ፋኖ ግብ ውጭ ለድብቅ ጠባብ ዓላማቸው ሊጠቀሙባቸው --- “እኛ አማራ እንዲሆን የምንፈልገው ዓይነት ብሔርተኛ፣ ርስቱም ሕወሓት አገርን ባዋቀረበት የተከለለ፣ ታሪኩም እኛ አዲስ እንደምንተርከው ይሁን” ሲሉ ይሰማሉ፤
(3) በግለሰብና በቡድን ደረጃ ሤራቸውን ወይንም ስሕተታቸው ሲተች ሰምቶ እንደመታረም ወይንም አስተያየቶችንና ትችቶችን በአመክንዮ እና በማስረጃ ከመሞገት ይልቅ ሐሳብና ትችት አቅራቢዎች “እገሌ የአማራ ጠላት ነው!! ለፋኖ አንድነት ጠላት ነው!” በሚል ጫጫታ ይታወቃሉ፤
(4) የሃይማኖት፣ የባህል፣ የማኅበራዊ ወንዝ ዘለል ጉዳይ ሲወሳ ፈጥነው “እኛ አዲስ ትውልድ ስለሆንን በአዲስ መንገድ ነው የምናስበው፣ እናም አማራ ሁሉ እኛን ብቻና ብቻ መስማትና ነባር እሴቶቹን መጣል አለበት” የሚል አንድምታ ያለው መልእክት ያስተላልፋሉ፤
(5) በመካከላቸው የተለየ ሐሳብ የሚያቀርብ፣ አደረጃጀትና ስልት ለማስተዋወቅ የሚሞክርን ጓድ ስም ከማጥፋት ጀምሮ በሐሰት በመክሰስ ማሳደድና መረሸን፤
(6) ከሕዝባቸውና ከፋኖ ሠራዊት ጀርባ ከአማራነት እሴቶች እና የተጋድሎ ግቦች ከሚቃረኑ የውጭና የአማራ ሕዝብ የህልውና አደጋ መከሰት ጀማሪና አስቀጣይ ከሆኑ አካላት ጋር ለጠባብ ቡድናዊ ግባቸው መሳካት እገዛ በመሻት በኅቡዕ መገናኘትና አንዳንድ የቁማር ስልታቸውን መዋስ፤
(7) ከኢሕአፓ፣ ሕወሓት፣ ደርግ፣ ኦነግ ወዘተ እንደተማሩት ጸረ-ኦርቶዶክስ አቋም ይዘው መንቀሳቀስና ሕዝቡን ለማጭበርበር የሃይማኖቱን ምልክቶች፣ አንዳንድ የታወቁ አነጋገሮችና መሐላዎች መጠቀም፣ ከሚወደዱ ስመ ጥር አርበኞችና ነገሥታት ዝና ለመጠጋት ደጋግሞ ስማቸውን ከሚገባው አግባብ ውጭ ሁሉ ሳይቀር መጥራት ነገር ግን በተግባር መቃረን፤
(8) ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ አማራን በሚከፋፍል ጎጣዊ ኔትዎርክ በመተሳሰር ያመናቸውን በአሳሳች መረጃና ፕሮፓጋንዳ አማራ አቀፍ ትብብርን ማዳከም፣ በየእምነት ቤቱና በማኅበራት መካከል አሉታዊ ሚና የሚጫወቱ የተሳሳቱ መረጃዎችን የሚያቀርቡ፣ ከጎጣቸው ውጭ ያሉ አማሮች ድጋፍ እንዳያገኙ አደረጃጀቶችን መከፋፈል፤
(9) “ያለ እነ እገሌ አገራት ይሁኝታና ፍቃድ ሥልጣን መያዝ ስለማንችል የሚሉንን ሁሉ እናደርጋለን” በሚል ያልተጻፈና ከሠራዊቱ የተሰወረ መርሕ በመከተል ቃል ኪዳን መግባት፤ ለምሳሌ ከኦርቶዶክስ ሃይማኖት መራቅና “ትግላችን ከሃይማኖት የጸዳ ነው” የሚል ጩኸት መደጋገም፣ የእምነቱን ምልክቶች በሰውነት ላይ እንዳይታይ መጠንቀቅ፣ ወልቃይትና ራያን በሚመለከት በምንም መልኩ አቋማቸው በግልጽ እንዳይታወቅ መጠንቀቅ፤
(10) አማራ አሁን የሚያጠቃውን ጠላት ከማሰብ በተጨማሪ ከፍታውን የሚያስጠብቁ አማራነትና የፋኖነት የድል ምሥጢሮችን አውልቆ ጥሎ በስሜትና በፕሮፓጋንዳ ስሜት ላይ እንዲቆም አማራነቱን ከነባርነቱ ለይቶ እንዲመለከት የፕሮፓጋንዳ ጎርፉን በጠላት ላይ ከመልቀቅ በሚበልጥ ደረጃ አማራን ዒላማ በማድረግና ከትግሉ በመግፋት፣ በውስጥ ውድድር፣ በዝና ግንባታ እንዲጠመድ ማድረግ ---- በመሳሰሉ ምልክቶች መረዳት ይቻላል።
እውነተኞቹ የአማራነት እሴት መገለጫ የፋኖ መሪዎች፣ ልሂቃንና ምክር ለጋሾች፣ የአማራ ጠላቶች እቅድ ተፈጻሚ እንዲሆን በሚያመቻች የነባር ማንነት ድምሳሴ ሂደት ውስጥ በተሠማሩ ፋኖ ባልሆኑ ሤራ-ሥር የሐሰት ፋኖዎች በሐሰት ጫጫታ እንዳይጠለፉ፣ ሕሊና ያለው የአማራነትና የሰብአዊነት ወዳጅ ሙሉ ሰው ሁሉ በይሉኝታም ይሁን የመንጋ ጫጫታ ሳይሳቀቅ ጠቃሚውን ከጎጅው እየለየ የመጠቆም የሞራል ዕዳ አለበት።
የአማራ ጠላቶች አማራውን ታናሽ ለማድረግ ከሚጠቀሙበት ስትራቴጂዎች መካከል አንዱና ዋነኛው አማራን ከትውፊቱ ከእሴቱና ከማንነቱ ማውረድ ነው። እንደነሱ አገላለጽ "አማራ የሚለው ስም የሚወክለው አጥንትና ደም እንጂ አማራ ሌላ የሚሰባሰብበት መሠረተ-ፍልስፍና፣ እሴት፣ እምነት፣ ባህልና ታሪክ የለውም ነው።” የሚል ድምዳሜ ይዘው ነው። ይህንን መከራከሪያ አድርጎ የሚቀበል ማንኛውም ታጋይና ልሂቅ የሚከተሉትን ጥያቄዎች በግልጽ መመለስ ይጠበቅበታል፦
1ኛ. አማራነት ስንል እሴት፣ አስተሳሰብ፣ ታሪክ፣ እምነት፣ ባህል፣ እና ኢትዮጵያዊነት የማይመለከተው፤ በደምና አጥንት ዝርያ ብቻ የሚበየን ብሔር ከሆነ፤ በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ አገው፣ ቅማንት፣ በርታ፣ ሽናሻ፣ ጉምዝ እና ሌሎች ንዑሳን ማንነቶች ሁሉ አማራነትን የማይጋሩ ሌሎች ናቸው?
2ኛ. ከአሰፋፈር፣ ከክልል፣ ከቋንቋ፣ እና አዳዲስ ሊፈጠሩ ከሚችሉ ፖለቲካ-ሥር ማንነቶች በዘለለ አሰባሳቢ አማራዊ እሴቶች፣ ለአማራነት ሁለንተናዊ የህልውና ድልና ዘለቄታዊነት የበለጠ የሚጠቅመው የትኛው ነው?
3ኛ. አማራን ሕወሓትና ኦነግ “ነጻ እናወጣሃለን” በሚል ጠባብ የደምና የአጥንት ልዩነት ትርክት ላይ እንዳቆሙትና ለአማራና ለኦርቶዶክሳዊ ክርስትና ጠላት እንዳደረጉት በፋኖነትና ደጋፊነት ስም “አማራ አንድ የሚሆነው፣ ድል የሚያገኘው በብሔርተኝነት ብቻ ነው።” በሚል ሀልዎት አማራነትን ተፈትኖ በወደቀ የፋሽስቶች ርዕዮት አማራጭ እንደሌለው አድርጎ ማቅረብ ለአማራ ሕዝብ ህልውና መረጋገጥና መዝለቅ፣ ወዳጅና ቤተሰብ ማስፋት እና በአንጻሩ በስሕተትና በሐሰተኛ ትርክት ምክንያት የአማራ ጠላት የሆኑትን በእውነተኛ አማራነት ለመማረክና ወዳጅ ለማብዛት የትኛው ይጠቅማል?
4ኛ. አማራን ከፍ ካለው ሰብአዊ እሴት ወደሚያዋርደው የዘረኞች የ50 ዘመናት የትግል አካሄድ በመዋስ ፋኖነትን አዲስ እና ባዕድ እሴት ማውረስ ነው ወይስ አማራነትን ተረድቶ የማክበር፣ በአሸናፊነቱ የመተማመን፣ በነባር አማራዊ እሴቶች መጽናት ፋኖነትን ይገልጻል? ትግሉንስ ይጠቅማል?
