ከሊቢያ ውድቀት ኢትዮጵያ ምን መማር አለባት?
አገር የሚጠፋው በብዙ መንገድ ቢሆንም የሊቢያን አወዳደቅና የምዕረባዊያንን ሤራ በአጭሩ በመመልከት አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚካሄደው ማመሳከሩ መፍትሔውን ቶሎ እንድንፈልግ ይረዳናል ብዬ አምናለሁ። (አቶ ቱምሳ ዹጋ)
መምህር ፋንታሁን ዋቄ “ኦርቶዶክሳዊነትና የሰይጣን መንግሥት በሚል ርዕስ ካሳተመው የትርጉም መጽሐፍ ምዕራፍ አንድ በባለቤቱ ፈቃድ ተቀንጭቦ የተወሰደ።
በትዕግስትና በማሰውተዋል ያንብቡ፣ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚካሄደው ሁለገብ ብጥብጥ ጋ ያገናዝቡ፣ ከዚያም ለአገራችን የሚበጀውን ሀሳብ እያመነጩ ለሕዝቡና ለሚመለከታቸው ባገኙት መንግድ ሁሉ ያጋሩ። ለአገርዎ ውለታ በመሥራት የደገሰውን ጥፋት ይቀንሱ።
መልካም ንባብ
የአገራት መንግሥታትን መውደቅና የሚጀመርው መሪዎች ከገዛ አገራቸው ሕዝብ ጋር በማይጣጣም አስተሳሰብ ሲመሩ ብቻ ሳይሆነ የአገራቸውን ፈቃድ ለመፈጸም በሚያደርጉት አርቆ አስተዋይነት ምክኒያት ኃያላን አገራት ሥጋት ከገባቸው በሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት ነው። በኢትዮጵያ ያለው ሁለት መልክ አለው። የአገራችን ጠላት ራሳቸው የአገሪቱ ልሂቃን ሲሆኑ ሁለተኛው የውጭ ጣልቃ ገብነትን ባለመዋቅ ወይንም በጊዜዊ ጥቅም ተገዝተው የሚያገለግሉ የፖለቲካ ልሒቃን መንሰራፋት ነው። የሊቢያ ግን በግልጽ መንግሥትን ከራሲ አገር ሕዝብ ጋር በማጋጨት የጣሉት ምዕረባዊያን ነቸው።
ለዚህ የሊብያን ቀውስ መመርመር ማስረጃ ነው፡-
ጋዳፊ ሥልጣን ከዯዘ በኋል፡-
1. ሕዝቡን ከበረሃ ችጋር አውጥቶ ዜጎችን ለከፍተኛ ሰላምና የኑሮ ደረጃው እንዲያድግ ያደረገውን መሪውን ሙሀመድ ጋዳፊን አስገደሉት
2. ይህን ተከትሎ ኢስላማዊ መንግሥትን (Islamic State) ጨምሮ የተለያዩ ጂሃዳዊ ቡድኖች መደበኛውን ሕዝብ እያሸበሩት የመከራ አገር አደረጓት
3. ሚሊዮኖች ተሰሰደዱ ሞቱ። እዛው በጦርነቱ መካከል የቀሩት በጥይት እርምታ መካከል በረሀብ፣ መብራትና ንጹሕ ውሐ በማጣት፣ ህክምና ትምህርት አጥው ይኖራሉ
4. አገሩን ለማፍረስና ሕዝቡን በመከራ ውስጥ እንዲገባ አቅደው የፈጸሙት ምዕራባዊያን በሊብያ ጦርነት መሪና ተሳታፊ የሆኑት ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሃዊ ዓላማ ኖሮአቸው አይደለም። ሕዘቡንም አማክረው አይደለም።
5. ሊቢያን መንግሥት አልባና የጦር ቀጠና ያደረገውን ሂደት የሚዘግቡ ጋዜጠኞች በአንድ ዓለም መንግሥት አገልጋይነት በሚያገለግሉት ፖለቲከኞች እና የተባበሩት መንግሥት ተቋማት ፍላጎት መረጃን አዛብተው ለዓለም ይመግባሉ።
6. በቍጥጥር ሥር የሚንቀሳቀሱት የመረጃ ተቋማት ሊብያን በቦንብ የምትደበደበው “ጋዳፊ ክፉና አምባገነን በመሆኑ ሕዝቡንም መከራ ስላጸናበት ሰዎችን ከሥቃይ ለመገላገል ነው” የሚል ነው።
7. ነገር ግን እውነታውን ስንመለከተው በጋዳፊ አገዛዝ ሥር የነበረው የዜጎች ሕይወት በ1967 ኮሎኔል ጋዳፊ በአፍሪካ ውስጥ ደሃ ከሚባሉ ሃገሮች ውስጥ አንዷን ተቆጣጠሮ በመምራት ጀመረ
- ጋዳፊ ከመገደሉ በፊት የሊብያ ሕዝብ ከሌሎች አፍሪካውያን በተሻለ ከፍተኛ የሆነ የሕይወት ርዝማኔ ዘመን ግምት (life expectancy) የነበራቸው
- የአህጉሩን ከፍተኛ አጠቃላይ ብሔራዊ የምርት ውጤት (GDP) ይዘው ነበር።
- ከድኽነት መስመር በታች የሚኖሩ ሊብያውያን ቁጥር ከአንዳንድ የምዕራብ አውሮፓ ሀገራት ያነሰ ነበር።
- ከዚህ በተጨማሪ ሀገር አቀፍ የሆነ እና በነዳጅ ምርት የተደገፈ ለሁሉም ለሴትም ለወንድም ነፃ የትምህርት እድል እና የህክምና አገልግሎት ይቀርባል።
- ጋዳፊ በአስተዳደር ዘመኑ የሕዝቡንም የማንበብ እና መጻፍ ችሎታ(literacy rate) ከ20 በመቶ ወደ 83 በመቶ አሳድጎታል።
- ሴቶችም የፈለጉትን የመልበስ በዩኒቨርሲቲዎች የመማር ነጻነት ነበራቸው፤ ዛሬ እነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ተዘግተዋል።
- በጋዳፊ ዘመን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ሴቶች ሲሆኑ እነዚህም ሥራ የመያዝ፣ ንብረት የማፍራት፣ ፍች የመፈጸም እንዲሁም በመጀመርያው የሥራ ዘመኑ ባፀደቀው የሥራ እኩልነት ሕግ መሠረት ከወንዶች እኩል ደመወዝ የማግኘት መብት ነበራቸው።
- ዛሬ ሊብያን ለመቆጣጠር የሚዋጉት አብዛኞቹ ኢስላማዊ ቡድኖች ይህን ለሴቶች የተሰጠ እድል አጥብቀው የሚቃወሙ ናቸው።
- እነዚህ የጋዳፊ የአመራር እቅዶቹ እና ስልቶቹ ይፋ በሆኑት የግል ፍልስፍናዎቹ የተደገፉ ሲሆኑ ዓላማውም ማኅበራዊ እኩልነትን የሚያስከብር ማኅበረሰብ መፍጠር ነበር።
- በጋዳፊዋ ሊብያ የቤት ባለይዞታ መሆን እንደ ሰብዓዊ መብት የሚቆጠር የነበረ ሲሆን የቤት ባለቤትነት ራሱ ለሰዎች ነፃነት መሠረታዊ ነገር መሆኑን ሕጉ ያስቀምጣል።
- ጋዳፊ ሁሉንም ሊብያውያን የቤት ባለቤት ሳያደርግ በድንኳን ለሚኖሩት ቤተሰቦቹ እንኳን ቤት ላይሰጥ ቃልገብቶ ነበር።
- የሰውን ሁሉ ምግብ፣ ልብስ እንዲሁም መጓጓዣ የማግኘት መብት እንደ አይነኬ ሃይማኖታዊ ቀኖና ቆጥሮ አውጇል።
- ሰፊው ሕዝብ ወይም ማኅበረሰብ በግለሰብ የግል ምርጫ ውስጥ ጣልቃ የመግባት መብት እንደሌለው እውቅና ሰቷል።
- ጋዳፊ መንግሥት-መር የትምህርት መዋቅር አደገኛ ተጽዕኖ መፍጠርያ መንገድ እንደሆነና ማንኛውም ሰው የተወሰነ የትምህርት ፍኖተ ካርታ እንዲከተልና የተወሰኑለትን የትምህርት አይነቶች እንዲማር መገደድ እንደሌለበት አስቀምጧል።
- ይህን መሰል መንግሥታዊ አሠራሮች አይምሮ መጠምዘዝና ማስገደድ ብሎ ይገልጣቸው ነበር ።
- ሊብያ አራጣ ማበደርን የማይቀበል ብሔራዊ ባንክ የነበራት ሲሆን በዚህም ምክንያት ዜጎች ወለድ የሌለው ብድር መውሰድ ይችላሉ።
ጋዳፊን የበለጠ የምዕረባዊያን ጥርስ ውስጥ የከተተው ምንድ ነው?
1. ጋዳፊ ከሊብያ የነዳጅ ትርፍ ከፍሎ አፍሪካን መልሶ የመገንባት እና በቂ የምግብ አቅርቦት እንዲኖር እቅድ ይዞ ይነቀሳቀስ ነበር
2. ጋዳፊም የመጀመርያውን የአፍሪካ የመገናኛ ሳተላይት ያበማምጠቅ ብዙ ክፍያ ከሚኣስከፍሉ የአውሮፓ ድርጅቶች በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያንን ነፃ አውጥቷል፣ ዛሬ አብዛኛው የአፍሪካ ክፍል ከእንግሊዝ የተሻለ የመገናኛ መረብ አለው።
3. ጋዳፊም የዓለማችንን ትልቁን “ታላቁ ሰው ሰራሽ ወንዝ” በሚል ስያሜ የጀመረውን የመስኖ ግንባታ ከግብ አድርሷል። ይህም አስቀድሞ በረሃ ለነበሩ ቦታዎች ውሃ ማቅረብ የቻለ ነው።
4. ምዕራባውያን በባርያ ንግድ ውስጥ ከመሳተፋቸው ብዙ አሥርት ዓመታት አስቀድሞ አረቦች አፍሪካውያንን በባርነት የመግዛት ረጅም ታሪክ አላቸው። በዚህም ሀገሩ ሊቢያ ለነበራት ተሳትፎ ጋዳፊ በይፋ ይቅርታ የጠየቀ ብቸኛው የአረብ መሪ ነው።
5. ብዙ የመገናኛ ብዙኃን ተንታኞች ጠንካራና የተዋሃደች አፍሪካን ለመገንባት ጋዳፊ የነበረው ፍላጎት [አፍሪካን ለዘላለም ለበዝበዝና ራሷን ሳትችል በእርስ በእርስ ግጭት፣ በድኽነትና በሁለግበ ጥገኝነት ታሥራ እንድትኖር አጥብቀው ከሚሠሩ አገራት]
6. እንደ አሜሪካ ካሉ ምዕራባውያን ኃይላት ጋር ቅራኔ ውስጥ እንደከተተው ይናገራሉ። ለምሳሌ ያህል ነሐሴ 2003(August 2011) ፕሬዝደንት ኦባማ ከሊብያ ብሄራዊ ባንክ ሠላሳ ቢሊዮን ዶላር የወረሰ ሲሆን ጋዳፊ የአፍሪካ ማዕከላዊ ባንክ ለመመሥረት የመደበው ነበር።
7. በተጨማሪም አፍሪካውያን በምዕራባውያን ላይ ያላቸውን ጥገኝንት መቀነስ በሚያስችሉ ትላልቅ መሠረተ ልማቶች ላይ በታቀደ መልኩ መዋዕለ ነዋዩን ሲያፈስ ቆይቷል።
8. መሠረታዊ ዓላማው አፍሪካን በኢኮኖሚ ነጻ ለማውጣት ነበር። ለምዕራባውያን ቁጥጥር ተቃዋሚ ሆነው ለሚታዩ ብሔራዊ ነፃ አውጪ ድርጅቶች ያደርግ የነበረው እርዳታ ምዕራባውያን መንግሥታት አላስደሰተም። በተለይ አሜሪካ እንደመደፈር ቆጠራዋለችና በአገሪቱ ላይ ጥፋት አወጀች።
9. የምዕራባውያኑ የዜና አውታሮች ታሪኩን ከዓረቡ ዓለም የለውጥ ንቅናቄ ጋር አገናኝተው በማቅረብ የምዕረባዊያን መንግሥታትን እጅአዙር ጣልቃገብነት ለጊዜውም ቢሆን ለመሠወር ችለዋል።
10. ዜና አቅራቢዎች ይህንን ነውጥ “ነጻነት በተጨቆኑት እጅ እየተያዘች ነው” የሚል ማስመሰያ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት የመላውን ዓለም ሕዝብ እውነቱን እንዳይረዳ በዘገባቸው አደርገውት ነበር። ለምሳሌ፡- የሊብያ አመጽ በተጀመረ
በሳምንቱ የካቲት 18(February 25th) [የወቅቱ የፈርነሳይ ፕሬዚደንት] ኒኮላስ ሳርኮዚ (Nikolas Sarkozy) ከፓሪስ “ጋዳፊ መሄድ አለበት” ሲል መግለጫ ሰጠ።
ከሦሥት ቀን በኃላም የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚንስቴር ዴቪድ ካሜሮን(David Cameron) ሊብያን ክልክል የበረራ ክልል ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ገለጠ (አብዛኛውን ጊዜ ይህ የምዕራባውያን ወታደራዊ እርምጃ የመጀመርያው ምዕርፍ ነው)።
ከወር በኋላም በኒውዮርክ ታይምስ (New York Times) መጽሔት የሲ.አይ.ኤ (CIA) የስለላ ሰራተኞች ለሳምንታት በሊብያ ተልዕኮ ላይ እንደነበሩ ይፋ ሆነ። ይህ መግልጫ በኒውዮርክ ታይምስ ይፋ የሆነው መጋቢት 21(March 30th) ነበር። ይህም የሚያመለክተው አመጹ ከተጀመረበት የካቲት(February) አጋማሽ ጀምሮ ለጦርነቱ መቀጣጠል ሲሠሩ እንደነበረ ያመለክታል።
በቀጣይም ሲ.አይ.ኤ ሊብያ ውስጥ በኤም.አይ.ሲክስ (MI6) እና የእንግሊዝ ልዩ ኃይል ሲደገፍ እንደነበረ እንዲሁም ፕሬዝዳንት ኦባማ ሲ.አይ.ኤ አማጽያኑን የሚያስታጥቅበትን እና የሚረዳበትን ስምምነት እንደፈረመ ተረጋገጠ።
ኦባማ በይፋ መግለጫው እንደተናገረው “የመንግሥት ለውጥ” (regime change) እንደሚያስፈልግ የአረብ ሕዝብንና ዓለምን ከእውነተኛ ሂደትና መረጃ ለማራቅና ግራ ለማጋባት ሂደቱ ሁሉ “የአረቡ ዓለም ለውጥ” (the Arab Spring) እየተባል በሚዲያ ይለፈፋል፤ ከፕሮፓጋንዳው አስቀድሞ ወታደራዊ ዝግጅትና ለግጭቱ በመሬት ላይ እሣት የሚያቀጣጥሉ ቡድኖች ድጋፍና ሥልጠና፣ መረጃና የፐሮፓጋንዳ ድጋፍ መስጠቱ አስቀድሞ በአሜሪካ ይካሄድ ነበር።
ዴቪድ ካሜሮን ክልክል የበረራ ክልል ተግባራዊ መደረጉ አስፈላጊ የሆነው ጋዳፊ የሊብያን ሕዝብ በቦምብ ለመደበድብ በማቀዱ ነው ብሎ ሲከራከር፣ ቢቢሲ(BBC) በበኩሉ የጋዳፊ የጦር አውሮፕላኖች በተቃዋሚዎች ላይ ተኩስ እንደከፈቱ እና የዘር ማጥፋት ሥጋት መኖሩን የሚያመለክቱ የመንግሥታት መግልጫዎችንም ያለምንም ማጣራት በተደጋጋሚ ዘግቧል።
