ኦርቶዶክሳዊነትና የፖለቲካው ትክክለኝነት ( ዘመናዊ ሥዝም ኑፋቄ ነው)
ፋንታሁን ዋቄ
ህዳር 2013
ኦርቶዶክሳዊነትና የሰይጣን
መንግሥት ከሚለው መጽሐፍ መግቢያ ተወስዶ ተስፋፍቶ የተጻፈ
ይህ ኑፋቄ ስነኳንስ ሕዝባዊውን ጳጳሳትን፥ መነኮሳትን፥ ካህናትን፥
የባህል መሪዎችን፥ ሙፍቲዎችንና ዑስታዞችን፥ ሰባኪያነ ወንጌል ሁሉ የበከለ የፍትሕ፥ የእውነት፥ የሰብአዊነትና የማኅበረሰብ አጠቃላይ
አጥፊ ሆኖ ተከስቷል። የፖለቲካ መሪዎች፥ የሲቪልና የቢሮክራሲ ባለሚያዎች፥
በአንድ የሥራ ጽ/ቤት ውስጥ ያሉ ተዋረዳዊ ግኑኝነት ያላቸው ሠራተኞች ሳይቀር የሚነጋገሩት ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን ታሳቢ አድርገው
ነው።
ሐሰትና እውነት፥ ፍትሕና ግፈኝነት፥ ሰብአዊነትና አራዊትነት፥
እኩል በዓለአገራዊነት፥ ክብረ-ሰብእ የመሳሰሉት ወሳኝ የመኖር ትርጉም መሠረታዊ እሤቶች ሁሉ ዋጋ አጥተዋል። በዚህ ጉዞ መእመናንና
ዜጎችም በየበኩላቸው በተክርስቲያንን ትተው የሚያስደስቱትን ጳጳስ ቆሞስ፥ ዜገችም የአገራቸውንና የትውልድ ነገር ትተው በወቅቱ ሥልጣን
ላይ ያሉትን ለማስደሰት ፖለቲካዊ ትክክለኝነታቸውን ጠብቀው የሚናገሩ፥
የሚያደርጉና ግኑኝነት የሚፈጥሩ ናቸው። ስለ እውነት፥ ስለ ፍትሕ፥ ስለ ክብረ-ሰብእ፥ ስለ ቤተ ክርስቲያንና አገር፥ ስለ ሕዝብና
መጭው ትውልድ ጥቅም የሚናገር የለም። አብዛኛው በፖለቲካዊ ትክክለኝነት
እግዚአብሔርን ሳይቀር እንደሚገባ በአምልኮታቸውና በአርአያነት ሊመሰክሩ አልቻሉም።
ፖለቲካዊ ትክክለኝት ሲገለጥ፦
የየዘመኑን ፖለቲካ
(የየዘመኑ ፖለቲካ መሠረቱ በየዘመኑ የበላይነት የሚጎናጸፍ ነፅሮተ ዓለምና ፍልስፍና
ነው) ለመምሰልና
ለማስደሰት መናገር እና እግዚአብሔርን ለማስደሰት መኖር
በአንድነት አይገኙም። ይጋጫሉ። እግዚአብሔርን ለማስደሰት የሚኖር
ኦርቶዶክሳዊያን
በእምነታቸው መኖር ከፈቀዱ ከሁሉቱ አንዱን መምረጥ የግድ ይላቸዋል።
ፖለቲካዊ ትክክለኝነትና
ኦርቶዶክሳዊ ክርስቶሳዊነት አብረው አይገኙም።
በምዕራቡ ዓለም Political Correctness (ፖለቲካዊ ትከክለኝነት) የሚባል አነጋገር የቆየ ባህል ነው። ዓለም ከእግዚአብሔር እውነት በራቀ መጠን በየዘመኑ የፖለቲካና የሀብት አቀም ያበጁ ልሒቃንን ፍልስፍና እና ፍላጎት የሚያጠናክር ወይንም የማይነካ አነጋገር በመለማመድ የሥጋ ኑሯአቸውን ያመቻቻሉ፣ ከመከራና ከስደት ራሳቸውን ይጠብቃሉ።