አማራን በነጻ አውጭዎቹና ወጭዎቹ አምሳል ሊፈጥሩትና ወደባሰ ዘለቄታዊ የህልውና አደጋ ውስጥ ሊያስገቡት የሚሹ አካላት ምክር የተጠለፉ ሰዎች ካልሆኑ በስተቀር ሰው በሚዛናዊ አስተሳሰቡ ከዘረኝነትና ጠባብነት በላይ ወጥቶ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ተገዥዎች የሙሉ ሰብእናና የበዓለአገርነትን ምንነት ያስተማረውን ሕዝብ መልሶ በጎሠኞች አምሳል ለማሟሸሽ መሞከር ከህልውና ጠላቶቹ ከፍቶ መገኘት ነው። ይህንን በአመክንዮአዊ ተጠየቅ ፊት የማይቆም ተልካሻ ሐሳብን በፕሮፓጋንዳ ብዛት ፋይዳ ያለው አስተሳሰብ ለማስመሰል መድከም በጉዳዩ አምኖ ከማድረግ ያለፈ ሤረኝነት ያስመስለዋል።
የአማራን ጠላት የሚዋጋ መስሎ አማራነትን ወደ መውጋት ሊለወጥ የሚችል ዕይታ
ምናልባትም የአማራን ጥፋት ለማሳለጥ የተቀጠሩ የውጭና የውስጥ ቅጥር ሠራተኞቻቸው አማራ የህልውናዬ ጠላት የሚላቸውን የፖለቲካ ርእዮቶችና መዋቅሮቻቸውን ዒላማ አድርጎ ለዘለቄታዊነት ከማጥፋት ይልቅ ለአማራ ዘለዓለማዊ የዘር ፖለቲካ ርዕዮትን በቋሚነት ለማስቀጠል በውጭ አማካሪዎች ሤራ አማራን ራሱን ዘረኛ ፋሽስት በማድረግ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያዊነቱ፣ ከኦርቶዶክሳዊነቱ፣ ከታሪኩና ከነባር አሸናፊ የማንነት እሴቶቹ በመለየት ዘላለማዊ ተሸናፊ ብሎም ጠፊ የማድረግ ሤራ ይመስላል።
በዘረኝነት የሚሰለፍ አማራነት በዘረኝነት ከተሰለፉበት ፖለቲካ-ሥር ትውልድ ጋር እኩል ዘቅጦ ቅኝ ገዥዎች የሚፈልጉት ዓይነት ጎሠኛ ይሆናል። ታሪኩና አገሩን በጠላቶቹ ዓይን የሚመለከት፣ ጠላትነቱም ከገዥው ዘረኛ ሥርዓትና የጎሣ ፖለቲካ መሥራች የባእዳን ተላላኪ ቡድኖቹ ጋር መሆኑ ቀርቶ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጎሣዎች ስለሚሆን ሲቪል የርስበርስ ጦርነት በር በመክፈት ከአማራ የህልውና አደጋ ትግል ግቦች ተቃራኒ ሆኖ ይመክናል። ዘር ሆኖ የሚመጣ ትግል ጠላቱ አስተሳሰብና ርዕዮት፣ ዕሴትና ስሑት ትርክት መሆኑ ቀርቶ አቻ የሆኑ ሌሎች በዘረኝነት የተሰለፉ ወገኖቹን በደምና አጥንት ልዩነት የሚፈርጅ ፋሽስት ይሆናል። ይህ ደግሞ የነባር የአማራነት እሴቶች ተቃራኒ ነው።
እኛ አማሮች ልዩ አጥንትና ደም አለን በሚል ስሑት ፖለቲካ-ሥር ማንነትን በማቀንቀን አሸናፊውን ነባር አማራነት እንደ ሌሎቹ “ሌላ የዘር ማንነት” ከተዋረደ በእርግጥ ያ የምናውቀው ፋኖነት ብቻ ሳይሆን የሰብአዊነትን የሰው ልጆች ክብር ጠላት የሆነ ናዚነት ይሆናል። በ "እኛ ልዩ ዘር ነንና የተሻለ ይገባናል፤ ሌሎች ከሰውነት ያነሱ ናቸውና እናጥፋቸው" በሚል ቀላል፣ ኢሰብአዊ፣ ኢፍትሓዊና አምላክ-የለሽ ርዕዮት መገንባት ለእውነተኛው ነባር አማራነት ከጠላቶች ሁሉ የከፋ የአስተሳሰብ ጠላትነት ነው፡፡
በዚህ ማኅቀፍ ውስጥ አማራን በአጥንትና በደም የሚለካ የፖለቲካ ልሂቅና የፋኖ ታጋይ ከተገኘ እርሱ ሰው ሳይሆን አማራን ዘር የማድረግ መንገድ ላይ በማስቀመጥ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት "ለናዚ ጠላቱ አይሁድ ነው” እንደተባለ ሁሉ ለአማራ ጠላቱ “እገሌ የሚባል ጎሳ ነው”፤ “እገሌ የሚባል ክፍለ-ሕዝብ ነው”፤ “እገሌ የሚባል እምነት ተከታይ ነው”፤ ወዘተ ወደሚል ተሸናፊና ጠፊ አማራን በመፍጠር የሩቆቹን የቆዩ አማራነት-ጠሎችና ተላላኪዎቻቸውን የኦነጋውያንና የሕወሓታውያን ውድቅ ርዕዮት ይዞ አጀንዳቸውን በአማራ ወጣቶች ደምና ሀብት ለማሳካት መንቀሳቀስ ይሆናል። በዚህ መንገድ ማሰብ የአማራውን ነባርና ዘመን ተሻጋሪ፣ አሸናፊ ማንነትና የህልውና ዋስትና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመቅበር የጥቁር ሕዝቦችን ሁሉ የብርሃን ፋና ማጥፋት፣ ፓን አፍሪካኒስት ምልክቶቻችንን መካድ ይሆናል።
ከአዲስ የደምና አጥንት አማራነት እና ከነባሩ የእሴት አማራነት መካከል የቱን እንምረጥ? ለምን?
ፋኖ አማራነትን ሳያውቁት እና ሳይሆኑ አማራ መስለው በአማራ ሕዝብ መካከል ተደራጅተው በመግባት እነርሱ በፈቀዱለት ሐሳብ፣ ክልል፣ ፖለቲካዊ ርዕዮት፣ አደረጃጀት፣ ሚዲያ፣ የአገር ትርጉም፣ የአማራነት ብያኔ፣ በመረጡለት እምነት ወይንም ሃይማኖት- አልባነት፣ ሕወሓትና ኦነግ በወሰኑለት ክልል እንዲወሰን ማመቻቸት ይሆናል። እነዚህ ፋሽስታዊ መሰል ሕዝብን የመወሰን ዝንባሌ ያላቸው ቡድኖች “ሌሎቻችሁ ምንም ዓይነት ሐሳብ አትስጡ፤ ሕዝቡ የግላችን ዕቃና መሣሪያ ነው" ይላሉ፤ አንዳንድ ፕሮፓጋንዲስቶችና የማኅበራዊ ሚዲያ ገበያተኞች ግልጽ የሆነ የፋኖን አቋም በማራመድ እኛ ከፈቀድንለት ውጭ ስለ አማራ ሕዝብ ተጋድሎ ማንም አይመለከተውም ማለታቸው ታውቋል።
በሕወሓታውያንና ኦነጋውያን አምሳል አማራን የግል መገልገያና መስዋእት እናደርገዋለን፣ እሴቶቹን፣ ታሪኩን፣ እምነቱን ጨፍልቀንና አጥፍተን በዘር ብቻ እንዲያስብ እናደርገዋለን ማለት ግን ከሰብአዊነት፣ ከክብረ-ሰብእ፣ ከእውነት፣ ከታሪክ እና ከእምነት ሁሉ የሚቃረን ከመሆኑም በላይ አገራችንን እንዳጠፉት በማያውቁት ቅዠታዊ አዲሥነት ነባሩን ሲነቅሉ እንደኖሩት ያለፉት ንቅናቄዎች መሆን ብቻ ነው። ፋኖነትንም አማራነትንም ይቃርናል። ምናልባትም ይህን ዓይነት ባዕድ ነገር “የእኔ ትውልድ ያፈጀና ያረጀ ትርክት አይቀበልም፤ አዲስ አስተሳሰብ እናስተዋውቃለን” በሚል ያላዋቂነት ትዕቢት ሕዝብን የሚያጠፋ ግልብና ያልተብራራ ዕሳቤ ማቀንቀን የሚጠቅመው ጠላትን እና ይህን አዲሥነት ለሚያቀነቅኑ ቡድኖችና መሪ ግለሰቦች ተክለ ሰውነት መገንቢያ ከመሆን አያልፍም። ምናልባትም ሐሳቡ የብዙኃን ወጣቶችን ልብ ማሸነፍ ከቻለም የሚደመደመው "የግለሰቦች ፖለቲካዊ ርዕዮት ፍጡር የሆነ አማራን" በመፍጠር አማራ ራሱ የሚሰዋለትን ነባር አማራነት የሚያከስም ይሆናል። ውጤቱም ቢበዛ ይሄንን ጨቋኝ መንግሥት የፈጠረውን ርዕዮት ማሸነፍ መሆኑ ቀርቶ የራሱን የሃይማኖት፣ የባህል፣ የማኅበረሰብእ ንዑስ ማንነት የሚወጋ፣ የኢትዮጵያውያንና የጎረቤት ሀገራት ሕዝቦችን ሁሉ ተስፋ የሚያስቆርጥ ሁኔታ ፈጥሮ ይሸነፋል።
ፋኖነት ራሱን ከዚህ አካሄድ ካላጸዳ ለአማራ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ማኅበረብ ከባድ የህልውና አደጋ በመጋረጥ ይሄንን አደገኛ አካሄድ የሚያስቆም ኃይል እስከሚወለድ ድረስ የአማራን ወጣት እያታለሉ በማስከተል የአማራው የሰቆቃ ማስቀጠያ የሕወሓትና ኦነግ ታናሽ ወንድም ከመሆን አያመልጥም።
ፋኖአዊ የአማራነት ተጋድሎን ለፋሽስታዊነት ካጩት ጠላቶች ለመታደግ የምሁራንና ደጋፊዎች ሚና