ከቀናት በኃላ መጋቢት 22(March 1st) ራሱ የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር ሮበርት ጌትስ (Robert Gates) በፔንታጎን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በጋዳፊ የጦር አይሮፕላኖች ተፈጸሙ ስለተባሉት ጥቃቶች ምንም አይነት ማረጋግጫ አለመኖሩን አምኗል።
አሁንም ግን መደበኛውን ሕዝብ ለመጠበቅ ወታደራዊ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል የሚለውን ሃሳብ ጣልቃ ገቢዎቹ ምዕራባዊያን በቢቢሲ በኩል ያራግቡት ነበር።
መጋቢት ማገባደጃ ላይ ኦባማ ወታደራዊ እርምጃው በቤንጋዚ (Benghazi) የደም መፋሰስን እንዲገታ በተደጋጋሚ መግለጫ ሰጠ። በመጨረሻም ደም መፋሰስን ገትቷል እየተባለ ሲወራለት የነበረው የፈረንሳይ የአየር ጥቃት ተሰልፈው በነበሩ አምቡላንሶች ላይ እና ሌሎች የጭነት መኪኖች ላይ ድብደባ ይፈጽም ነበር። እንኳን ለቤንጋዚ ነዋሪዎች የሥጋት ምንጭ ሊሆኑ ቀርቶ ከከተማው እየሸሹ የነበሩ ንጹሐን ላይ የተፈጸሙ የአየር ድብደባዎች መሆናቸው ዘግየት ብሎ ይፋ ሆነ። ይህ ሁሉ ሲሆን ቢቢሲ አሁንም የጭፍጨፋው የሚሸፋፍንና የጦርነቱን መቀጠል አስፈላጊ የሚያስመስል ፐሮፓጋንዳዎችን ቀጥሎበታል። ጋዳፊም ተጨማሪ የደም መፋሰስን ለማስቀረት አማፅያኑ ወደ ግብጽ የሚሸሹበትን መንገድ ክፍት አድርጎ ያመቻች ነበር።
ጉዳዩ በይበልጥ የተራገበው የአሜሪካ አምባሳደር ሱዛን ራይስ (Susan Rice) ጋዳፊ ወታደሮቹን የጅምላ አስገድዶ መድፈር እንዲፈጽሙ የቪያግራ እንክብሎችን (Viagra tablets) እያቀረበላቸው ነው በማልት ለተባበሩት መንግሥታት የደህንነት ምክር ቤት (UN Security Council) ምንም አይነት ማስረጃ ያልቀረበበት የፈጠራ አቀረበጭ። የተባበሩት መንግሥታት ተቀብሎ በመገናኛ ብዙኃን ደጋግሞ ዘግቦታል ።
በሰኔ ወርም የፀረ ጋዳፊ እንቅስቃሴው ከመጠን በላይ የጠነከረ በመሆኑ እንደዚህ ያለውን ሐሰት ማጋለጡ ዋጋ የሌለው ሆነ፤ መገናኛ በዙኃኑም ጉዳዩን እንዳላየ አለፉት።
ትንሽ በማዘናጋት ያንኑ ሐሰት ከመሬት በማንሳት በጋዳፊ ኃይሎች ተፈጽሟል ስለተባለው የጅምላ አስገድዶ መድፈር ለመመርመር አምነስቲ ኢንተርናሽናል (Amnesty International) እንቅስቃሴውን ጀመረ።
“ዓለም አቀፍ ሕግን” ጥሶ ኔቶ (NATO) የሊብያን ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣብያ ሆን ብሎ ከአየር በሚወረወር ሚሳለኤል እንደመታና ሦስት ሰራተኞችን እንደገደለ ሲጋለጥ ጥቂት ጋዜጠኞች በራሳቸው ሰው ሞት ተደናግጠው ነበር። ይሁን እንጂ (ድርጊቱቢሆንም እንኳን) ጉዳዩ ለዘገባ አልበቃም።
ኔቶ ለአማፅያኑ ጥበቃ ሲያደርግና አማፅያኑ የትሪፖሊን (Tripoli) ነዋሪዎች የምግብ፣ የውሃና የነዳጅ አቅርቦት እንዳያገኙ ሲያደርጉ ከጎናቸው ቆሞ ነበር።
ይሁን እንጂ መገናኛ ብዙኃኑ በዚህ ጉዳይ ዝምታን የመረጡ ሲሆን ጋዳፊን ግን ይህንኑ ደርጊት ፈጽሟል በማለት ይከሱት ነበር። እንደ ዘታይምስ (The Times)፣ ዘጋርዲያን (The Guardian) እና ዘቴሌግራፍ (The Telegraph) ያሉ ጋዜጦች ጋዳፊ የራሱን ሕዝብ ለመውጋት ከአፍሪካ ቅጥረኞችን እየተጠቀመ መሆኑን ሲያሥነበቡ ነበር። ሂዩማን ራይትስ ዋች (Human Rights Watch) ድርጊቱን የሚያረጋግጥ ምንም አይነት መረጃ ያላገኘ መሆኑን አስታውቆ ይልቁንም በእነዚህ ዘገባዎች ምክንያት ቅጥረኛ ይሆናሉ በሚል በሊብያ የተገደሉ ብዙ ስደተኛ ጥቁሮችን ማግኘቱን ገልጧል።
የጦርነቱ ውጤት
በሺዎች የሚገመቱ ሊብያውያን ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩም እንደ ቱኒዝያ እና ግብጽ ወዳሉ ሀገራት ተሰደዋል።
የነዳጅ ምርቱም በሁለት ሦስተኛ የወረደ ሲሆን ብዙ ሰዎች የወራት ደመወዛቸው እንዳልተከፈላቸው ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
በዚህ ምክንያት የአክራሪ ፖለቲካ ርዕዮተ ዓለሙ በሊብያ በእጅጉ እየተስፋፋ ወዳለው አክራሪ የእስልምና ቡድን እጅ ሥር ብዙ ወጣቶች እንዲገቡ መንገዱን ከፍቷል።
ይህ ሁሉ ሆኖ ሳለ ኔቶ በሊብያ ያደረገውን ጦርነት “በኔቶ የስኬት ታሪክ ውስጥ ቀዳሚውን ሰፍራ የሚይዝ” ሲል ደረቱን ነፍቶ ተናግሯል ። በመጀመርያ አስቂኝ ሁኖ ሊታየን ይችላል። እንዴት ነው የአንድ ሃገር መፍረስ እርሱንም ተከትሎ የመጣው የብዙ ሰዎች ሞትና የጂሃዳዊነት መጨመር እንደስኬት ሊቆጠር የሚችለው?