ይህ ባህል የኖረ ነው። በመጀመሪያው 300 የክርስትና ዘመን ቁስጥንጢኖስ እስኪጠመቅና ቤተመንግሥቱ ሃይማኖቱን ብሔራዊ
ከማድረጉ አስቀድሞ ይጠመቁ የነበሩ ክርስቲያኖች ሁሉ ለሰማዕትነት ሲዘጋጁ ነበር። ቤተመንግሥቱ ከተጠመቀ በኃላ ግን ብዙዎቹ
ክርስቲያኖች የክርስቶስ በመሆን የሚመጣውን መስቀል ለመሸከም
ሳይሆን ከቤተመንግሥቱ በመዛመድ የሚገኘውን የሥጋ ድሎትና ክብር በመሻት እየሆነ ልማድ ተጀመረ።
በአሁኑ ጊዜ ክርስቲያኖችን የሚናገሩትን እና የሚያስተምሩትን በአፍ እና በጽሑፍ የተገኘ ሁሉ እየተከታተሉ እውነት ተነጋሪዎችን በማሸማቀቅ ክርስቶሳዊ (ፍጹም አምላካዊ አስተምህሮ) አስተሳሰባቸው ከአሁኑ እና ከሚመጣው ትውልድ የተሰወረ ሆኖ አንዲቀር የቻሉትን ሁሉ እኩይ መንገድ ይጠቀማሉ።
ፍጽምት እውነት፥ ይህን የሚያደርጉት ጊዜ የሰጣቸው አካላት በአክራሪ ሴኩላሪዝም፣ በአክራሪ ፕሮቴስታንት፣ በፌሚኒስት ግሩፕ፣ በኤቲስት እና በአክራሪ ኢሳላም ርእዮት የሚመራ ወይንም የእነዚህ ትብብር የጋራ ጠላት ነው። ከአምስቱ መካከል እምነታዊ ዶግማ ያለውና ለታክቲካዊ ምክኒያት የሚተባበረው አክራሪ ኢስላም ብቻ ነው። ሌሎቹ መዳረሻቸውን ክህደት አድርገው የሚሠሩ የሴኩላሪዝም አጃቢዎች ናቸው። ነገር ግን አምስቱም የእግዚአብሔርን እውነት ከክርስቶስ ተቀብላ የምትኖረዋን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በማዳከም፤ በማሳደድና በማጥፋት ይስማማሉ።
ጥፋታቸውን ከሚሸሽጉበት አጀንዳዎች መካከል መዘመን፣ መሰልጠን፣ መበልፀግ፣ ማደግ፣ መሻሻል ወዘተ የሚሉ አጓጊ፥ ነገር ግን በተግባር የሚጠሩበትን መጠሪያ የሚቃረኑ ቃላቶች ነው።
እንዚህ ለጆሮ የሚያምሩ፥ ተጠቅመው ሲሆኑ ውጤቱ ግን ተቃራኒ ሆኖ ሲገለጥ ዓይናቸውን በጨው አጥበው ማስመሰሉን ይገፉበታል። እነዚህ አጓጊ ፕሮፓጋንዳዎች በተግባር ለዓለም ያስገኙትና እየሆነ ያለው ጥቂቶችን ማበልፀግና ብዙኃኑን ወዶ አደር ባሪያ ማድረግ፣ ግብረ ሰዶማዊነት፣ የትዳር መፍረስ፣ ግጭት፣ በሽታ፣ የተፈጥሮ ሀብት መመናመንና መበከል፣ ስደት፣ ጥላቻ፣ የጅምላ ጨራሽ መሣሪያ ክምችት፣ ውርጃ፣ ተዋልዶን በመጥላት የሚመጣ መምከን፣ ራስን ማጥፋት፣ የሕይወት ትርጉም መዛባት ወዘተ ነው።
ይህን በተግባራዊ ሕይወት ሊመሰክሩለት የማይቻል እውነታ በአነጋገር ማሰማመር፣ በቴሌቪዥን መስኮት አምሮና ተውቦ በመቅረብና በማስታወቂያ ስሕበተ ኃይል የሕዝብን ስሜት ማጓጓት፤እውነታውን የሚያጋልጡትን በፖለቲካ ማሸማቀቅ ዋናው ስልት ነው። በዚህ ምክንያት፣ ሰው ሁሉ በየትኛውም፣ ቦታ ጊዜና ሁኔታ ይህን ውድቀት የማይወቅስና የማያጋልጥ አነጋገር፣ ትምህርትና የኪነጥበብ አቀራረብ ብቻ አንዲያቀርብ ጫና ይደረግበታል። ይህ ዓይነት የምሁራዊ እይታ ፖለቲካዊ ትከክለኝነት (Political correctness) ይባላል።
ፖለቲካዊ ትክክለኝነት እውነትን፣ ፍትህን፣ ቅድስናን፣ ሞትን እና ሕይወትን ታሳቢ ከማድረግ በመቆጠብ በየወቅቱ የበላይነትን ከያዙ አካላት ፍልስፍና ጋር ራስን ማስማማት ብቻ ነው።
ፖለቲካዊ ትክክለኝነት ራሱን የቻለ የሊብራሊዝም ድብቅ ሃይማኖታዊ ዶግማ ነው። ክርስትና እውነትንና ቅድስናን በእግዚአብሔር ትምህርት እንደሚመዝን ሁሉ ፖለቲካዊ ትክክለኝነትም የሌብራሎችን የበላይነት ለማስፈን፤ ሕይወት እና እውነት የሚታይበትን ኦርቶዶክሳዊ ክርስትናን ለማጥፋት ለሚደረገው አጀንዳ የሚያገለግል መሣሪያ ነው።
ሊበራሊዝም እምርታን (ፕሮግሬስ/መሻሻል) የሚረዳው የሰውን ልጅ ቁሳዊ የሕይወት ዘርፍ ለመለወጥ አስተሳሰቡን መለወጥ የግድ እንደሆነ፣ አስተሳሰቡን ለመለወጥ እምነትን መለወጥ ቀዳሚው እንደሆነ አጥብቆ ያምናል።
ለዚህ የሰውን ሁሉ አስተሳሰብ መቆጣጠርና መምራት አጀንዳውን ለማሳካት የሚያስፈልገው የንግግር መልእክቶችን ይዘት መቆጣጠር፤ ይህን ለማድረግ ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን ማንገሥና አግዚአብሔራዊ እውነትን ከአደባባይና ከትምህርት ውስጥ በሳይንሳዊነት ስም ማሰወገድ ነው።
ቋንቋን መቆጣጠር ፖለቲካዊ ትክክለኝትን በማገልገል ለእውነትና ለፍትሕ ባዕድ እንዲሆን ማድረግ
የሊብራሊዝም
ወደ መጨረሻው የክህደት መዳረሻ ጎዚ(ምን ማለት ነው?) ዋና ሞተር ነው። ይህንን ሞተር የእኛ አገር ኮሚኒስቶች፣ ሴኩላሪስቶች በተለይ የብሔረሰብ ንዑስ ማንነትን ሃይማኖት-አከል አድርገው ሰውን የሚሰዉለት ዘረኞች
ተሳፍረውታል። ለመዋሸት፣ ለመቅጠፍና ሐሰታቸውን በትወልዱ ላይ ለመጫን መልካም አጋጣሚና ፍልስፍና አድርገውታል። ጆርጅ ኦርዌል፣ ዶሰቶቪስኪና ኒቼ በተለያየ መንግድ ይህን አስተሳሰብን በቋንቋ በኩል የመቆጣጠር አሠራር በጽሑፎቻቸው በቀጥታና በተዘዋዋሪም ቢሆን አመልክተውናል።