በመጀመሪያ ክቡሩንና ተስፋ ሰጭ የአማራነት እሴቶቹንና ፋኖነትን መንከባከብና እንዳይበላሽ መጠበቅ በጎሣ ፖለቲካ ስሌት ራሱን አማራ ብሎ በሚጠራ አማርኛ ተናጋሪና ንቁ የትጥቅ ትግል ተሳታፊ ብቸኛ ባለቤትነት መፈረጅ ታላቅ ስሕተት ይሆናል። ይህ ትግል የሚመለከታቸው አካላት በቅደም ተከተል (እንደ እኔ ምልከታ) የሚከተሉት ስለሆኑ ስለ ትግሉ ፍልስፍናና ምሪት ይመለከታቸዋል፡፡ ምክንያቱም ውጤቱ ስንኳንስ ኢትዮጵያውያንን ምሥራቅ አፍሪካንና የዓለምን ጂኦ ፖለቲካዊና ስትራቴጂካዊ ሁኔታ የመቀየር ከፍተኛ አቅም ያለው ነው፦
1ኛ. “አማራ ነህ” ተብሎ የህልውና አደጋ የተደቀነበት ማንኛውም ሰው ከደካማ እናትና አባት እስከ ተዋጊ ወጣት፤
2ኛ. ቋንቋ፣ አሠፋፈር፣ የፖለቲካዊ ንዑስ-ማንነት መሥመር ሳይገድባቸው የአማራነት እሴት ተጋሪዎች የሆኑ እና በዚህ ምክንያት የኦነጋውያንና ሕወሓታውያን እንዲሁም የውጭ ላኪዎቻቸው ዒላማ የተደረጉ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ሁሉ፣
3ኛ. በሰው እኩልነት፣ በአማራ የህልውና አደጋ ላይ መውደቅና ራሱን ለመከላከልና ህልውናውን ለማረጋገጥ በሚያደርገው ተጋድሎ ፍትሐዊነት የሚያምኑ ማንኛውም ቡድኖችና ግለሰቦች፣ የእምነት ተቋማት መሪዎችና መምህራን፣
4ኛ. በአገር ውስጥና ውጭ የሚኖሩ የአማራ ተጋድሎ ድል አድራጊነት በሕይወታቸውና በመጭው ትውልድ ተስፋ ላይ አዎንታዊ አሻራ እንዲኖረውና የአገራችንንና ሕዝቧን ልዕልናና ሉዓላዊነት እንዲያረጋግጥ የሚሹ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች በሙሉ፤ --- ናቸው።
እነዚህ ለትግሉ ባላቸው አዎንታዊ አመለካከት በልዩ ልዩ ዘርፍ ማለትም ከሐሳብ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት የሚሳተፉ ሁሉ የአማራ ትግል ይመለከታቸዋል። ስለዚህ ሁሉም እንደየአቅማቸውና ተጽእኗቸው መጠን ትግሉ ፋኖአዊ መልኩ ሲወይብ፣ አማራነትን ለማደስና ለመጥለፍ ሲሞክር፣ አንድ ሰው የራስ ወዳድ ሤራ ሰለባ ሆኖ የጠላት መጠቀሚያ ሊሆን መንደርደሩን ሲመለከት፣ ከሰብአዊነትና ፍትሕ ወደ ዘርና ፋሽስታዊ የአማራነት ጠላት እሴቶች ሲያሽቆለቁል መሪዎችን መናገር፣ መምከር፣ ሕዝቡን ማንቃትና ሠርጎ-ገብ እንግዳ ምልክቶችን ማጋለጥ ይኖርበታል። ይህን ባለማድረግና መሪዎችን ከስሕተት ባለመጠበቅ እንደተለመደው የቡድን መንጋና ጎጠኛ ዕሳቤ በጭፍን በመከተል ትግሉ ከአማራነትና ፋኖነት ወርዶ ሌላ ተጨማሪ የሕዝብና የአገር የህልውና አደጋ ካስከተለ ሁሉም ተጎጅና ተጠያቂ ይሆናል።
የኢትዮጵያዊነትና የእውነት ጠላት ከሆኑት የዘመኑ 'ነፃ አውጭዎች' (ሕወሓትና ኦነግ) ጋር እኩል የሩቅ ጠላት መገልገያ ማኅደሮች የሆኑ ግለሰቦችና ጥቂት ተከታዮቻቸው ትግሉን ሐዲዱን ሊያስቱት እንዳይችሉ አድርጎ በቅርበት መሳተፍ ግዴታ እንጂ ፍቃድ የሚጠየቅበት የፋኖ መሪዎች ሞኖፖሊና ብቸኛ ገንዘብ አለመሆኑን እና ለአማራና ለሀገራችን ህልውና አዎንታዊ ቁርጠኝነት ያለው ዜጋ ሁሉ መሆኑን ማጽናት ይገባል።
ክቡር እና ቅዱሱ የፋኖነት እሴትና ግብ በመንገድ ላይ ተጠልፎ ለጠላቶች መሣሪያ ወይንም የናርሲሲስት ባሕርይ ተጠቂ በሆኑ ግለሰቦች ጠባብ ድብቅ ፍላጎት መገልገያነት ከንቱ እንዳይሆን በስሜትና በፕሮፓጋንዳ ዝናም ውስጥ ባልተጠመቀ፣ ከቡድን ዕሳቤ እሥረኝነት ነጻ በሆነ የነቃ አእምሮ ትግሉን በሐዲዱ ላይ ማስኬድና የተነሳለትን ዋና ግብ እንዲያሳካ ማስቻል የሁሉም ሰብአዊ ባለ ሕሊና ሰው ሁሉ ግዴታ ይሆናል።
ሕዝብ አክባሪ ፋኖነት መገለጫው በሕዝቡ እሴቶች መመራት እና የመስዋዕትነት ዋጋውን ትርፋማ በማድረግ ላይ ማተኮር ነው
ፋኖነት ትህትናን ከጀግንነት ያጣመረ፣ ስልትና ቁማርን የለየ፣ ፍትሕንና ሰብአዊነትን ያስቀደመ፣ ወቅታዊነትን ከዘለቄታዊነት ያሰናሰለ ሩቅ አሳቢ፣ ጥንቁቅ የቅርብና የአሁን ተግባራዊ ውጤታማነትና ድል የሚስማሙለት ነው።
ፋኖነትን ተኩሶ መጣል ብቻ የማያስፈነድቀው፣ በወገንና በፖለቲካው ብልሽት የአማራነትና የነባርነት ጠላት ሆኖ የተሰለፈውን የገዥ ዘረኛ መንግሥት ሠራዊትና ባንዳን እንኳ አማራጭ በማጣቱ ምክንያት እያለቀሰ የሚገድል እንጂ በሰው አስክሬን ላይ እንደ አራዊት ግዳይ ጥሎ የሚፈነጥዝ ኢሰብአዊነት አይገልጸውም።
ፋኖነት ሰውን ከሰውነቱ አሳንሶ የማይመለከት፤ እና ክፉ አስተምህሮ፣ ስሑት ርዕዮትና ለተራዘመ ዘመን በሕወሓትና ኦነጋውያን መርዛማ የሐሰት ትርክት አማራ-ጠልነት ያሳወረውን ሰው ከጥይት ውጭ በሐሳብ ብቻ የሚያሸንፍበት አውድ ቢፈጠርለት ደም አፍሳሽነትን የሚጸየፍ፤ በፈሪሃ እግዚአብሔር የታነጹ የምኒልክ ልጆች ዕሴት መገለጫ ነው።
ፋኖነት፣ ቀደም ሲል እንዳብራራነው ሕዝብን ማክበሩ ስለሚመግበው፣ ከአብራኩ ስለተከፈለ፣ ከጠላት መሸሸጊያ ስለሚሆንለት ብቻ ለመጠቀሚያነት ሳይሆን ሕዝቡን፣ ልዩና የህልውና አደጋ አድራሾቹ ዒላማ ያስደረጉት ነባር የማንነቶቹ መሠረቶችን ማለትም እምነቶቹን፣ ባህሎቹን፣ ማኅበራዊ መስተጋብሩን፣ መንፈሳዊና ዓለማዊ መዋቅሮቹን፣ ተስፋውን፣ ዕውቀቶቹንና ባህላዊ አመራሮቹን ሁሉ ለማስጠበቅ፣ ለመጠቀም፣ አክብሮ ለማልማት ቁርጠኛ የሆነ ፖሊሲ ነው።
ነገር ግን ፋኖነትን ስሙን እየተጠቀሙ በተቃራኒው የሕዝብ ልጆችን እየመራን መዋጊያ መሣሪያ እናደርጋቸዋለን፤ ለዚህ የምንፈልገው ከባህልና እምነት ያገኘውን ጀግንነቱን፣ ጤናማ አካሉን እና የውጊያ አቅሙን እንጂ የነባር ማነነቱ መሥረቶችን ማለትም ኦርቶዶክሳዊ ክርስትናን፣ እስልምናን፣ የቀደመ ታሪካዊ የሥነ-መንግሥት ትርክቱን አልፈልገውም ማለት እጅግ የበዛ ትዕቢት፣ ሕዝብን መናቅ፣ አለፍ ሲልም ለአማራነት ጠላትነት ባፈሩት አካላትና ርዕዮት መሸነፍ ነው። በዚህ መንገድ “የአማራ ህልውና ታጋይና መሪ ነኝ” ማለት ትርጉሙ የአማራ ህልውናው እንደ እንስሳ አካሉና ሆዱ ብቻ ነው፣ እምነቱን (ክርስትናና እስልምናን)፣ ባህሎቹን፣ እሴቶቹን፣ ረዥም ታሪኩን ሙሉ አይመለከትም እንደማለት ሲሆን ውጤቱም ህልውናውን መታደግ ሳይሆን ለጥፋት ማመቻቸት ነው።
መሪዎችና መካሪዎች “በአማራ ብሔርተኝነት ብቸኛ ታዳጊነት” ዶክትሪን ተቸክለው፣ አማራነት የሚገለፅበትን ሙሉ የህልውናውን መሠረቶች ትተው፣ ለኢትዮጵያ ነጻ አገርነትና ለአፍሪካ መነቃቃት የተትረፈረፈ እሴቶቹን አስጥለው፣ በአዲሥነት ስም ወደማያውቁት ጨለማ ከመሩት የ፷ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ፣ የደርግ፣ የኢሕአፓ፣ የወያኔ፣ የኦነግ፣ እና የሌሎች ሀገር-ጠል ውጭ ናፋቂዎች አንጻር ልዩ የሆነውን እውነተኛ የፋኖነት ክብርና ውጤታማነት በፋሽዝም ተርጉመውት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከትውልድ መዝገብ ያጠፉታል። አማራንና አማራነትንም እስከነ ርስቱ ያስጠፉታል። ከዚህ ውድቀት ለመትረፍ ትህትና ያስፈልጋል። ትሑት መሪዎች አገር-ፈለቅ ሊቃውንቶቻቸውን መስማት፣ ምክሮችን ሰብስቦ መመዘን፣ ነባርነትን አክብሮ ዘመኑን የሚዋጁ ፈጠራዎችን በመጨመር ይገለጻሉ እንጂ የሐሳብ ሞኖፖሊ ይገባኛል በሚል ግብዝነት እንደ ሤረኞቹ አይዘምቱም።