ዓይናችን ይገለጥ
አብዛኞቻችን ፍትህ፣ እውነት፣ ደኅንነት እና የመሳሰሉት ሁሉ እንዲኖሩን ከመንግሥታቶቻችን ጋር እኩል የምንመኛቸው እሴቶች ናቸው ብለን እናስብ ይሆናል። እንደዚህ ባለው ዓይን ስንመለከተው በሊብያ የተደረገው ጦርነት ትልቅ ጥፋት ነበር። አሜሪካ ባለፉት አሥርት ዓመታት ለጦርነት በትሪሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያወጣች ሲሆን ለዚም በተለያዩ ሀገራት ኩዌት፣ ኳታር፣ ባህሬን፣ ካዛኪስታን፣ ኡዝቤኪስታን፣ ኬኒያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኒጀር፣ ቡርኪናፋሶ እንዲሁም ሌሎች ብዙ ሀገራት ላይ የጦር ካምፕ ከፍተዋል (የሚያስገርመው ሩስያ ከራሷ ድንበር ውጭ ሁለት ብቻ የጦር ካምፖች ያሏት ቢሆንም ቢቢሲ “የሩሲያ ጸብ አጫሪነት” እያለ በተደጋጋሚ ሲናገር ይደመጣል)። [ከ9/11 የኒዮርክ ጥቃት በኋላ አሜሪካ ከ8 ተሪሊዮን ዶላ በላይ ወጭ አድርጋለች፣ በ85 አገራት ውስጥ ቀጥተኛ ጣልቃገብነት አደርጋ እሣት ጭራለች፣ በጦርነቱ ቀጥተኛ ጥቃት ከ 929,000 ሰው ተገድሏል። ጉዳዩ የማይመለከታቸው 387,000 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል። ይህ ወጭ ግን በሌላ በኩል በብዙ እጥፍ ትርፍ ለአገሪቷ ካምፓኒዎች ገቢ ተደርጓል። መሣሪያ ይነገዳል፣ ማደንዘዣ ኦፒየም እርሻ ይስፋፋል፣ ነዳጅ ከአይሲስ ጋር ይዘረፋል፣ ሰው በባርነት ይሸጣል ወዘተ።]
ታድያ ማነው ስኬታማ የሆነው? አሁን በፍርሃት የሚኖረው የሊብያ ሕዝብ አይደለም፣ በየጊዜው በበቀለኛ የጂሃድ አሸባሪዎች ጥቃት የሚጎበኘው የምዕራቡ ሕዝብም አይደለም። ከዚ ሁሉ ከማንም በላይ ተጠቃሚ የሆነው የአሜሪካ ወታደራዊ ኢንዱስትሪና ወታደራዊ ልሂቃኑ(military elite) ብቻ ናቸው። በየትኛውም መንገድ ታሪኩን እናንብበው ልንጠይቃቸው የሚገቡ ጥያቄዎች አሉ። ለምን ይሆን የተለያዩ መንግሥታት ለራሳቸው ሕዝብም ሆነ ጥቃቱን በሚፈፅሙበት ሀገር ለሚገኘው ሕዝብ ምንም አይነት ጠቀሜታ ለሌለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ በጉጉት ድጋፍ የሚሰጡት? ለምን ይሆን መገናኛ ብዙኃኑ የሊብያን ሕዝብ ስቃይ መራዘም እና ጦርነቱ ያስከተላቸውን ዘርፈ ብዙ ጉዳቶች ይቅርና ግልጥ እውነታዎችን እንኳን ለመዘገብ ፍላጎት ያጣው? ምናልባት ይህን መሰሉ ዘገባ ወታደራዊ ተቋሙንም ሆነ መገናኛ ብዙኃኑን በኪሳቸው የያዙ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን የማያስደስት ስለሆነ ይሆናል። ነገርግን ነገሮችን ግልጥ ለማድረግ ስሞክር በቅድሚያ ለሚጠየቁት ጥያቄዎች በሙሉ መልሱ ስግብግብነትና ሙስና ነው ብዬ አላምንም። የራሳቸው የሆነ አስተዋጻኦ ቢኖራቸውም ነገሩ ጠለቅ ባለ አመለካከት ሊታይ የሚገባው ነው። በዚህ ውስጥ ተሳታፊ ቡድኖችን ከመመልከታችን በፊት የጦር መሣርያ አምራች ድርጅቶችን ቀርበን በትንሹ እንመልከት።
በ1999፣ የደቡብ አፍሪካ መሪ ታቦ እምቤኪ (Thabo Mbeki) ሃገሪቱን 5 ቢሊዮን ዶላር የሚያስወጣ የመከላከያ ስምምነቶችን ፈርሟል። በዚሁ ዓመት ደቡብ አፍሪካ 5 ሚልዮን ለሚደርሱ የኤች አይ ቪ ተጠቂ ዜጎቿ የፀረ-ቫይረስ መድሃኒቶችን ተደራሽ ለማድረግ በጀት የሌላት መሆኑን የሀገሪቱ መሪ በይፋ ገለጸዋል። ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲም ባደረገው ጥናት እአአ ከ2000 እስከ 2005 ባለው ዓመት ውስጥ 330,000 የሚደርሱ ደቡብ አፍሪካውያን ለህክምና የሚሆን ገንዘብ በማጣታቸው በኤድስ መሞታቸውን አረጋግጧል። የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ዘመቻ(Control Arms Campaign) የተሰኘ ቡድን እንዳቀረበው አብዛኛው የጦር መሣርያ ሽያጭ የሚፈፀመው ዝቅተኛ የኢኮኖሚ እድገት ላላቸው (የሦስተኛው ዓለም ሀገራት ብለን ለምንጠራቸው) አገራት ነበር ። ደቡብ አፍሪካም በዚሁ መንገድ ሀብቷን ያወጣች ብቸኛዋ ሀገር አይደለችም። ይህን መሰል ምሣሌዎች እየተፈጠሩ ያሉትን ክስተቶች እንድናስተውል የሚረዱ በመሆናቸው ሌሎችንም የምንመለከት ይሆናል። የታቀደ ጦርነትና ድኽነት እንደፖሊሲ ተቀርጾ አንደሚሠራበት ለማስተዋል ነገሮችን በጥልቀት መመርመር ስንችልና ትልቁን የዓለም አሠራር ምስል ማየት ስንችል ነው።
