በአማራነታቸው የተጠቁ ሰወች ‘ዜጎች’ ናቸው ወይስ ‘አማሮች’?
ሰብዐዊነት የተፈጥሮ ስጦ ነውና ሁሉም ሰው በሰውነቱ እኩል ነው። መንግስት የተፈጥሮ መብቶችን ለያንዳንዱ ግለሰብ የሚያስጠብቅበትን ህግ ታሳቢ በማድረግ በተለምዶ ‘የዜግነት መብት’ ብለን እንጠራቸዋለን። ዋናው ቁምነገሩ ሰው በተፈጥሮ
ያገኛቸውን መብቶች መንግስት የመጠበቅ ሃላፊነት አለበት የሚለው ነው፡፡ ይህን ሃላፊነት የሚወስድ መንግስት የሌላቸው ሰወች፣ ዜግነት አልባ (ስቴትለስ) ሊሆኑ ይችላሉ። በማይንማር 600000 የሚደርሱ ሮሂንጋ የሚባሉ ጎሳ አባላትን መንግስት የእኔ ዜጎች አይደሉም ስላላቸው ዜግነት አልባ ሆነዋል።
ወደሃገራችን ስንመለስ በህግ “ኢትዮጵያዊ አይደለህም” የተባለ ስለሌለ በማንነት የሚጠቁ ሰወች ችግር ለጊዜው የዜግነት ችግር አይደለም። አማራም ይሁን ትግሬ፣ አፋርም ይሁን ኦሮሞ ወዘተ ሁሉም ዜጎች በሁሉም የሃገሪቱ ቦታ ያለዐድልዎ የመኖር መብት እንዳላቸው በህገመንግስቱ ተደንግጓል። ሆኖም ወደተግባራዊነቱ ስንመለስ፣ ይህ የግለሰቦች መብት ከብሄሮች ሉዐላዊነት ስር ወድቋል። ህገመንግስቱን ተከትሎ በተደራጀው የብሄርተኝነት ርዕዮተአለም ሳቢያ፣ በአማራ ህዝብ ላይ እንደዜጋ ሳይሆን እንደአማራነት የተፈጠረ ማፈናቀልና ግድያ ተፈጥሯል። ግድያው አንድ ወቅት ብቻ የተከሰተ ሳይሆን፣ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ፣ እጅግ ዘግናኝ ግፎች የተፈጸሙበትና በበርካታ ቦታወች የተከሰተ ነው። በበደኖ፣ በአርባ ጉጉ፣ በገለምሶ፣ በጋራ ሙለታ፣ በወተር፣ በሃብሩ፣ በአጋሮ፣ በአሰቦት፣ በሸቤ፣ ወዘተ በገደል በመወርወር፣ በቢላዋ በመታረድ፣ በእሳት በመቃጠል፣ በጥይት በመደብደብ አማራ ማንነት ባላቸው ላይ አሰቃቂ ግፍ ተፈጽሟል። የአገዳደል ዘዴው ራሱ በማንኛውም ንጹህ ዜጋ ላይ የሚፈጸም የተለመደ አይነት ወንጀል አይደለም። የነፍሰጡር ሴትን ሆድ ቀዶ ልጁን በማውጣት ለእናት መስጠት፣ በእሳትና ዱላ ደብድቦ መግደል፣ ህጻናትን ማረድ፣ አስከሬን ጎዳና ላይ መጎተት የመሳሰሉ የጭካኔ ድርጊቶች እንደተፈጸሙ ማስረጃወች ያስረዳሉ። ከግድያው ጀርባ በአማራነት ላይ የተዘራውን ጥላቻ ምክንያታዊ የሚያስመስሉ የትምህርት፣ የጥናት፣ የሃይማንኖት፣ የሃውልት፣ የስነቃል፣ የሙዚቃና የትጥቅ እንቅስቃሴወች አሁንም አሉ። በዚህ አውድ የሚፈጸምን በደል ‘በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርስ በደል’ ብሎ መጥራት የመሳለቅ ያህል ነው። እዚህ ላይ አንዳንድ ሰወች በየዋህነት ‘ግን ምን ችግር አለው ዜጋ ቢባሉ” ስለሚሉ አንዳንድ ነጥቦችን ማየት ያስፈልጋል።
አንዱ ምክንያት በብሄር ማንነታቸው የሚገደሉ ሰወችን ባልተገደሉበት ምክንያት ዜጋ ብሎ መጥራት ማለት ገዳዮቻቸው ተራ የግድያ ወንጀል የፈጸሙ እንጅ የዘር ጥቃት ያደረሱ እንዳልሆኑ የሚያደርግ ከለላ መስጠት ነው። የሰብአዊ መብት ድንጋጌወች ሁሉ የዘር ተኮር ጥቃትን ከዜጎች ተራ ጥቃት የተለየ ትኩረት የሚሰጧቸው ብሄርተኝነትን ለማስፋፋት ፈልገው አይደለም። ጉዳዩ ከተራ ወንጀል በተለየ መልኩ አለማቀፍ ትኩረትና መፍትሄ ስለሚያስፈልገው ነው፡፡ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ከተገደለ በኋላ ሁኔታውን አጣርቶ የኢትዮጵያ ሰብዐዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው ዘገባ ላይ ግድያውን በሰብዐዊነት ላይ የተፈጸመ ከባድ ወንጀል እንደሆነና የዘር ማጥፋት ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል ያለውን ስጋት አስታውቋል። ይህ አይነት ወንጀል አለማቀፍ ወንጀል ነው። ወንጀሉ በኢትዮጵያዊነት ላይ ካለን የአመለካከት ልዩነት ጋር አይያያዝም። ወንጀሉ አንድን ማንነት የፖለቲካ ጠላት አድርጎ በመሳል፣ ከፖለቲካ ውጭ የሚኖሩ ድሃ ገበሬወችን ለግልጽ ጥቃት የሚያጋልጥ፣ ሰላማዊ ዜጎች በወገኖቻቸው ላይ ግፍ እንዲፈጽሙ የሚያነሳሳ ኢ-ሰብአባዊነት ነው። ምንም አይነት አላማ ቢኖረው፣ ይህ አይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሰላማዊ ሰወችን ማጥቃት በጀመረበት ሰአት ከፖለቲካ አውድ ወጥቶ ወደአሸባሪነትና ኢሰባዊነት አውድ እየተሸጋገረ ነው ማለት ነው። ይህ የአሸባሪነት የሽግግር ሂደት ዝም ከተባለ፣ በገዳዮቹና በተገዳዮቹ ብቻ የሚቆም የዜጎች ጠብ ሳይሆን ኦሮሞና አማራ በሆኑ ሰወች መካከል ሁሉ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ጥላቻን የሚያሰራጭና፣ የህዝቦችን ተስፋ እስከመጨረሻው ከንቱ ሊያስቀር የሚችል አደገኛ መርዝ ይሆናል። ይህን ወንጀል ለማስቆም የመጀመሪያው ተግባር የወንጀሉን የፖለቲካ ጭምብል አውልቆ አረመኔያዊ ድርጉቱን ለህዝብ በግልጽ ማሳየት ይሆናል። ከዚያም የመገናኛ ብዙሃን የጥቃቱ ሰለባ የሆኑትን ሰወች ታሪክ ለህዝብ በክብር በማሳወቅ፣ ሽማግሌወችና የሃይማኖት መሪወች የእርቅና ምክክር ስራቶችን በህዝብ ፊት እንዲፈጽሙ በማድረግ፤ የህዝብ ለህዝብ ውይይት በመክፈት፣ በመንግስት በኩል አጥፊወችን በህግ በመቅጣት፣ ተጎጅወችን በማቋቋምና በመካስ፣ እንዲሁም እርዳታ በማሰባበር የተጎዱትን ለማቋቋም ጠንክሮ መስራት አለበት። ይህ ጥረት በሃገሪቱ የሰላምና የትብብር ተስፋ መፍጠር ይቻላል። ይህን ካላደረገ ግን ጥቃቱን ይደግፈዋል ወይም አይቃወመውም ማለት ነው።
የማንነት ጥቃትን በስሙ አለመጥራት የምንከተለው ስርዐት ለመብት የማይመች መሆኑ ታውቆ አስፈላጊ መሻሻሎች እንዳይደረጉ ያደርጋል። መቸም በህይወት ከመኖር መብት የሚበልጥ መብት ያለ አይመስለኝም። የመንግስት ዋና ሃላፊነት ህይወትን መጠበቅ
ነው። የህገመንግስቱ አቀራረብ ብሄርተኝነትን እንደሉዐላዊ የጋራ መብት ስለሚቆጥር፣ መንግስት የግለሰብ መብትን አስከብራለሁ የሚለው በብሄርተኝነት መዋቅር ውስጥ አልፎ ነው። ይህ የቱንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆንም የመንግስትን ሃላፊነት ግን አያቀልለትም። መንግስት የተፈጥሮ መብት በብሄር ልዩነት እንዳይረገጥ የማድረግ አለማቀፋዊ ግዴት አለበት። በማንነት ላይ የሚፈጸም ጥቃትን በስሙ የማንጠራው ከሆነ ግን ይህንን ግዴታ ከመንግስት ትከሻ ላይ እናወርድለታለን። ጉዳዩ የስርዐት ችግር ወይም በፖለቲካ ስም የሚፈጸም ከባድ ወንጀል ሳይሆን የጥቂት ሰወች ህገወጥነት ችግር ብቻ ተደርጎ እንዲታይ ይሆናል። ይህ ደግሞ በሌላ አባባል የብሄር ፌደራሊዝሙ አተገባበር የፖለቲካ ወንጀልን ከህግ ቁጥጥር ውጭ አድርጎ እንዲቀጥል ያደርጋል:: ከዚህ በዘመናዊ የጦር መሳሪያ ከተደራጀ ገዳይ ሃይል በስተጀርባ ማን እንዳለም ለማወቅ አይቻልም። የአሜሪካን ጨምሮ በርካታ መንግስታት ከተጠያቂነት ለመሸሽ ህገወጥ ቡድኖችን አስታጥቀው ብዙ ወንጀል ስለሚያስፈጽሙ፣ ህዝብ መንግስትን እንዳይጠራጠር ከተፈለገ ጥርት ያለ መረጃ መስጠትና ቁርጠኛነቱን በተግባር ማሳየት አለበት።
የማንነት ጥቃትን በስሙ አለመጥራት ጽንፈኝነትን የበለጠ ያባብሳል። ዘር ተኮር ጥቃት በአለማቀፍና ሃገራቀፍ ደረጃ በስሙ ካልታወቀ መንግስትም ይሁን ጽንፈኞች እርምጃቸውን ለማስተካከል የሚያስገድድ ጫና እንዳይደርስባቸው ምክንያት ይሆናል። እንደውም በተቃራኒው ጽንፈኞች ያለማንም ተከራካሪ ትርክታቸው ትክክለኛ የፖለቲካ ምክንያትና የህዝብ ድጋፍ እንዳለው አድርገው ለማቅረብ ነጻ እድል ያገኛሉ። ዘርንና የፖለቲካ እምነትን በሚያደባልቅ ሁኔታ ኦሮሞም ይሁን ጉራጌ፣ ትግሬም ይሁን አማራ ብቻ የኢትዮጵያዊነት ወይም የአንድነት ፖለቲካ አቀንቃኝ የሆኑትን ሁሉ ‘አማራ’ በሚል ስም በመፈረጅ፣ ለጠላታቸው የብሄር ማንነት በመስጠት፣ የራሳቸውን የብሄር ትግል በህዝቦች የማንንት ልዩነት ላይ ይመሰርታሉ። የጥቃታቸው ሰለባ የሚሆኑትን ሰላማዊ ሰወች ከፖለቲካ ጠላቶቻቸው ጋር አንድ ማንነት እንዳላቸው አድርገው ከፈረጁ በኋላ ወንጀልን የተቀደሰ የነጻነት ትግል አካል አድርገው ለማቅረብ ይመቻቸዋል። ይህ ሰላማዊ ህዝቦችን ለከባድ ወንጀል የሚያጋልጥ አሰራር በግልጽ ካልተነገረና የህዝብ ተቃውሞ ካልገጠመው በሃገር ብቻ ሳይሆን በውጭም ብዙ አድማጭ ያገኛል። ምክንያቱም አብዛኛው የአለም ህዝብ አፍሪካውያንን የብሄር ዘረኞች አድርጎ ስለሚያይ የኢትዮጵያን ነባር ገጽታ በቀላሉ ወደሌላው የአፍሪካ የጎሳ ዘረኝነት ታሪክ ለመቀየር ከባድ አይሆንበትም።
በማንነት ላይ የሚፈጸምን ጥቃት በግልጽ አለመታገል የፖለቲካ ትርፍ ማግኛ እንዲሆን ያደርገዋል። በዜግነት ወይም በኢትዮጵያ አንድነት እናምናለን የሚሉ ልዩ ልዩ ፖለቲከኞች ከፖለቲካ ተሳትፎ ውጭ የሆነው የአማራ ህዝብ በነሱ የፖለቲካ አቋም ምክንያት የሚደርስበትን ጉዳት ተገንዝበው በማንንት ላይ የሚፈጸምን ወንጀል ከፖለቲካ በመለየት ለአለም ለማሳወቅ ሲጥሩ አይታዩም። ይባስ ብለው በአማራ ማንነት የሚደርሰውን የሰብዐዊ መብት ጥቃት በግልጽ ባለመናገር ራሳቸውን ከብሄር ፖለቲካ የነጹና ገለልተኞች የሆኑ አድርገው ለማቅረብ ሲሞክሩ ይስተዋላሉ። ይህም በማንንት ላይ የሚፈጸመው ወንጀል የህግ ሳይሆን የፖለቲካ አጀንዳ ብቻ ሆኖ እንዲጥል አስተዋጾ ያደርጋል። እነዚህና ሌሎችም ምክንያቶች በማንንት ላይ የሚፈጸም ወንጀልን እንደፖለቲካ መሳሪያ የሚጠቀም ባህልን ያጠናክራሉ። ይህ ሁኔታ ወደፊት ከቀጠለና በማንነት ላይ የሚደርሰው ወንጀል እንደተድበሰበሰ ከቀረ፣ መንግስት ራሱ በአክራሪነት የተፈጠረውን የፖለቲካ ሃይል የራሱ አጀንዳ ማስፈጸሚያ ያደርገዋል። በዚህም ምክንያት ሃገሪቱ የከፋ የአድልወ ስርዐት ውስጥ ልናገኛት እንችላለን። ይህንን ሁኔታ ለመቀነስ በተለይም ከመንግስት የሚጠበቀው የመጀመሪያው እርምጃ በማንነት ሳቢያ የሚደርሰውን ግድያና መፈናቀል በስሙ በመጥራትና፣ በህግ እንዲዳኝ እንጅ የፖለቲካ ትርፍ ማግኛ እንዳይሆን ማድረግ ነው።