ትዕቢተኞች ሌላው መለያቸው ሕዝብን እንደ ግል እቃቸው ለመሥራት በራሳቸው ብሔራውያን ሊቃውንት ባልተመከሩባቸው ዕሳቤዎች ለማጥመቅ መጣራቸው ነው። ምናልባትም ዕውቀት ብለው የሚይዙትና የሚያምኑበት ጉዳይ ባላስተዋሉት መንገድ ከአማራነት እና ኢትዮጵያዊነት የሚቃረንና ጠላት ያሳደረባቸው ሊሆን እንደሚችል ባለመገመት አማራጭን ባለመቀበል ከዕውቀት ሕግ ጋር ሲጋጩ ይገኛሉ። በአዋቂነት ሽፋን የጠላት ማኅደር የሆኑ ግብዝና አላዋቂነታቸውን ለማወቅ ስንኳ የምትጠቅም ለሰው ልጆች ሁሉ በእግዚአብሔር የተሰጠችን ጥቂት የዕውቀት እርሾን በራስ ወዳድነታቸው ጨለማ ስለሚሰውሩት ማንንም አያዳምጡም። በዚህ መንገድ የሚጎዱ መሪዎች መታወቂያቸው በማን አኽሎኝነት ትዕቢት መደንቆር ነው። ለዚህ ሕያው ምሳሌ የሚሆኑን ጠ/ሚ አብይ አህመድ አሊና ጭፍን አገልጋዮቹ ናቸው። አብይ አህመድ የማያውቀውን እና የማይረዳውን፣ በጥቂት ንባብና በጆሮ ጠገብ የሚገኙ ጽንሰ ዐሳቦችን ሁሉ ከራሱ ያፈለቀ አድርጎ ራሱን ከማሳመን አልፎ ሌሎች አያውቁትም በሚል ትዕቢትና ግብዝነት ራሱን የጦር ጄኔራሎች፣ የአርቲስቶች፣ የሀኪሞች፣ የሚኒስትሮች፣ የሼኪዎችና ጳጳሳት አሠልጣኝ ያደርጋል። መስማትን የሚሰማው ከባእዳን ገንዘብ ለጋሾች ብቻ ሲሆን ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ መምህርና ሊቅ እንደሆነ ያምናል። የፖለቲካ መሪነት ሥልጣኑ የዕውቀትና የጥበብ ብቸኛ ቁንጮ እንዳደረገው ይሰማዋል።
እንዲህ ዓይነት አላዋቂነትን በዕውቀትነት የሚያስተረጉመው ክፉ በሽታ ትዕቢት ነው። ትዕቢት የጥፋትን በሮች የምትከፍት፣ የሰይጣን በር መክፈቻ መሆኗን የሚያውቁ የአማራነትና የኢትዮጵያዊነት ወዳጆች ሁሉ ለመስዋዕትነት የተሰለፉልን ጀግኖቻችንን የሚመሩ ወገኖቻችንን በምክርና ተግሣጽ ጥበቃ ሊያደርጉላቸው ይገባል።
ትህትና የራቃቸው የፖለቲካና የጦር መሪዎች ሕዝብን እንደ ዕቃ የሚቆጥሩ ናቸው። ይህን በሕወሓትና ኦነግ፣ በኢሕአፓና ደርግ አገዛዝ እናውቀዋለን። ሕዝቡን ለማዳን፣ ነጻ ለማውጣት፣ ለማበልጽግ፣ የራሱን ዕድል በራሱ እንዲወስን ወዘተ በሚሉ ያልተብራሩና ከአገራዊ መሠረታዊ እምነቶችና ባህሎች ውስጥ ከመነጩ ዕሤቶች ጋር ያልተገናዘቡ ግልብ ዕሳቤዎችን ከባዕዳን በመዋስ ሕዝቡን ይገድላሉ፣ ያገዳድላሉ፣ ያሳድዳሉ፣ ያፈናቅላሉ፣ ይከፋፍላሉ፣ በሐሰት የጥላቻ ትርክት ይመርዛሉ። ግራ የተጋባ መንጋ እየፈጠሩ በመሪነት ስም ይነዱታል። ካለፈው ታሪክ መማር ሲገባን በፋኖ እንዲደገም መፍቀድ ራስን እንደ ማጥፋት ይቆጠራል። ማንኛውም ውጭ-ገብ ርዕዮት ላይ የተመሠረቱ ንቅናቄዎችና ለውጦች ሁሉ በዋናነት ዒላማ የሚያደርጉት ነባርነትን ነው። ለምሳሌ ከፋኖ ውጭ ያሉት ከ60ዎቹ ጀምሮ ያየናቸው ንቅናቄዎችና የለውጥ ጥረቶች ዒላማ ካደረጓቸው መካከል ዋና ዋናዎቹ፦
● የኦርቶዶክስ ክርስትናን እስከነ ታሪኳ፣ ትውፊቷ፣ ዶግማዎቿ፣ አሻራዎቿ፣ ንብረቶቿ እና ተከታዮቿ፤
● በሁለተኛ ደረጃ ኦርቶዶክሳዊነት አይሎ ይገለጽበታል የሚሉትን ሕዝብ የማንነት መሠረት “አማራነትን”፤
● በሦስተኛ ደረጃ ነባር እሴቶችንና ባህሎችን፣ ነባር እስልምናን፣ ነባር የቦረና ገዳን፣ የሶማሌና የአፋር፣ የራያና የእንታሎ ዋጅራት፣ የአክሱም፣ የኢሳና ጉርጓን ሥነ-መንግሥትና የፍትሕ ሥርዓቶችን፣ የፍትሐ ነገሥት የፍትሕ ሥርዓትን፣ የክብረ-ነገሥት ትርክትን ወዘተ ናቸው።
ትዕቢት ከነባርነት ጋር የሚጋጭ የናርሲሲስቶችና የአላዋቂዎች ራስን የማግነኛ ተመራጭ መሣሪያ ነው። ነባርነትን በመቅበር የግልና የቡድን ዕሳቤዎችንና ሥርዓቶችን አማራጭ አልባ ማድረግና የሐሳቡ አመንጭዎችን ምትክ-የለሽ መሲሆች ለማድረግ ቀላል ስለሚሆን ነው። በዚህ መንገድ ትዕቢተኞች አእምሮውን የተቆጣጠሩት ትውልድ ለጭፍን መንጋነትና ለአምባ ገነኖች መጠቀሚያነት የተመቻቸ የማይጠይቅ መሣሪያ ይሆናል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰቱት ነባር ንቅናቄዎች መሠረታዊ ርእዮታቸው የመነጨው በእምዬ ምኒሊክ መሪነት በአድዋ ድል ከቆሰሉትና ቂም ቋጥረው “ነባርነትን መስበር፣ ኢትዮጵያን መበቀል ነው” ብለው ከሚያምኑ ባዕዳን መሆኑን በሰፊው አንስተናል። ዛሬም ይህን የጥፋት ሂደት ለማስቆም የፋነነውን የአማራ ወጣት ተጋድሎ በሤራ ጠምዝዞ የአማራን የዘመናት የአሸናፊነት መሠረቶች በማጣጣል በአዲስ፣ ጠባብ፣ አጥፊ እሴቶች በመተካት አማራነትን በአማራ ለማጥፋት ፋኖነትን ለጠላቶቻችን መጠቀሚያ ሊያውሉ የሚፈልጉ አካሄዶችን ያለ ይሉኝታና ማመንታት ተከታትሎ መከላከል የሁሉ ኃላፊነት ነው።
እውነትን፣ ማሰብን የሚፈሩና በጭፍን መከተል የሚቀላቸው አንዳንድ የዋህና ሳያስቡ በጎጠኝነት ወይንም በዝምድና ቅርርቦሽ ሰውን የሚከተሉ ወገኖቻችን “የአማራን ትግል ለአማራ ተዉለት! አሁን ነቅተናልና ማንንም አንሰማም! ሐሳቡ የመነጨው ከእገሌ ጎሣና መንደር ስለሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃልም ቢሆን በእነርሱ ሲነገር ተቀባይነት የለውም! እገሌ ብቸኛ መሪያችን ስለሆነ ስሕተቱም ጥፋቱም ልማት ነው! ወዘ.ተ.” የሚሉ ድምጾች በማኅበራዊ ሚዲያው ይመላለሳሉ።
ለአማራ እምነቶች፣ ለአማራ ታሪካዊ ሀገር ባለቤትነት፣ ታሪክና ነባር ትርክት እንዲሁም ለአሸናፊ ነባር እሴቶች የጠላትነት መንፈስ ያላቸው ሰዎች ለመኖራቸው ምልክቶቹ ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ አሉ። ከእነዚህ ምልክቶች መካከል ዋና ዋናዎቹን ለመጠቆም፦
1) የአማራ ፋኖ አድነት እንዳይሳካ በቴክኒክ፣ መተማመን እንዳይኖር የተለያዩ የሐሰት መረጃዎችን በፋኖና በደጋፊዎች መካከል በማሰራጨት፣ በማንአኽሎኝነት፣ ከፋፍሎ በማነጋገር፣ ድጋፍ በመስጠትና መንሳት ስልት የሚንቀሳቀሱና በጎጥ ማንነት አማራን ለያይቶ በመምረጥ በአገርና በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የሤራ መረብ ዘርግተው የአማራን ሙሉ አንድነትና ትብብር ከውስጥ በሤራ በማፍረስ የሚሠሩ ሰዎች መኖር፤