እነዚህ የፖለቲካ ትክክለኝነትን ለማመልከት ጥቅም ላይ ከሚውሉ የታወቁ አነጋገሮች መካከል --- ዘረኛ፣ ትምክህተኛ፣ እገሌ-ጠል፣ ነጭ/ጥቁር ወይን የእገሌ ብሔረሰብ ልዩ ጥቅም/ጉዳት፣ ጾታዊ ትንኮሳ፣ የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂነት፣ ወዘተ የሚሉና ሰዎች ሲናገሩ ላለመፈረጅ ራሳቸውን ሳንሱር የሚያደርጉባቸው ቃላት ሊሆኑ ይችላሉ።
እንደዚህ አይነት ቃላት ተፈጥረው የሚሰራጩት የበላይነት በያዙ አካለት በተለይ
በልሒቃን፣ በፖለቲካ ሰዎችና የዘመኑ ታዋቂ ሰዎች ስለሚሆኑ
አጠቃቀማቸው ምንም አይነት ህግና መሥፈርት አይበጅለትም፤ እንደተፈለጉ በማሸማቀቂያነት ሥራ ላይ ይውላሉ።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ አንድ እምነትና ባህል፣ ዶግማና ቀኖና ያለው ሰው
ምንም እውነት ቢኖረው፣ ምንም ለፍትሕ መቆም ቢገባው ምንም ከማድረጉ አስቀድሞ ከቃላቱ አንፃር ራሱን በተቀመጡለት
የፖለቲካ ትክክለኝነት መሥፍርት ሳያፈርስ ለመናገር ሲል እውነትን ሳይናገር
ይቀራል፣ ለፍትሕ ሳይሟገት ራሱን ይገታል። ሥነ-ምግባር፣ ሞራል፣ ሃይማኖት ከማሰቢያችን አካልነት ሳይወገዱ ግን ራሳቸውን እንደገለፁ በማድረግ በአፍ፣ በመጽሐፍ፣ በትውፊት ወደሚቀጥለው ትውልድ ሳይተላለፍ ይቀራል። አዲሱ ትውልድ ከወላጆቹና ከቀዳማዊያኑ፣ ከእምነቱና ከባህሉ ምንም ሳይወርስ በሌብራሊሰቶች የአስተሳሰብ ማኅቀፍ ውስጥ እስረኛ ሆኖ ይቀራል።
ይህ የፖለቲካዊ ትክክለኝት ውጤት ነው።
በ1960ዎቹ በምዕራባዊያን መምህራኖቻቸው አእምሮአቸው ታጥቦ አገራዊ ማንነታቸውን በመክሰስና ባእድን በመናፈቅ የሚታወቁት ተማሪዎች አዲስ መፍጠር የተመኙትን አገርና ማኅበረሰብ ለመገንባት አግባብነት ያለው ርእዮት ተውሰው ነበር። ይህን የተውሶ ርእዮታቸውን በቀጣዩ ትውልድ ላይ ለመጫንና ቀዳሚዎቻቸውን በማሸማቀቅ በትውልዱ መካከል የአስተሳሰብ ሽግግር እንዳይኖር ነባር እሴትን የሚገልጡ አነጋገሮችን በሙሉ አሉታዊ ትርጉም ይሰጡታል፤ በአንፃሩ የተውሶ ሆነው ለአገራዊ እምነትና ባህል ተቃራኒ የሆኑትን ቃላት በአዎንታዊና ወደፊት ከሚመሰረተው ምቹ ምናባዊ አገር ጋር አያይዘው ይነዙታል።
ዘውዳዊ ሥርዓትን ሰው በላ፣ ሰታሊኒዘም አይነቱን ኮሚኒስታዊ ጅምላ ጨራሽ
ሥርዓት በምድር ላይ ገነትን እንደሚመሠርት አድርገው ያቀርቡት ነበር። በጊዜው፣ ይጮኹ የነበሩ ቃላት፡- ጭቆና-ጨቋኝ፣ አድሃሪ፣ ደሃ-ባለፀጋ፣ ተበዝባዥ-በዝባዥ፣ አፈና-አፋኝ፣ የወንድ ትምክህት-የሴት መብት ታጋይ፣ --- ወዘተ ነበሩ። ይህ አዲሱ ሃሳብን ለመቆጣጠር
ተግባር ላይ የሚውሉ ቃላት መርዛማና የሞራል ንቅዘት መነሻ ሆነው የኢትዮጵያን ማኅበረሰብ ከመንግሥት የሥልጣን ቁንጮ እስከ አንድ ቤተሰብ ተፃራሪ መደቦችን በመፍጠር የግጭትና የአገር መፍረስ፣ የማኅበረሰብ የሞራል ውድቀት መነሻ ሆኗል።
ይህን ውድቀት የሚመሩ ጥቂት ልሒቃን ከግጭቱና ከንቅዘቱ ውስጥ ስልጣንና የበላይነት ያገኙበታል፣ ነባር አቅሞችን ሁሉ ያደቁበታል፣ ሕገወጥ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ህጋዊ ሞራላዊ መሠረቶችን ሁሉ ሕገወጥ ያሰኙበታል፣ ነባርና ቀዳሚ ጥበቦች፣ ብልሓቶችን፣ እውቀትና መዋቅራትን ያዋርዱበታል--- በመጨረሻም አገራቸውን ሙሉ በሙሉ ለባእዳን አሳልፈው በመስጠት አልጋ ላይ አንደተኛ በሽተኛ ወደ ፍጹም ጥገኝነት ያስገቧታል።
ኢትዮጵያኖች፣ በተለይ ክርስቲያኖች ይህ ሂደት እውነትንና ፍትሕን፣ ቅድስናና ሰማያዊነትን እያረሳሳ የማትጨበጥ የምድር ላይ ገነት በቅዠት መሰል ፕሮፓጋንዳ እየጋተን ከመስቀል እንድንርቅ ያደርገናል።
መስቀልን ሽሹ እያለ በሽብርና ጭንቀት፣ በሐሰትና በቅዠት መኖር የዘላለም ሕይወትን የሚያሳጣ መንገድ እንደሆነ ባለፉት 50 ዓመታት አይተናል።
የቋንቋ መጣመምና ለፖለቲካ ትክክለኝነት መኖር ሞራልን
ያዘቅጣል፣ ሃይማኖትን ያስለውጣል፣ ሐሰትን ያነግሣል።
ፖለቲካዊ ትክክለኝነት ራሱን የቻለ እምነት (ከልት) ነው። በሃይማኖት ዶግማና ቀኖና የሰው ልጆችን መላ ሕይወት ለድኅነት መሠረት፣ ግርግዳና ጣሪያ አጥርና ማገር ሆኖ አንደሚያገለግል ሁሉ
ፖለቲካዊ ትክክለኝነት ሰዎች የዘመኑ አሸናፊዎች የፖለቲካ ሥልጣንን፣ መገናኛን፣ ሀብትን፣ መደበኛ ትምህርትን፣ ኪነጥበብን ጠቅለለው በመያዝ በሚያደርጉት ጫና ለአሸናፊዎች ምናባዊ ዓለም የሚስማማ ንግግርና አስተሳሰብ ለመያዝ ሲሉ ራሳቸውን የሚያቅቡበት እሥርቤት ነው።
በዚህ እምነት የተጠለፈ ሰው ሌሎች በትክክል የሚያስቡ፣ እምነት፣ ባህል፣
የራሳቸው ነባር ፍልስናና ርእዮተ ዓለም ያላቸውን ሰዎችና ማኅበረሰብ ኃላቀር፣ የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ፣ የዲሞክራሲና የብልጽግና እንቅፋት፣ ለዘመናዊነት የማይመቹ፣ ዘረኛ፣ እገሌ የሚባል ክፍለ-ሕዝብ የማጥቂያ መሣሪያ፣ ሴት-ናቂ፣ ኢስላም-ጠል፣ እንትን-ጠል ወዘተ