በማንነት ላይ የሚደርስ ጥቃት በስሙ መገለጽ ያለበት ከተጠቃው ማንነት ጋር የሚያያዝ መፍትሄ ስለሚያስፈልገው ነው። በአማራ ማንነት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በስሙ አለመጥራት የሚጠቃውን የአማራ ማንነት ለመታደግ ምንም ነገር እንዳይደረግ ያደርጋል። በህይወት የመኖር መብት ከሁሉም መብቶች ስለሚበልጥ የመንግስት ቀዳሚ አስፈላጊነት ይህንን መብት ማስከበር ነው። መንግስት የሰወችን በህይወት የመኖር መብት አሁን ባለው የብሄርተኝነት መዋቅር ውስጥ ማረጋገጥ ካልቻለ፣ ያለው ብቸኛ አማራጭ ከግለሰቦች ጋር እንደብሄር የፈጸመውን ህገመንግስታዊ ጋብቻ አፍርሶ እንደዜጋ መዋዋል ይሆናል። (እርግጥ ይህን እሚያደርግ ከሆነ የዜግነት መብቶች የብሄር መብትን እንዳይረግጡ ማድረግም ይኖርበታል)። ያኔ ሰወች በብሄር ስማቸው ቢገለጹ
ወይም ባይገለጹ ላያከራክር ይችላል። አሁን ግን ዜግነት በራሱ በቂ ሆኖ በማይከበርበት ሁኔታ፣ የብሄር ጥቃትን በስሙ አለመጥራት፣ አማራወችን ያለህገመንግስት ከለላ ራቁታቸውን ማስቀረት ይሆናል። መርሳት የሌለብን እውነታ፦ የተጎጅወቹን ጥቃት የብሄር ማንነታቸው ምክንያትየደረሰ ነው ብሎ አለመጥራት ህይወታቸውን ከብሄር ፖለቲካ ነጻ አያደርገውም። ይልቁንም፣ በህይወታቸውና በኑሯቸው ላይ የተፈጸመው ወንጀል የፖለቲካ አጀንዳ ማራገቢያ ሆኖ ይቀጥላል። (በነገራችን ላይ ዜግነትም ይሁን ብሄርተኝነት ከባዕዳን የቀዳነው ትርከት እንጅ ከሃገራችን ህዝብ ባህልና ልምድ የወረስናቸው ሃሳቦች አይደሉም። ሁለቱም ሳይኖሩ ኢትዮጵያ ለብዙ ጊዜ ኑራለች)።
አንዳንዶች አማራወች ተበደሉ ብሎ መናገርን ለአንድ ብሄር መቆም እንደማለት አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ ይህ አተያይ ግን የተበዳዮቹን ሰብዐዊ መብት በራስ ርዕዮተአለም ብቻ ከማየት የሚነሳ ስህተት ነው። የዘር ፖለቲካን አልቀበልም የሚለው እሳቤ ችግር የለበትም፡፡ በእኔ እምነት የብሄርም ይሁን የአንድነት ፖለቲካ ከህዝብ ውስጥ በፈለቁ ፍላጎቶችና እሳቤወች ካልተመራ አብዛኛውን ድሃ ህዝብ አያገለግልም። ያም ሆነ ይህ፣ ፖለቲከኞች የአንድነትም ይሁን የብሄርተኝነት ፖለቲካን የማራመድ መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከሰላማዊው የአማራ ህዝብ ጥቃት ጋር ተያይዞ እየተነሳ ያለው ጥያቄ የርዕዮተአለም ሳይሆን የመብትና የገሃዱ አለም ጥያቄ መሆኑን ማስታወስ ይገባቸዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ትግሬም ይሁን አማራ፣ ኦሮሞም ይሁን ኮንሶ እንደዜጋ ብቻ ሳይሆን፣ እንደብሄር ማንነቱም እንድንቆምለት የሚያስገድድ ሁኔታ ተፈጥሯል። የቱንም አይነት የተለያየ የፖለቲካ እሳቤ ቢኖረን፣ የማንነት መብት የፖለቲካ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የህግ ጉዳይ ስለሆነ ይህ መብት ሊከበር ይገባል። ይሁን እንጂ፣ ህገመንግስቱ የብሄር ማንነትን በህግ መከበር እንዳለበት መብት አድርጎ ከደነገገ በኋላ አፈጻጸሙን ግን አማራነትን ተከባሪ ሳይሆን ተጠቂ እንዲሆን በሚያደርግ የፖለቲካ አውድ ላይ ጥሎታል። መንግስት ይህ የፖለቲካ አውድ የህግ መብትን እንዳይጥስ የማድረግ ግዴታ አለበት። ይህን ካላደረገ መንግስት የአማራን ማንነት በህግ የፈጠረው ለማስከበር ሳይሆን ለማስጠቃት አልሞ ነው ብሎ ለመናገር ያስደፍራል።
ለማጠቃለል፣ የአማራም ይሁን የአፋር፣ የትግሬም ይሁን የኦሮሞ፣ የጉራጌም ይሁን የኮንሶ ማንኛውንም ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት በሚፈጸምበት ጊዜ በኢትዮጵያ አንድነት አምናለሁ የሚል ሰው “የማምነው በዜግነት እንጅ በብሄር አባልነት አይደለም” በማለት ወይም በሌላ ምክንያት ጥቃቱን ተራ ጥቃት አድርጎ መመልከት የለበትም። በብሄርተኝነት የሚያምንም ሰው “የማምነው በብሄርተኝነት እንጅ በዜግነት አይደለም” ብሎ ጥቃቱን ዝም ሊል አይገባውም። ይህንን ማድረግ ፖለቲካ ከህግ ቁጥጥር ውጭ እንዲሰራ መተባበር ነው። በማንነት ላይ የሚፈጸም ጥቃት ከፖለቲካ አጀንዳነቱ በፊት ከፍተኛ የሆነ አለማቀፍ ወንጀል ነው። የማንነት ውንጀላ በህግ ካልታረመ ማንኛውንም ሰው በሰበብ ባስባቡ ሰለባ ስለሚያደርግ ማህበረሰባችንን በፍርሃት አስሮ የሚያኖር ሰንሰለት ይሆናል። “ያንተ መብት በእኔ የፖለቲካ እሳቤ ካልተቀረጸ አያገባኝም” ማለት ከሰው ህይወት የራስን ርዕዮተአለም ማስቀደም ይሆናል። በሌላ አባባል የወንጀሉን ግዝፈት ተቀብሎ በስሙ መጥራትና ማውገዝ የመፍትሄ ፍላጎት ምልክት ነው።
የአማራ ማንነት የፖለቲካ መጫወቻ ለምን ሆነ?
አንዳንዶች ለዚህ የሚሰጡት መልስ አማራወች ማንነታቸውን ስለማይቀበሉ ነው የሚል ነው። አማራነትን እንደፖለቲካ ማንነት ብንቀበለውም ባንቀበለውም፣ መብት የሚከበረው የፖለቲካ እምነት እየታየ ስላልሆነ፣ የአማራ ማንነት በህግ ከሌሎች ማንነቶች እኩል መጠበቅ አለበት። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በርካታ የአማራ ተወላጆች አማራነትን እንደማንነት ለመቀበል ለምን እንደሚከብዳቸው እንመልከት።። በእኔ እምነት ብዙ ሰወች አማራን የፖለቲካ ማንነት አድርገው ላለመቀበል በቂ ምክንያት ነበራቸው። ይህም የአማራነት ፖለቲካዊ ትርጉም ከጥንት ጀምሮ በኖሩበት ባህልና እሳቤ ሳይሆን በሌሎች የፖለቲካ ትርክት ተወስኖ የተጫነባቸው ማንነት (politically imposed identity) ስለሆነ ነው። ማንነት የተወሳሰበ ጽንሰሃሳብ ስለሆነ አጭር ታሪክ ቀመስ ገለጻ ላቅርብ።
ማንነትን ራሳችን መርጠን ስንሆነውና ሌሎች “ እንዲህ ናችሁ” ብለው ሲጭኑብን አቀባበላችን ይለያያል። ለምሳሌ የሰው የቆዳ ቀለም (ጥቁር ወይም ነጭ የመሆን ጉዳይ) በአይን የሚታይ ልዩነት ቢሆንም፣ በ17ኛው ክፍለዘመን ከስልጣንና ከፖለቲካ ጋር