2) ከኦነጋውያንና ሕወሓታውያን ባህልን በመቅሰም ሐሰትንና የተሳሳተ መረጃን በአንድ ማዕከል ፈብርከው የአማራን እሴቶች የሚያጣጥሉ፤ አማራ የትግል ወዳጆች እንዳይኖሩት ግብ አስቀምጠው የትግሉን ደጋፊዎች ሁሉ ጥርጣሬ ውስጥ የሚያስገቡ፤ ሤራቸውን ሊያጋልጥ የሚችል ማንኛውንም ግለሰብና ቡድን ቀድመው ስም የማጥፋት ዘመቻ የሚያደርጉ መታየታቸው፤
3) የአማራ ትግል ወጤታማ የሚሆነው እንደ ሕወሓታውያንና ኦነጋውያን በፋሽስታዊ ዘር አጥፊ፣ ርስት ነጣቂና ታሪክ አጠልሺ አካሄድ የተሰማሩ፣ ብሔርተኝነት ወደ አስፈሪና የተጠላ ዘረኝነት ብሎም ጠባብ ጎጠኝነት እንዲያሽቆለቁል የሚሠሩ፣ ሃይማኖት ታሪክና ባህል የማያስፈልገው ልሙጥ ሴኩላሪዝም፣ ሆድና ስሌት እንጂ ልብና መንፈስ የማያሻቸው ኢሰብአዊ ፍጡራን በጭፍን መንጋነት የሚደራጁበት፣ አዲስ አማራነትን የሚሰብኩ የሞሉበት መሆኑ፤
4) የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ስም፣ ምልክት እና እሴቶች ላይ የተከፈተውን ግልጽ ሀገር አቀፍ ጥቃት ፈጽሞ ትኩረት እንዳያገኝና ኦርቶዶክሳውያን ለመሰባሰብ የጎሣ ድንበር ዘለል ንቅናቄ ማድረጋቸው “የአማራ ትግል ጠላት ነው” ብለው ፕሮፓጋንዳ የሚያካሄዱ መኖራቸው፤
5) ግራ ቀኛቸውን የማያውቁና እንደ ማሽን ያስጨበጧቸው፣ መልሰው ከማስተጋባት ውጭ ለውይይት የሚያበቃ ፋይዳ ያለው ሐሳብ የማያመነጩ ሕሊና አልባ ምላሶችን በማስተባበር ሐሳብ ባላቸው ቅን ወገኖች ላይ የሚያዘምቱ መበራከታቸው፤
6) በመረጃ ላይ ተመሥርቶ በሚሰጣቸው ትንበያ ራሳቸውን እንደ ብቁ መንፈሳዊ ነቢይ የሚያስቆጥሩ፣ አጭበርባሪ ጠንቋዮች በዘረጉት የሐሜትና የወሬ አመላላሾች ድጋፍ ለአስተሳሰባቸውና ግባቸው እንቅፋት ይሆኑብናል ብለው የሚያስቡትን ጠቃሚ አማራጮች ሁሉ እንዳይሰማ የሚከላከሉ፤
የመሳሰሉትን ጎጂ ዝንባሌዎች ----- ወደ ሰፊው የአማራ ሕዝብና ራሱን ለመስዋእትነት ወዳቀረበው የአማራ ጀግና ወጣት በማድረስ ትውልዱን ብዥታ ውስጥ እንዳያስገቡት እጅግ ያሠጋል። ሥጋቱንም የሚጋራ ቅን ሰውና ለመልካም ዓላማ የተደራጀ ቡድን ሁሉ ጥፋቱን ለመከላከል መጣር ይኖርበታል።
በፋኖ ውስጥ ለትግሉ ውጤታማነት እንቅፋት የሚሆኑ አሉታዊ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎችና ቡድኖች ፍላጎት ምንድን ነው?
እነዚህ ከላይ ያነሳናቸው አሉታዊ ዝንባሌዎች የሚታዩባቸው ሰዎች ምናልባትም፡-
● አማራንና እሴቶቹን፣ ነባር እምነቶችና ባህሎችን ከሰባ ዓመታት በላይ ካጠቁት እና በክህደት ፍልስፍናና ርዕዮት ከሚመሩት አካላት ጋር ግንኙነት ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ መገመት ለመፍትሔ ፍለጋ ቁልፍ ጉዳይ ይሆናል።
● ሁለተኛው ከግምት ማስገባት ያለብን ስልት፣ ሤራ፣ አስተሳሰብና ርዕዮትን ከአማራነት ጠላቶች በመዋስ ለአማራ ትግል መፋጠን፣ ለግል ጥቅም መሳካትም ይጠቅማል ብለው በማሰብ ወይንም በወዳጅ መሳይ ጠላቶች በመመከር ያመኑ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ።
● በሌላ በኩል ነባር አማራነት ለ50 ዓመታት የጠለሸ፣ የሚያሳቅቅ እንጂ የማያኮራ እሴት ሆኗል፤ ኋላ ቀርና የጃጀ ውድቅ መንገድ ነው የሚል ሥጋት፤ ባእዳን የሚያጨበጭቡለትና የሚደግፉትን ዕሤት፣ ስልት፣ አነጋገር፣ እምነት/ኢአማኒነት መምረጥ አማራን ከህልውና አደጋ ለመታደግ ቀላሉ መንገድ ነው ብለውም የደመደሙ አእምሮዎች ሊሆኑ ይችላሉ።
እነዚህ ወገኖች ከባዕድ ተልእኮ ከሌላቸው ወይንም ድንቁርና ካልበረታባቸው በስተቀር ከንግግሮቻቸው እንደምንመለከተው ያለ ምክንያት ተነስተው ነባር ነገሮችን ሁሉ እንደ ብልጽግና ወንጌሉ መንግሥት "ያረጀ ያፈጀ ትርክት፣ የእግዚአብሔርን ሰሎሞናዊ ቅባት እና እግዚአብሔርን አንፈልግም፣ ---- የምንፈልገው አማራንና የአማራን እግዚአብሔር ነው።" ወደማለት ደፋርና እጅግ አደገኛ በነገረ መለኮት፣ በአመክንዮ፣ በፖለቲካዊ ስሌት፣ በባህል ሁሉ የሚያስወግዝ ነውረኛ አቋም እስከ መግለጽ አያሽቆለቆሉም ነበር።
--- እናም የትግሉ መሪዎችና ደጋፊዎች በሰከነ መንገድ መምከርና ለትግሉ ዕሳቤዎች ጥበቃ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ታጋዩን ዶላርና ፕሮፓጋንዳ መመገብ ብቻ ትግሉን ውጤታማ አያደርገውም።
ትግሉን ዘገምተኛና ከተነሳበት ቀዳሚ ግቡ ውጭ ሊያደርጉት የሚያስቡ ሰዎች ንግግርና ድርጊት እንዴት ይታወቃል?
በእርግጥ የአንዳንድ ተናጋሪዎች ፍላጎት የአማራ ትግል ውስጥ በሚሳተፉ ሰዎች የማኅበራዊ ሚዲያ መልእክቶች በኩል እያፈተለከ ይገለጣል። እና እርሱን በማጤን መገመት ይቻላል። በተለይ የማኅበራዊ ሚዲያ መልእክቶች በዘመቻና በተቀናጅ መልኩ ሲደረጉ ከግለሰብእ አስተያየትነት ወደ ቡድን አጀንዳ አራማጅነት አዘንብለው ይጋለጣሉ።
በቡድንና በግል ጠባብ ፍላጎት ታጥረው አፍራሽ እና ድብቅ አጀንዳ የሚያራምዱ ጥቂት ፋኖ ውስጥ ብልጭ ድርግም የሚሉ ዕሳቤዎች የሚመነጩት “ፋኖ ነኝ” ባይ የፋኖነት እሴት ተቃራኒ እሴትና ግብ ባላቸው እና ሥነ ልቦናቸው በሕወሓታዊና ኦነጋዊ የቁማርና የሤራ ባህል የተመረዙ፣ አማራጭ ስልት የማይታያቸው፣ በትዕቢትና በብልጣብልጥነት የማሰብና የማዳመጥ አቅማቸውን ሁሉ ለአሉታዊነት የሚጠቀሙ ረቂቃን እኩያን ናቸው። የእነዚህ ገጸ ባሕርያት መገለጫዎችን ከተግባራዊ ልምዶች አንጻር ስንመለከትው፦
1) የአማራን ሕዝብ ጨፍለቀው በመያዝ አእምሮው ማሰብ አቁሞ እነርሱን ብቻ እየሰማ ወደ ላኩት እንዲሄድ ማድረግ የሚመኙ ናቸው። ይህን ደግሞ የተማሩት ከሕወሓትና ኦነግ፣ እንዲሁም ከማርክሳዊ ርእዮተ ዓለም አቀንቃኝ ንቅናቄዎች ነው።
2) ሁለቱ የኢትዮጵያዊነት ጠላቶች ማለትም ሕወሓትና ኦነጋውያን መነሻቸው ዘረኝነት ነው፤ ማታገያቸው አማራንና ነባር እሴቶችን ጠላት በማድረግ ባልተብራራ አዲሥነት ትውልዱን ከነባር የማንነት ንዑስና የጋራ ኢትዮጵያዊ እሴቶቹ ነቅሎ ባዛኝና ተነጂ ማድረግ ስልታቸው ነው።
3) የአማራን የህልውና ትግል ያቆሸሹ እኩይ ዘረኛ ድርጅቶች ለ50 ዓመታት ተከታዮቻቸውን ወደ ማሽንነት እንደቀየሩትና የጥፋት መሣሪያ እንዳደረጉት ሁሉ እነዚህ በፋኖ መካከል በፋኖ ስም ተገኝተው ከፋኖነት ዓላማ ውጭ ሕዝቡን ሊጋልቡት የሚሹ ሰዎች የሚገፋቸው ኃይል የሥልጣን ስግብግብነት በመሆኑ ስሕተታቸው የሚያስከትለውን አደጋ ለመመዘን አቅመ ቢስ መሆናቸውና በጠላት አጀንዳ መጠለፋቸው ሊሆን ይችላል።