በማለት ምንም ዓይነት እውነትን የሚመለከቱ ውይይቶችና ትምህርቶች እንዳይደመጡ ይደረጋል።
እድገት፣ ለውጥ፣ እምርታና መሻሻል፣ ሊብራሊዝም የተሰኙ ቃላት የሚወክሉት ፅንሰ ሐሳብ ከነባር አውነቶችና ፍትሕ አንፃር ሲመዘኑ ኒቼ የተበላው ፈላስፋ እንዳጤነው እሴቶችን በተለይ ሥነ-ምግባርን እና ሞራልን ገልብጦ በማንበብ አዲስ ስብእናን ማስተዋወቅ ነው።
ለምሳሌ ያህል አቀራረቡ
ነባሩን የተወደደ እውነኛነትንና
ፍትሓዊነትን፣ ሥነ-መግባራዊነትና መልካም ሞራልን የሚገልጡ ቃላት በመጠቀም ተቃራኒ ትርጉም እንዲኖረው ማድረግ ነው። የእናት ደኅንነትና ጤናን ለመጠበቅ የሚያስፈልግ ውርጃ፣ ስቃይን ለማስቆም በበቃን መሞት፣ የሴቶችን መብት ለማስከበር ፍቺን ሕጋዊ ማድረግ፣ ሁሉም እመነቶች እኩል ሃይማኖቶች ናቸው የሚለውን ክህደት በመቻቻል መግለጽ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን በእምነትና ትወፊት ውርስ እንዳያሰድጉ ለማድረግ የልጆችን መብት ማስከበር በሚሉ ውጤታቸው ከመልካምነት በተቃራኒ የሆኑ ቃላትን አለማምዶ የመንግሥት አስገዳጅ ሕግ ወደመሆን ማሳደግ እና የመሳሰሉት ናቸው። ተራማጅ፣ ዘመናዊ እና ሴኩለር ሊብራል መሪዎች ለእውነትና ለተጨባጭ መልካምነት ሁሉ ተቃራኒ ሆነው የምናገኛቸው ለዚህ ነው።
ብዙዎች ግራ የሚጋቡት ሊብራል ተራማጆች የሚናገሩት ነባር እምነትና ባህል ውስጥ የሚነገሩ ቃላትን ሳቀይሯቸው ተግባራዊ
ትርጉማቸውን በመቀየር
የሕዝቦቻቸውን እሴቶች ሲቃረኑ ነው።
የሊብራል ተራማጆች ቃላት ነባሩን የሕዝብ እሴት የሚገልጽ ቃላት የሚጠቀሙት በተቃራኒው ለሚያልሙት የማኅበረሰብ ግብ ስለሚሆን ከባህሉና እምነቱ ጋር ባይጣጣምም ዜጎች ባይጥማቸውም ፖለቲካዊ ትክክለንነትን በማክበር ቀጣዩ ትውልድ ቃላቶቹን አዲስ ከሚፈጸመው ግብር ጋር እያገናዘበ ናባሩን ትርጉም ያጠዋል።
አገራዊያኑ አዋቂዎችና ሊቃወንት ይህን ተቃራኒ ሂደት ሳይረፍድ
እንዳይቃወሙት ንግሮቹ ታሪካዊና እምነታዊ መሠረቶችን ለመደበቂያነት እያደናነቁ ይናገራሉ [ኦርቶዶክስ አገር ናት እያሉ ኦርቶዶክሳዊያንን ማፈናቀል፣ መግደል፣ ተቋሙን መከፋፈል አንደሚሠሩ የብሔር ፖለቲከኞች ያለ ማደናገሪያ ያለ ንግግር]።
በዚህ ንግግራቸው ሞራላዊ ኃይል አግኝተው የሚተቻቸውን ሁሉ ተሰሚነት ይቀሙታል።
ለዚህ ነው ብዙ ሊብራል ተራማጆች ለእውነትና ለተጨባጭ ማስረጃዎች የማይሸነፉትና እንደ ዲዳ የራሳቸውን ብቻ በትውልድ ላይ የሚጭኑት። ሂትለር፣ ሞሶሎኒ፣ሰታሊን፣ ስብሀት ነጋ፣ አብይ አህመድ፣ ወዘተ