አባላቱ በየዓመቱ በትንሹ ሚቀያየሩ ቢሆንም ትልቁን የጦር መሣርያ ሽያጭ የሚፈፅሙ ሀገራት የተባበሩት መንግሥታት የደኅንነት ምክር ቤት ቋሚ አባል መሆናቸው አስገራሚ ነው። እነዚህም ሀገራት አሜሪካ፣ ሩስያ፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ እና ቻይና ናቸው። አቀማመጣቸው የሚለያይበት ጊዜ አለ። ለምሣሌ በ2007 ትንሿ ሀገር እሥራኤል 4.4 ቢልዮን ዶላር የሚገመት የጦር መሣርያ በመሸጥ አራተኛውን መቀመጫ ይዛ ነበር። ነገርግን በተደጋጋሚ ከ60% በላይ የሚሆነውን የጦር መሣርያ ንግድ በመፈጸም ቀዳሚውን መቀመጫ አሜሪካ ትይዛለች (ቀሪውን ከ30% ብላይ የሚሆነውን ሰሜን አውሮፓ ይሸፍነዋል)። በዚህ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን አስገራሚ ነው። አሜሪካ ብቻ ከ70 ቢልዮን ዶላር በላይ ለመከላከያ ትመድባለች (በ2008 በአፍጋኒስታን እና ኢራቅ በነበረው ግጭት አሜሪካ ለጦር የምታወጣውን ወጪ ከ2000 ዓም አንፃር ሲታይ በ83% አሳድጋ ነበር። ይህም ተደምሮ ለ46 የአሜሪካ ግዛቶች የሚመደበውን በጀት የሚበልጥ ነው)። በዓለማችን በየዓመቱ ከመቶ ቢልዮን ዶላር በላይ የሚሆን ገንዘብ ለቀላል የጦር መሣርያ እንደሚውል ይገመታል። አንድ የቀላል የጦር መሣርያ የዳሰሳ ጥናት የሚያሳየው በምርቱ ላይ የሚሳተፉ ከመቶ በላይ ሀገራት መኖራቸውን ነው።የገንዘብ ዝውውሩ እጅግ የሚያስገርም ቢሆንም ግን በሰው ልጆች ሕይወት ላይ የሚያስከትለው ውጤት የከፋ ነው። የጄኔቫ በጦር መሣርያ ትጥቅ የሚፈጸም ግፍ እና የፍብረካ አዋጅ(The Geneva Declaration on Armed Violence and Development) እንደሚያስቀምጠው በዓመት ከግማሽ ሚልዮን በላይ ለሚገመቱ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው የጦር መሣርያ ትጥቅ መስፋፋት መሆኑን ይገልፃል።
እንደዚህ አይነቱን የገንዘብ መጠን እያየን፤ ነፃነትን፣ ፍትሕን፣ ዴሞክራሲን እና ደኅንነትን ለማስቀጠል ሊከፈል የሚገባው መሥዋትነት ይሄ ይሆንን? ብለን እናስብ ይሆናል። መቼስ መንግሥታቶቻችን የማኅበረሰቡ አካል በመሆናቸው የሚሠሩትም ለማኅበረሰቡ የሚበጀውን ነው ልንልም እንችላለን። በእርግጠኝነት ራሳቸውን በዚህ መልኩ ለማሳየት የወሰዷቸው እርምጃዎች አሉ። በ2011 የተባበሩት መንግሥታት አባል ሀገራት ተወካዮች በኒውዮርክ የጦር መሣርያ ንግድ ዙርያ ስምምነት ለመፈራረም የተሰበሰቡ ሲሆን ለኛም የተነገረን የጦር መሣርያ ንግዱን ለመቆጣጠርና የጋራ እሴቶቻችን መከበራቸውን እና መጠበቃቸውን ለማረጋገጥ ነው የሚል ምክንያት ነበር። አንድሪው ፌንስታይን( Andrew Feinstein) ባጠናው ጥናት የጦር መሣርያ ንግድ ስምምነቱ ቢኖርም እንኳን በዓለማችን 40% የሚደርሰው ኢኮኖምያዊ ሙስና ከጦር መሣርያ ንግድ ጋር በቀጥታ የተገናኘ መሆኑን ደርሶበታል። ለምሣሌም በኢራቅ እና አፍጋኒስታን በነበረው ጦርነት የአሜሪካ የጦር መሣርያ አምራቾችና ነጋዴዎች በቢልዮን የሚቆጠር ትርፍ አግኝተዋል። ለዚህም እንዲረዳቸው በአንድሪው ፌንስታይን አጠራር “ተሽከርካሪ በር” (በመንግሥት መዋቅርና በንግድ ተቋማት መካከል መመላለሻ በር) የተሰኘውን ፖሊሲ ከአሜሪካ መንገሥት ጋር በመሆን ተግባራዊ አድርገዋል። ይህም የመንግሥት ባለሥልጣናት ከኀላፊነት ሲነሱ በመከላከያው ኩባንያ የሚቀጠሩ ሲሆን በተዘዋዋሪ ወደ መንግሥት የሥራ ሃላፊነታቸው የሚመለሱበት ሥርዓት ነው በማለት ያስቀምጠዋል። [በዚህ የሥልጣን ቦታ በመቀያየር የሚሰየሙ የኩባኒ ባለቤቶች በመንግሥታዊ ሥልጣናቸው በሚሰሩባቸው ግዜአት ለአደገኛ ንግዳቸው ድጋፍ የሚሰጥ ፖሊሲ እንዲቀረጽ በማድረግ የግፍ ሀብት ማካበቱን ሕጋዊ አስደርገው ወደ ቦታቸው ይመለሳሉ።]