4) ምናልባትም በሥነ ልቦና ደረጃ ከራሳቸው ውጭ እንኳንስ የፖለቲካና የትግል አማራጭ ሐሳቦችን ሊያመነጩ ቀርቶ፣ የኦርቶዶክሳውያንን ራስን ከሥርዓታዊ ጥቃት ለመከላከል የሚያደርጉትን ጎሣ ዘለል ንቅናቄ ያለ ሐፍረት "ሞዓ ተዋህዶ ግብረ ኃይል የአማራ ሕዝብ ትግል ጠላት ነው" እስከ ማለት የሚያስደፍራቸው፣ የሐሰት አምራችነትና አከፋፋይነት ከሤረኞችና ቁማርተኞች ተዋርሷቸው ሊሆን ይችላል።
5) ምናልባትም ባለፉት 50 ዘመናት “ለብሔራችን፣ ለሕዝባችን፣ ለጭቁኑ፣ አደራ ለሰጠን፣ ለብልጽግናችን፣ ለሰላማችን፣ ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓታችን፣ ለክልላችን ወ.ዘ.ተ” በማለት ሕዝብ እያሳሳቱ በማስከተልና መስዋእትነት በማስከፈል በተግባር ግን "ለግል ፍላጎቴ" የምትለዋን እውነት ሰውረው "የትግራይ ሕዝብ፣ የኦሮሞ ሕዝብ፣ የእገሌ ሕዝብ ጥቅም፣ ጥያቄ ወዘተ" እያሉ በሕዝብ ስም የሕዝብ ልጆችን ደም በግጭትና በጦርነት ውስጥ እንደሚያኖሩት የጎሣ ሤረኛ ነጻ አውጭዎች አሁንም "የአማራ ሕዝብ ትግል ጠላት" ብለው ፈርጀው የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት ይሆናል።
6) ለእኔ አማራነትን (ደምና አጥንት አላልኩም፣ ባንዳን ሳልጨምር) ማወቅ የምፈልገው በፈሪሃ እግዚአብሔር፣ በሰብአዊነት፣ በአገር ወዳድነት፣ በጀግንነት፣ በእውነተኝነት፣ ዘረኝነትን በመጸየፍ ብቻ ሳይሆን በሕይወቱ ዋጋ ከፍሎ የተዋጋላቸው እሴቶቹ ሲሆኑ ምስክሮቹ ፍትሕን፣ አማኝነትን፣ ፍቅርንና አንድነትን በተግባር ያሳየ መሆኑ ናቸው።
7) የኦርቶዶክስ ክርስትና እና በክርስትናው አስተምህሮ 3 ሺ ዘመን የተሻገረውን የአማራና የሌሎቹም ማኅበረሰቦች የሥነ መንግሥት፣ የሥነ ማኅበርና የአገር ትርጉም ሁሉን በመቃረን --- ለራሳቸው ጠባብ ግብ አዲስ መንጋ ተከታይ ለማልማት መሞከር --- የአሸናፊ እሴቶቹ ጠላትነት ብቻ ሳይሆን ከአሁኑ የከፋ የህልውና አደጋ የሚያስከትል ስሑትነት ነው።
በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ከተዘዋወሩት የአንዳንዶቹ ሰዎች የበር ዘግተናል መልእክቶች እንደምንረዳው የአማራነትን እሴቶች በመቃረን እና ከመስገብገባቸው ጥልቀት የተነሳ "ጣልቃ አትግቡብን፣ ሕዝቡ እኔ ብቻ እና ብቻ ስለሆንን ሌላ አማራጭ ዕሳቤዎች ወደ ጆሮው አይድረሱ" ማለት ትርጉሙ አሉታዊ ነው። በሌላ አነጋገር የህልውና ትግል ውጤት መደምደሚያ “የእኔ የግል ፍላጎቴ ተሟልቶ ለአማራ ሕዝብ የመስዋእትነቱ ዋጋ ከዚያ የሚተርፈው እንዲሆን እበይናለሁ” በሚል ትዕቢት የተያዘ አእምሮ ውጤት ወይንም የተላላኪነት ስውር አጀንዳን በሥልጣን የማስፈጸም ተልእኮ ተሸካሚነት ውጤት ይመስላል። ይመርመር።
የአማራን የህልውና ትግል መሠረታዊ ግቦች የሚቃረን የሐሰተኝነትና የነባር-ጠልነት የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ለምን?
የአማራን ሕዝብ የህልውና ትግል ለግልም ይሁን በተሳሳተ ቅን የድል ስሌት ወይንም በጠላቶች ረቂቅ ምክር በመታለል ለከፍተኛ የግል ፍላጎታቸው ማርኪያነት ጠልፈው ወደ ጸረ ኦርቶዶክስ ክርስትናና ረዥም የሥነ መግሥት ታሪክ ጠላትነት ለመቀየር ልባቸውን ያዘነበሉ ጥቂት ግለሰቦች ከሠራዊቱ ጀርባ እንዳሉ አንዳንድ ፍንጮች ይታያሉ። እነዚህ ጥቂት ሰዎች ከአንድ ምዕራባዊ አገር ዲፕሎማት ጋር ተነጋግረው የሚከተለውን ቃል ኪዳን እንደተቀበሉም ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ የሕዝብ መገፋት የሚያንገበግባቸው የመሥሪያ ቤቱ ምንጮች ገልፀውልኛል። የገቡት ቃል ኪዳን ሕዝቡን ሳይሆን እኛን ለሥልጣን በሚያበቃ መንገድ እርዱን የሚል ሲሆን በበኩላቸው እሺ እንፈጽማለን ብለው የተቀበሉት ቅድመ ሁኔታ ፭ ነው ብለን እንገምታለን፤ ሁለቱን ነባር እምነቶችና የአማራን ግዛት ለሕወሓት የመስጠቱ ጉዳይ ግን እርግጥ ነው።
እነዚህ የቃል ኪዳን ነጥቦች፦
፩ኛ) "በፕሪቶሪያው የብልጽግና ወንጌል መንግሥት እና የአገር መከራ ቋት ፈልፋዩ ሕወሓት መካከል በተደረገው ስምምነት መሠረት:- ወልቃይትንና ራያን ለሕወሓት አሳልፈን ስንሰጥ ላትቃወሙ ቃል ግቡልን፣ ሕወሓት ግዛቶቹን ለማስመለስ በአማራ ዞኖች ላይ ወረራ የምትፈጽም ከሆነ እነሆ እኛ "አንተኩስም" ብላችሁ ከወዲሁ አቋማችሁን አሳውቁን፤
፪ኛ) በምሥራቅ አፍሪካ የክርስትና ሃይማኖት ጽንፈኝነት የመፈጠር ሥጋት ስላለብን የፋኖ ትግል አምላክ-የለሽ ሴኩላር ፖለቲካዊ ዕሳቤ እንደሆነ፣ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን እምነት እንደማትደግፉ፣ ምልክቶቿንም በሰውነታችሁ ላይ እንደማታደርጉ፣ ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ጋር ትግላችሁን በመነጣጠልና የክርስቲያን ጥቃቶችን ሁሉ በምንም መልኩ ላለመጥቀስ ቃል ግቡ፤
፫ኛ) ከኢትዮጵያዊነት ነባር ትርክቶች በተለይ የሰሎሞንና የዛጉዌ እንዲሁም ከቀዳማዊ ምኒልክ ጀምሮ የሚነገረውን ታሪክ አለማንሳት ብቻ ሳይሆን ትውልዱ እንዲቃወመው ለማድረግ ቃል ግቡ፣
፬ኛ) የአማራ የህልውና ትግል በአማራ ክልል እንዲወሰን፣ አማራነትም ከእሴትና ታሪክ ተነጥሎ ደምና አጥንት ወይንም ራሱን የሕወሓትና የኦነግ አቻ እንጂ ወደ አሰባሳቢ እሴቶች ለምሳሌ፡- ክብረ-ሰብእ፣ ፍትሕ፣ እኩልነት፣ ክልላዊነትንና ጎጠኝነትን ወደ ሀገራዊነት እንዳይቀየር፣ እንዲሁም አጀንዳውን ከአማራ ክልል ውጭ ስለሚኖሩት አማራ እንዳታሳድጉት ቃል ግቡልን፣ -------፡፡
በዚህ ከተስማማችሁ በሳምንታት ውስጥ ሠራዊቱ ከክልሉ እንዲወጣላችሁ እናደርጋለን። ሕዝቡ እንዲቀበላችሁ ሚዲያዎቻችሁን አቅም ገንብተን ገፅታችሁን ከፍ እናደርጋለን። አቢይ አህመድ በአጭር ጊዜ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲያገኝ እንዳደረግነው ለእናንተም እናደርጋለን።
በዚህ ድብቅ ውል መሠረት ቃላቸውን የሰጡት ወገኖች የፕሮፓጋንዳ ማሽናቸውን አንቀሳቅሰው መርዝ መርጨት ከመጀመራቸውም በላይ ለውሉ መገዛታቸውን መደበቅ ላለመቻላቸው የሚከተሉት ምልክቶች ማሳያ ናቸው፦
⇒ መስቀልና ዳዊታቸውን እያሳዩ ክላሽ አንግተው በየማኅበራዊ ሚዲያው ሲገሸሩ የነበሩ፣ ከሎይታ አድርገው በየሸንተረሩ ሰላት ሲሰግዱ ይቀረጹ የነበሩ አንዳንድ የትግል አመራርና ፕሮፓጋንዲስቶች ቀኝ ወደ ኋላ ዙረው መስቀላቸውንና የሰላት ከሊማቸውን ደብቀዋል፡፡ ከዚያም አልፈው “ከሃይማኖት ንጹሕ የሆነ፣ ሴኩላር ትግል ነው የምናካሂደው” የሚል በቅጥረኛ ሚዲያዎቻቸው በኩል ለሚታዘዟቸው አካላት መተማመኛ ማስነገራቸው፤