እስከሚገናኝ ድረስ አስፈላጊ ማንነት አልነበረም። አሜሪካ በእንግሊዝ ቅኝ ስትያዝ እዛ የተወሰዱት ድሃ ነጮችና ከባርነት የተለቀቁ ጥቁሮች ተመሳሳይ ህይወት ነበራቸው። ነጭ ወይም ጥቁር መሆናቸው ከየት እንደመጡ የሚያሳይ እንጅ የበላይነትና የበታችነት ምልክት አልነበረም። በ1675-6 ናትናኤል ቤከን በሚባል ሰው አነሳሽነት ድሃ ነጮችና ጥቁሮች ተባብረው አንድ ፐርሰንት በሚሆኑት የእንግሊዝ ከበርቴወች ላይ አመጹ (Becon’s Rebellion)። በዚህ ስጋት የገባቸው የእንግሊዝ ገዥወች፣ ነጮቹንና ጥቁሮቹን ከፋፍለው ለመግዛት ዘረኝነትን በቀለም ላይ እንዲመሰረት ወሰኑ። ለድሃወቹ ነጮች ምንም ሳይሰጡ ጥቁሮቹን የነጮቹ ባርያ አደረጓቸው። የነጭና ጥቁር ጋብቻ ተከለከለ። ህይወታቸው እንዳይቀላቀል አስገዳጅ ህግ ወጣ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ጥቁር ማለት የቆዳ ቀለም ሳይሆን የማንንት ምንጭ ሆነ። ጥቁሮቹ ጥቁርነታቸውን ራሳቸው አልፈጠሩትም። ነገር ግን ጥቁር አይደለሁም ቢሉ በነጮች ‘ጥቁር” ከመባልና ከመጨቆን ስለማያመልጡ ያላቸው አማራጭ የጥቁር ማንነትን ተቀብለው ትርጉሙን በራሳቸው ታሪክ መቀየር ነበር። ለምሳሌ ኢትዮጵያኒዝም ያሉትን ንቅናቄ የጥቁር ማንንት የማስከበሪያ መንገድ አድርገውት ነበር። እዚህ ላይ ልብ እንበል። ማንኛውም ልዩነት ከፖለቲካና ከስልጣን ጋር ካልተያያዘ የግለሰቦች ጉዳይ ስለሚሆን ማንነት ብለን ብንጠራው ወይም ባንጠራው ብዙ ችግር የለውም። ማንነት የፖለቲካና የስልጣን ምንጭ ከሆነ ግን የማይከበር ማንንት ያለው ሰው ከባድ ጉዳት ላይ ሊወድቅ ይችላል። ለምሳሌ ለብዙወቻችን የአፍንጫ እርዝመት አስፈላጊ አይደለም። አንድ ወቅት ግን ርዋንዳ ውስጥ ቤልጀሞች ቱትሲወቹን ከሁቱወቹ የለዩት የህዝቡን አፍንጫ በሴንቲሜትር በመለካት ነበር። ረዘም ያለ አፍንጫ ያላቸውን ቱትሲ ብለው ስልጣን ሰጡዋቸው፤ አጠር ያለ አፍንጫ ያላቸውን ሁቱ ብለው ተገዢ አደረጓቸው። በአፍንጫ ልዩነት ሰበብ የፖለቲካና የጥቅም ልዩነት ተፈጥሮ ከቆየ በኋላ አንዱ ተነስቶ “በቃ እንርሳው፣ የአፍንጫ ልዩነት እኮ ማንነት አይደለም” ቢል ሰሚ አያገኝም። ማንነት የባህል ጉዳይ ቢመስልም የስልጣንና የጥቅም ደረጃ ማውጫ ከሆነ ችላ ሊባል አይችልም። ቱትሲና ሁቱ መጀመሪያ ትርጉም በሌለው የአፍንጫ እርዝመት ቢለያዩም፣ ባሳለፉት የፖለቲካ ህይወት ሳቢያ እስከመተላለቅ ደረሱ።
የተለያየ ቋንቋ፣ ባህል፣ ልምድ ወዘተ ከህዝቦች ጋር ሁሌ የሚኖር ማንንት ነው። ይህን ማንንት ከፖለቲካና ከስልጣን ጋር ካልተያያዘ ሰወች በነጻነት ሊቀይሩት፣ ሊደበላለቁ ይችላሉ። ሆኖም ፖለቲከኞች ይህንን ልዩነት ሰወችን ጠላትና ወዳጅ አድርገው ለመክፈል ሲጠቀሙበት ያኔ የጠላት ማንነት የተጫነባቸው ሰወች የተጫነባቸውን የማንነት ትርጉም እስኪቀይሩት ድረስ መቀበል ይከብዳቸዋል። አማራወች ከጥንት ጀምሮ በኖሩበት ባህልና እሳቤ ሳይሆን በብሄር ፖለቲካ ልዩ ትርጉም የተሰጠው ማንነት ተጭኖባቸዋል። ብዙወቹ ከቋንቋቸው ጋር በማያያዝ አማራነታቸውን ይሁን ብለው ቢቀበሉም ፖለቲካው ለአማራነታቸው የሰጠውን ትርጉም ግን ሊቀበሉት የሚከብድ ነበር። ለምን?