ችግሩ ከዚህም የሰፋ ነው። የደህኅንነት ምክር ቤቱ አባላት የጦር መሣርያ ንግድ ስምምነቱ መንግሥታት በሕግ ተከልለው እንዳሻቸው በጀታቸውን በመከላልከያ ላይ እንዲያፈሱ ካደረገላቸው ምን ገዷቸው። በተጨማሪም ከ1947 ጀምሮ የዓለም የንግድ ድርጅት (World Trade Organisation) የጦር መሣርያ ንግዱ ከሁሉም የንግድ ቀረጥ ስምምነቶች ውጪ እንዲሆን አድርጎታል።[ይህ ለሕክምና መድኀኒትና ለምግብ አንኳ ያልተደረገ ፖሊሲ ነው።] ዓለም አቀፉ ንግድ የሚሠራው የተባበሩት መንግሥታት እና የዓለም የንግድ ድርጅት በደኅንነት ምክር ቤት አባላት የሚሸጡትን የጦር መሣርያዎች መንግሥታት ያለምንም ገደብ ገንዘባቸውን እንዲያፈሱባቸው አስፈላጊውን ኃይል ተጠቅመው እንዲያመቻቹ ነው። በያንዳንዱ ዓለም አቀፍ ንግድ ስምምነት፤ ስምምነቱ ለብሔራዊ ደህንነት አስፈላጊ ነው ተብሎ ከሚታሰብ ምንም አይነት ፖሊሲ ነፃ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሐረግ በውስጡ እንዲገባ ይደረጋል። ይህ ቀዳዳ ገደብ የሌለው ወታደራዊ ወጪ እንዲኖር የሚያስችል ነው። እንደዚህ አይነቱን አካሄድ መንግሥታት ከጦር መሣርያ ሰምምነት ጋር በተያያዘ ራሳቸው ባወጧቸው ሕጎች ላይ ሲንጸባረቅ ይታያል። ምዕራባውያኑ መንግሥታትም በራሳቸው ሕዝብ ላይ መሣርያዎቹን ለሚጠቀሙ ሀገራት የመሸጥ መብታቸው እንዲጠበቅ መጠየቁን እና ራሳቸውም ማስጠብቁን ቀጥለውበታል። የጦር መሣርያ ነጋዴዎችም ንግዱ የሚተዳደርባቸውን ደንቦች ሲጥሱ እንኳን ተጠያቂ ሲሆኑና ሲቀጡ አይታይም። ይህን ለማሳየት አሁንም በምጽፍበት ሰዓት እየተካሄደ ያለውን የየመን ጦርነት መመልከት ከበቂ በላይ አጥጋቢ ነው። እንደ ኔዘርላንድ፣ ስዊድን እና ስዊዘርላንድ ያሉ ሀገራት “በራሳቸው ሕዝብ ላይ ጦር መሣርያዎቹን ለሚጠቀሙ ሀገራት መሸጥ ህገወጥ ነው” ሲል የጦር መሣርያ ንግድ ስምምነቱ ያጸደቀውን እውቅና በመስጠት ተራውን ሕዝብ በቦንብ እንደምትደበድብ ለተረጋገጠባት ሳውዲ አረብያ መሣሪያ ሽያጩን ከልክለዋል። ታድያ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እንዲሁም አሜሪካ ከትናንሽ ጀምሮ እስከ ከባድ መሣርያ ለሳውዲ መሸጣቸውን የቀጠሉ ሲሆን። እንግሊዝም ድርጊቷን የኮነኑትን አካላት “በዚህ ውሳኔያችሁ ሌሎች ሀገራት የጦር መሣርያ ንግድ ስምምነት ውስጥ እንዳይገቡ እያደረጋችሁ ነው” ብላ እስከመንቀፍ ደርሳልች። እንግሊዝ ይህን መሰሉን ድርጊት የመፈጸም ረጅም ታሪክ አላት። በ1970 ቺፍቴይን ታንኮችን (Chieftain Tanks) በተማሪ ሰልፈኞች ላይ ሲጠቀም ለነበረው ለኢራኑ አጼ ስትሸጥ እንደነበር የታወቀ ነው።
የመሣርያ ንግዱ ከሌሎች ንግዶች አንፃር በጣም ግልጽነት የጎደለው ሲሆን ሕዝብ ሳይመረምረውና ሳያውቀው ስምምነቶች የሚፈጸሙበት ሥውር ዓለም ነው። በዚህ ሥርዓት የሚሳተፉ ካምፓኒዎችና መንግሥታቶቻቸው በሙስና የተጨማለቁ መሆኑም የሚያስገርም አይደለም። በ2010 የእንግሊዙ ኩባንያ ቢ.ኤ.ኢ. (BAE)(የዓለማችን ሁለተኛ ግዙፍ የጦር መሣርያ አምራች) በምሥራቅ አውሮፓ ያለውን ንግድ ለማጠናከር ሙስናን አቋራጭ በማድረጉ አራት መቶ ሚልዮን ዶላር ተቀጥቷል። ቢ.ኤ.ኢ. በሚልዮኖች የሚቆጠር ዶላር በስዊስ ባንክ ( Swiss bank) በኩል ክፍያ ሲፈጽም እንዲሁም ሐሰተኛ የሂሳብ አያያዝና አሳሳች መግለጫዎችን ሲሰጥ የነበረ ድርጅት ነው። በ2006 ሲሪየስ ፍራውድ ኦፊስ ( Serious Fraud Office) በቢ.ኤ.ኢ. ላይ የጀመረው ምርመራ የተቋረጠ ሲሆን ይሔም የሆነው የሳውዲ ባለሥልጣናት በሙስናው ተሳታፊ በመሆናቸው እንዳይጋለጥ በመፍራት ጣልቃ በመግባታቸው ነው።
ዋናውን ሥዕል ስንመለከት ግልጽ ሆኖ የሚወጣው መንግሥታት የጂኦ-ፖለቲካ ፍላጎቶቻቸውን ለማስፈጸም ከሚጠቀምባቸው ቁልፍ መንገዶች አንዱ የጦር መሣርያ ግብይቱ የሚፈጥረውን ጫና በመጠቀም በአገራት መካከል ግጭት፣ በአገራት ውስጥ ድኅነት እንዲጠናከርና በጎረቤታሞች መካከል ምንም አይነት ዘለቄታዊ የልማት ትብብር እንዳይኖር ማድረግ ነው። በመንግሥታት ደረጃ የሚደረጉ ንግግሮች አብዛኛውን ጊዜ የሚያተኩሩት የኒውኩሌር መሣርያን ስለመቆጣጠር በመሆኑ መገናኛ ብዙኃኑም በሰፊው ሽፋን የሚሰጡት ይህንኑ ነው። ነገር ግን በስፋት እየተገበየ ስላለው የተለመደው የጦር መሣርያ ግን እምብዛም አይዘገብም። በመሆኑም እውነታው ይፋ ሊሆን አልቻለም። አሜሪካ፣ ፈረንሳይ እንዲሁም እንግሊዝ እርዳታ ለሚሰጧቸው ታዳጊ ሀገራት ከሚሸጡት የጦር መሣርያ አብዝተው ያተርፋሉ። ታድያ እነዚህን እርዳታዎች የሚያገኙትን ሀገራት በጥንቃቄ ይመርጣሉ። ለምሣሌ ህንድ ከእንግሊዝ እርዳታ ተቀብላለች ይሁንና በጦር መሣርያ ግዢው ቀዳሚ ደምበኛ መሆኗን ቅጥላለች። [ኃያላኑ ፊት ለፊት እያሳዩ በጦር መሣሪያ መልክም ሆነ በሰብአዊ እርዳታ ስም ከሚሰጡት ገንዘብ ብዙ እጥፍ በሰውር ከተቀባዮቹ አገራት መልሰው በመውሰድ ድኽነትንና ጥገኝትን ዘለቄታዊ፣ መዋቅራዊና ሥርዓታዊ ደርጉታል።]
የኢኮኖሚ ቀውሶችን ተከትለው የወጡት ጥብቅ ፖሊሲዎች በተለያዩ የማኅበረሰብ አካላት ላይ ጫና ያሳደሩ ሲሆን የጦር መሣርያ ገበያውም የዚህ ገፈት ዋና መነሻ ነበር። የጦር መሣርያ አምራች ድርጅቶችም እንደማንኛውም ሌላ ድርጅት አዲስ ገበያ ለመፈለግ ተገደዋል። ታድያ ለቢዝነሱ ከጦርነት ወይም ከጦርነት ሥሥጋት በላይ ምን የተሻለ ገበያ አለ። ጄ.ደብሊው.ስሚዝ( J.W. Smith) የዓለም የባከነ ሀብት( The World’s Wasted Wealth) በተሰኘ መጽሐፉ ሁለቱ መንግሥት እና የጦር መሣርያ አምራች ድርጅቶች በታዳጊ ሀገራት ጣልቃ በመግባት ከሌሎች ሀገራትና ከአሸባሪዎች ሥጋት እንዲሰማቸው ሁኔታዎችን በማመቻቸት መልሰው መሲህ በመምሰል ከጦርነት ጋር የተያያዘ ፖሊሲ አንዲያወጡ እንደሚገፋፉ ገልጿል። የጦር መሣርያ አቅራቢዎች የአንድን ሃገር የመከላከያ አቅም አጋኖ የሚያሳይ የሐሰት መረጃ በማውጣት የጦር መሣርያ ግዢው እንዲጨምር ያደርጋሉ። ከዚሁ ጋር የጦር መሣሪያ ፋብረካውን ግብር ለመቀነስ መንግሥት ድጎማ ያዘጋጃል ይህም ማለት እኛው ግብር ከፋዮቹ የጦር መሣርያ ኢንዱስትሪውን እንደጉማለን። በዚህ መንግሥት ሕዝብ ሀብት ወደ ሞት ነጋዴዎቹ ይዛወራል፣ ብዙኃን ወደ ድኽነት እየተገፉ ሞራል የሌላቸው የመንግሥት ባለሥልጣናትና የጦር መሣሪያ ነጋዴዎች ሀብት ያካብታሉ። የሰው ልጅንም ሞትና ስደት ያባብሳሉ።
ከ9/11ኑ ክስተት በኃላ [September 11, 2001/መስከረም 1-1993ዓም የኒውዮርክ የንግድ መዓከል በአሸባሪዎች የወደመበት ቀን] የአሜሪካ መንግሥት የጦር መሣርያ አምራቾች ቀድመው ተዘግተው ወደነበሩ ገበያዎች እንዲመለሱና የንግድ መረቦቻቸውን እንዲያሰፉ እድሉን አመቻችቶላቸዋል። ጆርጅ ደብሊው.ቡሽ አሜሪካ ከሽብርተኝነት ጋር እያደረገች ባለችው ጦርነት ለሚሳተፉ ሀገራት ጦር መሣርያ መሸጥ ብቻ ሳይሆን ሊለገሳቸው ይገባል በሚል ጦር መሣርያ ሚሸጥላቸውን ሀገራት ዝርዝር ከልሷል። በዚህ አዲስ ውሳኔ መሠረት ከጥቃቱ አስቀድሞ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት ጦር መሣርያ እንዳይሸጥላቸው ገደብ ለተጣለባቸው ሀገራት ሳይቀር ሽያጭ እንዲፈጸምላቸው አድርጓል። ጆርጅ ቡሽ በፀረሽብር ትግሉ አስተዋጿቸው በወል ለማይታወቅ ወይም ድብቅ ሚና ለነበራቸው ሀገራትም ጭምር ለድጋፍ የሚሆን ሦስት መቶ ሚሊዮን ዶላር እንዲጸድቅ አስችሏል። በሌላ አነጋገር ገንዘቡ ለምን እና ለማን እንደደረሰ ተጠያቂ የሚሆን ሰው አይኖርም ማለት ነው። ይህን መሰሉ እርዳታና ድጋፍ አሜሪካ በዓለም ያላትን ተጽዕኖ እንድታሰፋ እንዲሁም ጨቋኝ መንግሥታት እንድትደግፍ አስችሏታል። አንዳንዶችም ይህ ተግባር አሜሪካን የአምባገነኖች ደጋፊ አድርገው የሚያዩ አክራሪ የፖለቲካና የእምነት ቡድኖችን ወደመፍጠር ደርሷል ሲሉ ይሟገታሉ። የዓለም የፖሊሲ ተቋም (World Policy Institute) አሜሪካ በተደጋጋሚ ዴሞክራሲያዊ ላልሆኑ ታዳጊ ሀገራት የመከላከያና ትጥቅ እርዳታ እንደምትሰጥ ደርሶበታል። በተጨማሪም ታዳጊ ለሆኑ ሃያ አምስት ሀገራት በትጥቅ መልኩ እርዳታ የተሰጣቸው ሲሆን ከእነዚህም አሥራ ሦስቱ በአሜሪካ የስቴት መምርያ (U.S. State department) ዴሞክራሲያዊ ያልሆኑ ተብለው የተመደቡ መሆናቸውን ገልጧል።
ሥዕሉ የሚያሳየው የጦር መሣርያ ንግዱ ሀብት እና ደኅንነት የማግኛ መንገድ ብቻ ሳይሆን ብሄራዊም ሆነ የውጭ ፖሊሲዎችን የመቅረፅ እና የተለያዩ የዓለም ሀገራት ላይ ሥልታዊ ተጽዕኖ የማድረጊያ መንገድ መሆኑን ነው። ለምሳሌ አሜሪካ በቁጥር ሰማንያ የሚሆኑ ኤፍ16 (F16’s) የጦር አይሮፕላኖችን (ዋጋቸው ወደ ሃምሳ ቢልዮን ዶላር የሚጠጋ) ለተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ እንዲሸጥ ለኩባኒያዎቿ ፈቃድ ሰጥታለች። ታድያ በአረብ ኤሚሬትስ የጦር ሰፈር ለመገንባት አስቀድማ ይሁንታውን አግኝታለች፤ ይህ የፐርዥያን ባህረ ሰላጤ (Persian Gulf) ለመቆጣጠር ያስችላታል። በሰብዓዊ መብት ጥሰት በምትታወቀው ቱርክም ሌሎች የጦር ሰፈሮችን ገንብታለች። እነዚሁ የጦር መሣርያ ነጋዴዎች ለሁለቱም ለፓኪስታንም ለህንደም መሣርያ ይሸጣሉ። እንደውም ደረጃቸው ከፍተኛና