⇒ ለትግሉ ውጤታማነትና ለአማራ-ዐቀፍ የወል ግቦች እና ጥቅሞች መከበር ቅድመ ሁኔታቸው ምን እንደሆነ ለሚሠዋው ሠራዊትና ሕዝብ ግልጽ ያልተደረገ ስምምነት ከሕወሓት ጋር እንዳላቸው የሚያሳብቅ "በሕወሓት ላይ አንተኩስም" በሚል መልእክት ገልጠዋል፤ የህልውና አደጋ መንስኤ የሆኑትን ሕገ መንግሥት፣ ክልል፣ ትርክት ከፈበረከውና የባእዳን መሣሪያ ከሆነው ሕወሓት ጋር የሚደረግ ትብብር አስቀድሞ ለሕዝቡ ግልጽ መደረግና ስምምነት ላይ መደረስ ይኖርበታል፤
⇒ ስለ ወለቃይትና ራያ ጉዳይ በፕሮፓጋንዳ ማሽናቸው ሁሉ እንዳይነሳ በማድረግ በሌሎች ዕለታዊና የግል ሰብእና ግንባታ ወይንም ሌላውን በማጠልሸት ላይ ማተኮራቸውን ስናይ፣ ከህልውና ትግል የሚበልጥባቸው ግብና ፍላጎት ያላቸው መሪዎችና ደጋፊዎች ሊኖሩ ይችላሉ የሚለውን ግምት ማጣጣል እንዳንችል ያስገድደናል፤
⇒ በኦርቶዶክስ ክርስትና እና ተያያዥነት በነበራቸው ሥርወ መንግሥታት ታሪክ ላይ "ያረጀ ያፈጀ ትርክት አንፈልግም፣ መንግሥትም የሰሎሞን እግዚአብሔር የሚቀባው ሳይሆን የአማራ ብቻ የሆነ፣ እና የአማራ እግዚአብሔርን ብቻ ነው የምንፈልገው" በማለት ከአመክንዮአዊ ተጠየቅ ውጭ፣ የአንድ አምላክ ህልውናን ክዶ በማባዛት የአማራን የህልውና ትግል አምላክ-የለሽ፣ ታሪክና እሴት የለሽ፣ ግዕዛን እና ሰብአዊ አእምሮ የሌላቸው ሰዎች ለመስዋእትነት የተሰለፉለት፤ የፍትሕ ትርጉም የማያውቅ ሕዝብን ከሥጋ ሞት አድኖ ለመግዛት እንደተሰለፈ አካል ሲናገሩ መሰማታቸው “የትግሉን መነሻ ዓላማ የካዱ” ሠርጎ ገቦች ይኖሩ ይሆን ለማለት ያስገድዳል፤
⇒ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጥቃትን የሚከከላከሉ አደረጃጀቶችንና ንቅናቄዎችን ለባእዳን በገቡት ቃል ኪዳን መሠረት እና የብልጽግና ወንጌል መንግሥት አማካሪው “ዘንዘሪጡ ሙሐዘ ሕምዝ” ተብሎ በሚታወቀው ከሀዲ ግለሰብ በተዘጋጀው "በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ጽንፈኝነትን መዋጋት" ሰነድ መሠረት "ሞዐ ተዋሕዶ ግብረ ኃይል የአማራ ትግል ጠላት ነው" በሚል ፍረጃ የሚፈርጁ አንዳንድ የፋኖ ንዑስ-ቡድን መሪዎች በተከፋይነትና ሕሊና ቢስ ሎሌዎች የማኅበራዊ ሚዲያ ተስፈኞች በኩል ዘመቻ መክፈታቸው፤
⇒ በመላው ሀገሪቱም ሆነ በአማራ ክልል በአብነት ትምህርት መምህራንና ተማሪዎች፣ በካህናት፣ በገዳማት፣ በአድባራት የሚፈጸሙ የአገዛዙ ጥቃቶች በቤተ ክርስቲያን ላይ የተቃጣ ተደርጎ እንዳይነገር ለማዲያዎቻቸው አቅጣጫ በመስጠት በዝምታ እንዲያልፉት፣ መዘገብ ግድ ከሆነም ሃይማኖታቸው እንዳይጠቀስ፣ ከክልሉ ውጭ የሚገኙ ክርስቲያኖች ጭፍጭፋ እንዳይዘገብ ማድረጋቸው፤
ይህ ሁሉ ክህደት ከአማራነት የተቃረነ መሆኑ በአማራ ስም የሚንቀሳቀሱ የአማራ እሴቶችና ፍላጎቶች እንቅፋት የሆኑ ሰብእናዎች በትግሉ መካከል ተጽዕኖ እየፈጠሩ መሆናቸውን እንድንገምትና ድምጻችንን ሳይረፍድ እንድናሰማ ይጋብዘናል።
ለክቡር ዓላማ ነፍሱን የሰጠን የፋኖ ሠራዊት ከዓላማውና ከዕሤቱ የሚቃረኑ ጮሌዎች እንዴት ሊያታልሉት ቻሉ?
ዘመናችን የችኮላ፣ የስሜትና የጊዜአዊ ጥቅም ማርኪያ የሚነዳው መሆኑ የታወቀ ነው። በዚያ ላይ ፍልስፍና፣ ርእይ፣ ሕሊና፣ ፈሪሃ እግዚአብሔርና ርቱዕነት እንግዳ እየሆኑ በምትኩ ጎሣ፣ የግል ጀግና፣ በቀል፣ ያለ ድካም ፍሬ ፍለጋ ቦታ ይዘዋል።
አብይ አህመድ ይህን የትውልድ ስሜታዊነትና ቅዠታዊ ተስፈኝነት ተገንዝቦ ከ120 ሚሊዮን ሕዝብ መካከል 90 በመቶ የሚያክለውን አደንዝዞ ሥልጣኑን ካደላደለ በኋላ ጭፍጨፋና ማፈናቀል ሲጀምር ከ90% ድንዝዝ መካከል ከ20% የማይበልጥ ሕዝብ ለዚያውም በቀጥታ ከተወጋው መካከል ጥርጣሬ አሳድሮ መቃወም ጀመረ። በዚሁ መሠረት በፋኖ መካከል ልታይ ልታይ የሚሉትን በማደንዘዝ የፋኖን ግብና ዓላማ ብቻ ሳይሆን የፋኖነትን መገለጫዎች ያረከሱ ግለሰቦች በፋኖ መካከል ሠራዊቱን አንድ እንዳይሆን ከመከላከል ጀምረው የነቁትን እስከ መግደል ደረሱ። አሁንም ድንዛዜው መቀጠሉና የኢትዮጵያ ሕዝብ አልፈወስ ያለው ከቤተ ክርስቲያን ዓውደ ምሕረት እስከ ጦርሜዳ በእልልታና ጭብጨባ መንጋነት የሚነዳ ትውልድ መብዛቱ ያመጣው ችግር ይመስላል። ለምን ነፍሱን ለክቡር ዓላማ በሰጠ ሠራዊት መካከል እንዲህ ዓይነት ስብእናዎች በተጽዕኖ መፍጠር ደረጃ ተገኙ? ብሎ መጠየቅና መልስ መስጠት የአማራ ሕዝብ ዕዳ ነው። እንደ እኔ አመለካከት ከሆነ መልሱ፡-
1) ጥቂት የፋኖ ሰዎች አንድም በቅንነትና በግንዛቤ እጥረት ለትግሉ ድጋፍ ለማግኘት፤
2) አንድም በግል የሰነቁት ጠባብ የሥልጣን ጥም አሳውሯቸው የአማራን ወጣቶች ደም ከህልውና ትግሉ ታላቅ ግብ ለወረደ ርካሸ ፍላጎታቸው ለማዋል፤
3) አንድም ቀድሞውኑ በረቀቀ ስልት ወደ ትግሉ የገቡና በአማራ ስም ተሰይመው የአማራን ሕዝብ ከክልል፣ ከዘረኝነት እና ከጠባብነት ልቆና ርቆ መሄድ፣ በታሪካዊ ጠላቶቹ ከተጠመደለት የጎሣና ሃይማኖት ርኲቻ አምልጦ ወደ ክብረ-ሰብእ፣ ታሪካዊነት፣ አገር ዐቀፋዊነት እንዳያድግ፣ ፍትሕና እውነት ላይ መቆም እንዳይችል ለማጨናገፍና ለማልከስከስ ተልእኮ የተቀበሉ፤
4) አንድም በዓድዋም ይሁን በአርበኝነት ዘመን የታየው የአልገዛም ባይነት፣ የሰብአዊ ልዕልና ምንጭ ናት ብለው የሚያምኑትን ኦርቶዶክስ ክርስትናን ከአማራ ሕዝብ ልብና አእምሮ በመነጠል እና ሕወሓትና ኦነግ ኦሮሙማ በተከታዮቻቸው ላይ እንደፈፀሙት ያለ ወንጀል በአማራ ሕዝብ ላይ ለመፈጸም የቃጡ ሰዎች፤
5) ሃይማኖት፣ ባህል፣ ታሪክ እና ነባር ዕውቀትን መሠረት ያደረገ ተጋድሎን፣ ሕዝቡን አደንዝዘን፣ ጭፍን፣ ተከታይ፣ የማያስብ መንጋ፣ እና መሣሪያችን ልናደርገው፣ ውጤት እንዳያገኝ ማድረግ አንችልም በሚል ሰይጣናዊ ስሌት ተመርተው ሊሆን ይችላል።
በአጭሩ ሕዝብን ከእምነት፣ ከነበረ ባህሉ በመንቀል ወደ ተራ አምላክና ሕሊና የለሽ ተከታይነት ለማውረድ የሕወሓትንና የኦነጋውያንን ርዕዮት መቅዳት ላይ የተመሠረተ ዕሳቤ ይመስለኛል። እንዲህ ዓይነት አገሩንም፣ እምነቱንም፣ ሰንደቅ ዓላማውንም፣ ታሪኩንም ጥሎ መሪዎቹ በሚያሳዩት ምናባዊ አዲስነትና አዳዲስ ሪፐብሊክ ተስፋ 50 ዓመት ሙሉ ደም ሲያፈሱና ሕዝብ ሲከፋፍሉ የኖሩትን መምሰል ፈልገው ይመስላል።
ቀደምትነቱን ጥሎ በጎሣ ነጻ አውጭዎቹ ዕድሜ ልክ ታሪክ የሚተርክ መንጋ ፈጥሮ ኢትዮጵያዊነትን፣ ኦርቶዶክሳዊነትን፣ አማራነትንና ነባርነትን ለማጥፋት ሲደግፋቸው ከሚኖረው ጠላት ጋር ተማክረው መስቀላቸውን እና የእስልምና ምልክታቸውን ደብቀው በተሰጣቸው መመሪያና የድጋፍ ተስፋ መሠረት የኦርቶዶክሳውያን ንቅናቄዎችን ማጥቃት መጀመራቸው ላኪው ያው የተለመደው የአድዋ ድል ቁስሉ የሚያሳክከው ጸረ-ኦርቶዶክስ ወገን ለመሆኑ ምንም ጥርጣሬ የለኝም።