ኢሃዴግ ስልጣን በያዘ ማግስት አማራ የተባሉ ሁሉ ራሳቸውን የጨቋኙ ብሄር አባል ሆነው አገኙት። ይህ የማንነት ፍረጃ ለማንም ምክንያታዊ ሰው ግራ የሚገባ ነው። ምክንያቱም በ17 አመቱ የደርግ አገዛዝ ዘመን፣ የነገስታቱ ስርዐት (የብሄርም ይሁን የመደብ) የፖለቲካና የኢኮኖሚ መሰረቱ (በመሬት ላራሹና በሌሎችም) ከስር ከመሰረቱ ተነቅሎና በአዲስ የልሂቃን መደብ ተተክቶ ነበር። ኢሃዴግ ስልጣን ላይ ሲወጣ ሁሉም ድሃ ኢትዮጵያውያን በአንድ መደብ ላይ ነበሩ፡፡ ያኔ በሃገሪቱ ላይ ጉልበትና ሃብት የነበራቸው የዘውዱ ስርዐት ናፋቂወች ሳይሆኑ የዘውዱን ስርዐት ያጠፉት ወታደሮች ነበሩ። ይህም ማለት ህወሃት ጫካ ሲወጣ የሃገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በተመለከተ ያረቀቀው የብሄር ትንታኔ (ስህተትም ሆነ አልሆነ) ወደስልጣን ሲመጣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አውዱ ጠፍቶ ነበር ያገኘው። ሆኖም ከላይ እንዳልሁት ርዕዮተአለም የፖለቲካ ሃይማኖት ነውና፣ ህወሃት ሃይማኖቱን ለመቀየር አልሞከረም። አማራነትን ከነገስታቱ ዘመን የጨቋኝነት መደብ ጋር አስተሳስሮት ቀጠለ። የህወሃት አስተሳሰብ በኢሃዴግ ውስጥ ስለተተገበረ ባለፉት 30 አመታት አማራ በብሄሩ ጨቋኝ ለመሆን የሚችልበት መሰረት ሊኖረው ይቅርና፣ በብሄሩ ጥቃት የሚደርስበት ማንነት ወደመሆን ተቀየረ። በዚህ ሳቢያ ብዙ አማርኛ ተናጋሪወች የአማራነትን ትርጉም ለመቀበል ሲከብዳቸው በአንዳንድ ክልሎች ዘንድ ግን አማራነትን የሚያገሉ ህጎች፣ እምነቶችና አደረጃጀቶች ተፈጠሩ። ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ፣ ያለፉት 47 አመታት ምን ያህል የዱሮውን የዘውድ ስርዐት እንዳጠፉትና በአዲስ የልሂቃን ስርዐት እንደቀየሩት እየታወቀ፣ አሁንም አማራ ከነገስታቱ ዘመን ጋር የተሳሰረ ማንነት ሆኖ ተፈጠረ። ከዚህም ይባስ ብሎ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ፣ አንዳንድ የኦሮሞ ልሂቃን የነገስታቱን ታሪክ ከብሄር ጭቆና ወደ ጥገኛ ቅኝ አገዛዝ ታሪክ ስለቀየሩት አማራነት ከቅኝ ግዛት ሰፋሪነት ጋር የተያያዘ አዲስ ማንነት ሆኖ ብቅ አለ። እዚህ ላይ በብሄር ጭቆናና በቅኝ አገዛዝ ጭቆና ያለውን አንድ ልዩነት ማጤን ይገባል።
የብሄር ጭቆና በአንድ ሃገር ውስጥ ካሉ ብሄሮች መካከል አንዱ ብሄር ሌላውን የሚጨቁንበት ስራት ሲሆን የቅኝ አገዛዝ ጭቆና ግን ምንም አይነት የዘርና የባህል ግኑኝነት በሌላቸው ባእዳን መካከል የሚፈጠር፣ የአንድ ሃገር መንግስት በሌላ ሃገር መንግስት ላይ የሚጭነው ጭቆና ነው። ለምሳሌ ሻዕቢያ አላማው ኤርትራን ከኢትዮጵያ መገንጠል ስለነበረ የተከተለው ትርክት ኢትዮጵያ ኤርትራን ቅኝ ገዝታለች የሚል ለበር።አሁንም አንዳንድ የኦሮሞና የትግራይ ብሄርተኞች ከብሄር ጭቆና ወደ ቅኝ አገዛዝ ጭቆና የሚያደላ ትርክት በመከተል አላማቸው ነጻ መንግስት መመስረት መሆኑን ይናገራሉ። የቅኝ ግዛት ትርክት በነጭ አውሮፓ ሰፋሪወችና በጥቁር አፍሪካ ኗሪወች መካከል የነበረውን የዘርና የስልጣን ልዩነት መሰረት አድርጎ የሚተነተን ስለሆነ ትርክቱ ሙሉ ተቀባይነት ካገኘ የመገንጠልን ጥያቄ የነጻነት (ዲኮሎናይዜሽን) ጥያቄ የማድረግ ሃይል አለው። በኦሮሚያ የዚህን ትርክት መስፈርት ለማሟላት በደርግ ዘመን ከልዩ ልዩ ቦታ ለሰፈራ የሄዱ ድሆችን ልክ በቅኝ ግዛት ዘመን ከአውሮፓ ወደአፍሪካ እንደሄዱት አይነት ተደርገው እንዲቆጠሩ የሚያደርግ የርእዮተአለም ግንባታ ሲደረግ ቆይቷል። አንዳንድ ‘ልሂቃን’ በኦሮሚያ የሚኖሩ አማሮችን ባልተፈጠሩበት ዘመን የነበሩ ‘የሚኒልክ ሰፋሪወች’ የሚሏቸውና አንዳንድ የትግራይ ልሒቃን ሳይቀሩ የኢትዮጵያ መሰረት የሆነችውን ትግራይ በአማራ ቅኝ አገዛዝ የተጨቆነች የሚሉት፣ የቅኝ አገዛዝ ጭቆና ትርክት ሁለት የጥቅም አማራጭ ስላለው ነው። አንደኛ የመገንጠልን ተገቢነት ስለሚያስከትል ነው። ሁለተኛ ቅኝ ገዥ ተብሎ የተፈረጀው አካል የያዘው መሬትና ሃብት በቅኝ አገዛዝ የተያዘ ነው በሚል ሰበብ ሃብትና መሬቱን ከመቀማት ጀምሮ ከሃገር እስከማባረር የሚደርስ እርምጃ ለመውሰድ ስለሚመች ነው። ከዚህ አንጻር ከብሄር ጭቆና ወደቅኝ አገዛዝ ጭቆና የተቀየረው ትርክት በአማራ ህዝብ ላይ ከፍተኛ የህልውና ስጋት መፍጠሩ የሚገርም አይደለም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደሞ የአማራ ማንነት እየሰፋ የብሄር ፖለቲካን የሚቃወሙ ወይም አንድነትን የሚደግፉ የሌላ ብሄር ተወላጆች ወይም ከአማራ ዘር የተደባለቁ ሁሉ የሚፈረጁበት ማንነት ሆኗል። አማራነት አማራ ባልሆኑ የፖለቲካ ቡድኖች የሚፈጠር ብቻ ሳይሆን አማራ እየተባሉ ነገር ግን አማራነትን የሚቃወሙ ሃይሎች ሁሉ የወል ስያሜ ወደመሆን ተሸጋገሯል። በዚህ ሁሉ ሂደት የአማራ ህዝብ የራሱን ማንነት በራሱ ፍላጎትና ልምድ እንዳይፈጥር ከፍተኛ እክል ገጠመው። ለምሳሌ የአንድነት ሃይል የሚባሉት በአክራሪ ብሄርተኞች ‘አማራ’ እየተባሉ የሚጠሩ ቢሆንም የአማራን ህዝብ በማንነቱ መደራጀት ግን አጥብቀው የሚቃወሙ፣ አልፎ አልፎም ‘ብቸኛው የኢትዮጵያ አለኝታ’ እያሉ የፖለቲካ መሳሪያ ሊያደርጉት የሚሞክሩና በማንነቱ ጥቃት ሲደርስበት ግን በዝምታ የሚያዩ ሆኑ። ይህ ሁሉ የሚያሳየን የአማራ ማንነት በፖለቲካ መነጽር የሚታይና ብሄርተኞች ብቻ ሳይሆሙ የአንድነት አቀንቃኞችም በየራሳቸው ምክንያት የማያከብሩት ማንነት ሆኖ እንደቆየ ነው።
ብሄርተኝነትን እንጸየፋለን የሚሉ ልሂቃኖች ብሄር ተኮር የሆነውን ጥቃት እውቅና ባለመስጠት የሞራል ልዕልና ለማግኘት ወይም የሃላፊነትን ስሜት ለማስቀረት ሲሞክሩ ይስተዋላል። የሞራል ልዕልና የምለው የብሄር ተኮሩን ግድያ “የዜጎች ግድያ ነው” ስንለው ገዳይም ሟችም የእኛው እኩል ዜጎች ናቸው ብሎ ለማመን ይመቸናል። ከዛም ገዳዩንም ተገዳዩንም ዜጋ ካደረግናቸው በኋላ ችግሩ እኛን በማይመለከተን ጥፋት የተፈጠረ እንደሆነ አድርገን በማቅረብ ከሃላፊነት ነጻ የመሆን ስሜት ይሰማናል። በዚህም የሞራል ልዕልና በመታገዝ የመብት ጥሰቱን የብሄር ፖለቲካን አደገኛነት ለማሳያነትና ደጋፊ ለማብዛት እንጠቀምበታለን፡፡ ወገንተኝነት የሚጠይቀውን ከተጠቂወቹ ጎን የመሰለፍ ሃላፊነትንም እናስቀራለን። ‘አማራነት መሞቻ ሳይሆን መከበሪያ ይሁን’ ከማለት ይልቅ “ብሄርተኝነት ይጥፋ” በማለት የመብትን ጥያቄ ወደርዕዮተአለም ጥያቄ እንቀይረዋለን። ይህ አስተሳሰብ ውስጡ ምን ያህል ከዘር እሳቤ የጸዳ እንደሆነ ማወቅ ያዳግታል። ምክንያቱም ይህን የሚሉ ሰወች የእኔ ብሄር ተጎዳ ባይሉም የእኔ ዜጋ ተጎዳ ብለው ግድያውን ለማስቆም ከብሄርተኞች የተሻለ ጥረት ሲያደርጉ ስለማይታይ ነው። የብሄር ፖለቲካ አይመለከተኝም የሚሉ ሰወች አንዳንድ ነጮች በዘረኛ ስርዐት ውስጥ እየኖሩ ‘I donot see colour’ እንደሚሉት አይነት ናቸው። ከራሳቸው አይን ላይ የብሄር መነጽር ሰክተው የማንነት ተጎጅወችን ባያዩ ኖሮ ሞታቸውን ከብሄር ፖለቲካ ጋር ባላገናኙትም ነበር። እነሱ ሞትን የፖለቲካ ትርፍ ማግኛ ስለሚያደርጉት፣ ዜጋ የሚሉትን ድሃ በዝምታ የሚያስገድሉ የህልውና ጠንቆች ናቸው።
አስተያየቶች