ውስብስብ የሆኑ ሌሎች ሀገራት እየታጠቋቸው ያሉ የጦር መሣርያዎችን ለምርምር እድገቱ ግብዐት እንዲሆን እና ለመሣርያዎቹ መዘመን እንዲረዳ በተግባር እንዲሞከሩ [እርስ በዕርስ ወይም በጎረቤታሞች ሀገራት መካከል ጦርነቶች በመቀስቀስ አገልግሎት ላይ እንዲውሉና የመሣሪያዎቹን አቅም እና እንዴት ማሻሻል እንደሚችሉ ለማጥናት] በነጻ ይሰጣሉ። አብዛኛውን ጊዜ ፖለቲከኞች ወደሌሎች ሀገራት የሚያደርጓቸውን ጉዞዎች ለሰብዓዊ እርዳታ ወይም ለዲፕሎማሲ እንደሆነ ይናገራሉ። እውነታው ግን ለጦር መሣርያ ኩባንያዎች ስምምነቶችን ለመፈጸም ነው። በ2002 ቶኒ ብሌር (Tony Blair) ወደ ህንድ ባደረገው ጉዞ ለመገናኛ ብዙኃኑ የመሬት መንቀጥቀጥ ስለሚያመጣው ትጽዕኖ እንዲሁም በህንድና በፓኪስታን መካከል ያለውን ግጭት ስለማስቆም ንግግር ሲያደርግ ቆይቷል። በኋላ ግን አብዛኛውን ቆይታውን ያሳለፈው የሕንድ መንግሥት ሥልሳ ስድስት ሃውክ የጦር አይሮፕላኖችን (Hawk jets) እንዲገዛ በማስማማት እንደነበር ተጋልጧል። ፖለቲከኞቻችን ስለራሳቸው እና ስለ ሥራቸው የሚነግሩን እኛን ለማገልገልና ፍትሕ እንዳይጓደል ለማድረግ እንደሚሠሩ አምነን እንድገዛላቸው ነው። እውነታው ግን የሚሠሩት ለእነዚሁ ግዙፍ የጦር መሣርያ አምራቾች መሆኑን በቀላሉ የደረስናበቸው መረጃዎች ያጋልጣሉ።
የቀድሞ የአሜሪካ መሪ አይዘንሃወር (President Eisenhower) በመሰናበቻ ንግግሩ ህዝቡን ሲያስጠነቅቅ “ከመከላከያ ኢንዱስትሪ ኮምፕሌክሶች የሚመጡትን አስፈላጊም ሆኑ አላስፈላጊ፤ አግባብነት ከሌላቸው ትጽዕኖዎች ራሳችንን ልንከላከል ይገባናል። እያደገ ያለና ማደጉንም የሚቀጥል ያለቦታው የሚገኝ አደገኛ ኃይል እየመጣ ነው” በማለት ተናግሯል። በእውነትም ይህ ያለቦታው የተቀመጠ ኃይል ልንቆጣጠረውና በሕግ ልንወሥነው በማንችለው መልኩ ማደጉን እየተመለከትን ነው። ይህን ኃይል በእጁ ያስገባ አካል ጦር መሣርያን ከመነገድ እና ከመጠቀም የበለጠ ነገር ይቆጣጠራል። በጦር መሣርያ ንግዱ ዙራያ የተተበተበውን ሙስና እና ማጭበርበር እንዲሁም የሚወስኗቸው ወደ ጦርነት የሚመሩ ውሳኔዎች ከተመለከትን በኋላ ከእነዚህ ሁኔታዎች የሚጠቀመው እንዲሁም ይህን የሚያበረታታው ማን ይሆን? ብሎ መጠየቁ ብልኅነት ነው። በተጨማሪም መገናኛ ብዙኃኖቻችን ምን እየተከወነ እንዳለና ስለሚካሄደው ድብቅ ዓላማን የማሳካት ሂደትና ድርጊት ለምን እንደማያስጠነቅቁን መጠይቅ ይገባል።
ለአገራችን ለኢትዮጵያ ከዚህ ምን እንማር ብለን በዯለንበት ይወያይ
1. ኢትዮጵያኖች ከዚህ ምን እንማራለን? ምንስ ማድረግ አለብን?
2. ዓለም አቀፍ ጣልቃገብነት በራሱ ከባድ ፈተና ሲሆን እኛ በገዛ አገራችን በቦታና በቋንቋ፣ በአምነትና በፖለቲካ ልሒቃን የትርክት መሥመር መከፋፈላችን ምን ያህል ውስብስብ እዳ ውስጥ ይከተናል?
3. የአርሻ መሬታችን በምእረባዊያን የኬሚካል ማዳበሪያ የሚሠራ፣ ትምህርት ቤቶቻችናና ሕጎቻችን ከውጭ የሚቀዱ፣ አዳዲስ እምነትን አንደሸቀጥ ወደ አገር ማስገባት ላይ በሚገኙ የፖለቲካ ልሒቃን የምንመራ እኛ ምን ወደ ምን አይነት ጥልቅ፣ ሁለገብ ጥገኝነት አንደሆነ ምን ያህል አስተውለናል? እንዴትስ አንደምንወጧ እየተነጋገርንና እየሠራን ወይስ በጭፍን መንጋንተ አጀግነን በምንከተላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ታውረድ ወደ አጠቃላይ ጥፋት እየተጣደፍን ወን?
4. እኔ፣ አንተ፣ አንቺ፣ አንዴት ብናስብ፣ ምን ብንመኝ፣ ምን ማድረግ ብንጀምር ይሆን ራሳችንን አድነን አገራችንን ለቀጣዩ ትውልድ በክብር የምናስረክበው?
---- ሁሉም ባለበት ይወያይ!!!
ይህን ምዕራፍ ቀነጫጭቤ ለብዙ አንባቢያን ውይይት እንዳቀርብ ለፈቀደልኝ ለአቶ ፋንታሁን ዋቄ የከበረ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። እግዚአብሔር ዕድሜና ጤና ሰጥቶ የበለጠ እንዲያገለግሉን ያድርግዎ።
ቱምሳ ዹጋ
ከነቀምት/ወለጋ
Telegram: https://t.me/+io2m-XA1OBE2NmM0
YOUTUBE:- https://www.youtube.com/@Orthodox_Secular_FantahunWakie/videos
ትዊተር፦ @fwakie
FB:- https://www.facebook.com/fwakie
Blog:- https://ethiopiaorthodoxchristian.blogspot.com
አስተያየቶች