ከጭፍን መንጋነት የተላቀቀና የማሰብ ነፃነቱን ያስከበረ ሰው ሁሉ ይህን ምልከታዬን እንድንማርበት ይሞግተው።
ነገር ግን --- እንደተለመደው፡-
የማስተዋል ጸጋችሁን ጥላችሁ በግለሰብ መመሪያ ብቻ እንደ ማሽን የምታስቡ እሥረኞች ግን፣ የምትከተሉት አካል ወንጭፍ ላይ ሆናችሁ የምትወነጨፉ ግዑዛን ጠጠሮች በመሆናችሁ ሐሳባችሁ ለመማር ከመጥቀም ይልቅ አዋራጅና ተራ ስለሆነ የሚያስቡ ነፃ አእምሮዎች እናንተ በበከላችሁት ሜዳ ላለመገኘት ይሸሹኛልና አትምጡ።
ግድ ሆኖባችሁ ከተላካችሁ ግን የሚከተሉትን የተለመዱ ጠጠሮቻችሁን እንዲቀይሩላችሁ ላኪዎቻችሁን ጠይቁና ሌላ ዓይነት ተወንጫፊ ሁኑ፦
⇒ አንተ የአባትህ ስም ዋቄ ስለሆነ ኦሮሞ ነህ፤ ኦሮሞ ከሆንክ ደግሞ ካንተ የሚገኘው ሐሳብ ጸረ አማራ ነው፤
⇒ በአማራ ትግል ምን አገባህ፣ አማራ ከእኛ ከጠጠሮቹና ከአስወንጫፊያችን ሐሳብ ውጭ አማራጭ እንዲሰማ አንፈልግም፤
⇒ እኛ ለአማራነት (ለዚያውም የሆነ ቡድን በሚነግረን ያልተጻፈ ትርጉሙ መሠረት ብቻ) የምንታገለው በአምላክ-የለሾች አዛዦቻችን ርዕዮትና መርሕ ብቻ ስለሆነ ስለ ኦርቶዶክስ ህልውና አታንሳብን፤
⇒ ሃይማኖትን መከላከል ይከፋፍለናል፣ ሃይማኖትህን በትግላችን ውስጥ አትጥቀስብን፤
⇒ አንተ የብልጽግና መንግሥት ተላላኪ ስለሆንክ ነው የሃይማኖትን ጉዳይ የምታነሳው፤
⇒ እኛ አዲስ (ምን እንደሆነ የማይታወቅ ጸረ ነባርነት ላይ የተመሠረተ አዲስነት) መንገድ ላይ የምንጓዝ ነን፤ እኛ ያረጀና ያፈጀ ትርክት፣ እምነት፣ ሥነ-መንግሥት፣ ሥርዓተ ሕዝብ አንፈልግም --- የሰሎሞን ቅባትና እግዚአብሔርን ሳይሆን የአማራን እግዚአብሔር መፍጠር እንፈልጋለን፤
⇒ አማራ እንዲመኝ፣ እንዲያስብ፣ እንዲያልም የምንበይንለት እኛ ስለሆንን ለአማራ አዲስ ሐሳብ አታምጣብን፤
⇒ ለአማራ እንዲሰዋለት የሚገባውን ግብ የምንወስንለት እኛ እና እኛ ብቻ ስለሆንን ተጨማሪ ሌላ አማራጭ ሐሳብ ማቅረብም ሆነ መተቸት "በህልውና ትግሉ ጣልቃ መግባት፣ ወዳጅነት ሳይሆን የአማራ ጠላትነት ነው" ብለናልና "ጣልቃ አትግባ"፤
⇒ ይህ ጽሑፍ አማራ መንግሥታዊ ሥልጣን እንዳይጨብጥ ከቃሊቲ እሥር ቤት እስከ ጎንደርና ሸዋ ከተዘረጋው ከሞዐ ተዋሕዶ ግብረ ኃይል የሤራ መረብ የመነጨ ነው። ---- ወዘተ ---- የሚሉ የሤራ ፕሮፓጋንዳ ልምምዳቸውን በሕወሓት ትምህርት ቤቶች ሲማሩና በሥራ ልምድም ያገኙ ሰዎች ስለሚነግሯችሁ ማሰብ የተሳናችሁ እባካችሁ አትምጡ።
የዚህ ሁሉ መስዋእትነት ዋጋ ቢስ ፕሮፓጋንዳችሁ ትግሉን በሐሳብ ልዕልና እንዲመራና እንዲጠናቀቅ ሳይሆን በማወቅሞ ሆነ ባለማወቅ አማርኛ ተናጋሪ የአቢይ አህመድ ዓይነት አጭበርባሪዎች (master cheater and mass hypnotiser) መጠቀሚያ ለማድረግ የምታሤሩ በወንድም እኅቶቻችን ጀግንነትና መስዋእትነት ጥላ ሥር የምላስና የሤራ መሰላል ተክሎ ለመንጠላጠል እንዲመች ራስን አውለው የሚያሳድሩ የሥነ ልቡና ቀውስ ያላባቸውን የምትላላኩ ለከርሳችሁ መሙላት የተጫናችሁትን ያህል እንደምትተፉ አውቄአለሁና ---- እዚያው በራሳችሁ ልክ በተሠራ ሜዳ አላዝኑ።
የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የትግሬ፣ የአፋር፣ ወዘተ ማኅበረሰቦችን ሕይወት ስለሚወስኑ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ያገባኛል። ከባዕድ ዲፕሎማት ስትመክር መካሪሀን "አያገባህም" ሳትል አጎንብሰህ ከሕዝብ ጀርባ ቃል ገብተህ ትግሉን ስታንፏቅቅው፣ "ባዕድ አያገባውም" የማለት ወኔና ሕሊና አልነበረህም። በተቃራኒው እንዴት እኔና በሃይማኖት፣ በባህል፣ በእሴትና በሰውነት፣ በአንድ አገር ልጅነትና የአንድ ተስፋ ተካፋይነት የምኖረውን ሰው "አያገባህም" ልትለኝ ቻልክ? መልሱ ተላላኪ ስለሆንክ እና "ከኦርቶዶክስ ራቅ" ተብለህ ስለታዘዝክ ነው።
እቅጩን ስነግርህ፡-
ያገባኛል!!!! አያገባኝም ብል እኔ ሰብአዊ ፍጡርነቴንና የጥምቀት ልጅነቴን በመካድ፣ ስለ እውነት መስክር ያለኝን ጌታዬን ኢየሱስ ክርስቶስን ክጄ እንደ ዘረኞቹ የጎሣ ነጻ አውጭ ከሐዲ ተከታዮች እቆጠራለሁ። አምላኬም በሰማይ ሠራዊትና በአባቱ ፊት በፍርድ ቀን ይክደኛል።
እኔም ክርስቲያን ሳልሆን መንጋና የዘመኑን ገበያ ተከትዬ የፖለቲካዊ (political correctness) ትክክለኝነት ኑፋቄ ሰለባ ሆኜአለሁ ማለት ነው። ስለ ፖለቲካዊ ትክክለኝነት ኑፋቄ ዝርዝር ለማንበብ ይህን ማስፈንጠሪያ ይከተሉ፡፡ ( https://ethiopiaorthodoxchristian.blogspot.com/2024/07/blog-post.html )
ለሚፈሰው ደምና ለአማራነት ስትሉ ቁማሩን ማቆም የምትፈልጉ እውነትን በፍቅር እንነጋገር።
ፋንታሁን ዋቄ
ነሐሴ 2017 ዓ.ም
ከጥር 27 ጀምሮ በተለያዩ የኦሮምያ ከተሞች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና ውጭ የተሾሞና በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዘው የተለዩ አካላትን ወደ ቤተ ክርስቲያን እናስገባለን ባሉ የመንግስት የጽጥታ አካላት በተትኮሰ ጥይትና ሕገ ወጡ ቡድን ባደራጃቸው ወጣቶች ተደብድበው የተገደሉና የቆሰሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህናትና ምእመናን።። 1) ሻሸመኔ ከተማ I. የተገደሉ 1. አያሌው ተረፈ ● በሻሸመኔ የደብረ አስቦ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ማህደረ ፃድቃን ሰንበት ትምህርት ቤት አባል ● ጥር 27 ዓ/ም በሻሸመኔ ከተማ በጸጥታ ሃይሉ በሚመራ የጨፍጫፊ ቡድን በደረሰበት ከፍተኛ ደብደባ ወደ ሆስፒታል ገባ ● በአላቲዮን ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገለት ሕይወቱን ማትረፍ አልተቻለም ● በ ጥር 30 2015 ዓ/ም ሰማዕትነትን ተቀብሏል 2. ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ሐረገወይን ● የሻሸመኔ ደብረ ስብሐት ቅዱስ ሚካኤል አገልጋይ የነበሩት ● በሻሸመኔ በሕገወጦች በጸጥታ አካላት በበግፍ በዱላ ተቀጥቅጠው በጭንቅላታቸው በእጅና በእግራቸው ላይ በደረሰባቸው ድብደባ በሀዋሳ ሕክምና እያሉ አርፈዋል። ● ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት ተመትተው በያኔት ሆስፒታል ሕክምና ሲደረግላቸው ቢቆዩም ሕይወታቸውን ማትረፍ አልተቻለም። ● በዛሬው ዕለት ጥር 30 2015 ዓ/ም ሰማዕትነትን ተቀብለዋል። 3. ዘማሪ ፍቃዱ ደጉ ● የቅዱስ ሚካኤል ከሣቴ ብርሃን ሰ/ትቤት አገል...
አስተያየቶች