የሺ ዘመናት እሴቶችን፣ የሚሊዮኖችን ጩኸትና ፍላጎት የወከሉ አስመስለው የራሰሳቸውን ሀሳብ በሕዝብ ቋንቋ
ለተቃራኒ ግብ ሲጠቀሙ የሚታዩት።
ዘረኝነት፣ ውርጃ፣ ፅንስ ማስቀረት፣ መናፍቅነት፣ ውጭ-ገብ ርእዮት፣ መለያየት፣ የሀሰት ትርክት፣ ፍቺ፣ በሃይማኖት ጣልቃ መግባት፣
ወዘተ በብዙኃን የተጠሉ ቢሆኑም አዲስ ሊብራል አገር ለመፍጠር የተማማሉ ልሒቃኖቻችን
ተቃራኒውን እየሠሩ በአብረቅራቂ ቃላት ሲሸፍኑ የሚታዩት።
ለዚህ ነው የለውጥ አቀንቃኝ ሊብራል ተራማጆች
የሚሊዮን ኦርቶዶክሳዊያንን መከራ አንዳልሰማ፣ መብቷንና የአገር ባለቤትነቷን እየካዱ፣ እየገደሉና ንበረቷን ባለተጻፈ ሕግ እየነጠቁ የሚቀጥሉት።
ኦርቶዶክሳዊ ሰው ወይንም ሌላው ነባርና ኢትዮጵያዊነቱ የጸና ማህበረሰብና ባህል መብቱን ሲጠይቅ የለውጥ ጠላትና አንቅፋት ተደርጎ የሚፈረጀው።
ለዚህ ነው አክራሪ ኢስላም፣ አክራሪ ብሔርተኛ፣ አክራሪ ሴኩላሪስት አገር ሊያፈርስ፣ ሕዝብ ሊያፋጅና በባዕዳን ላይ ያለንን ጥገኝነት የበለጠ ሲያጠናክረው የሚስተዋለው። ዜጎች አደጋውን ለመቀነስ ሲናገሩ የለውጥ፣ የእድገትና የብልጽግና እንቅፋት፣ የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ ወዘተ ተብለው ድምጻቸው ዋጋ የሚነፈገው። ሰው በጅምላ እየተፈናቀለና እየተገደለ እንኳ ለእውነታው ዲዳ ሆኖ በመቅረብ አብለጭላጭና ጊዜያዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የጀመሩትን የእውነት መቅበሪያ ጉደጓድ በመማሱ የሚፀኑት። ለዚህ ነው የጎሣ ባንክ፣ የጎሣ የፖሊስ ኃል፣ የጎሣ ከተማ፣ የጎሣ ሕገ መንግሥት፣ የጎሣ አሉታዊ ትርክት፣ አሁን ደግሞ የጎሳ ታክሲም መቷል (ጉድ እኮ ነው!) ወዘተ አደጋው በተግባር እይታ እንኳን
እንደ መልካም የለውጥ አቅጣጫ አድርገው የሚገፉበት።
አስተሳሰባቸው ሃይማኖትን የተካ ጭፍን ሆኖ ስለተቀረፀ በተግባር ዜጎች የሚጋቱትን ሕይወት የሚገመግሙትና የሚተነትኑት በፖለቲካ ርእዮታቸው ማኅቀፍ ውስጥ ብቻ በመሆኑ ንግግራቸው ለርእዮታቸው ትክክል የሆነ ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን የጠበቀ ንግግር፣ ውሳኔ፣ ዜናና ሕግ እየሰሩ ይቀጠሉት።
ለምሳሌ አጣዬ የሚባል ከተማ ሙሉ በሙሉ በወደመበት ማግሥት የአገሪቱ ባለሥልጣናትና ርእሰ መንግሥት የመረጃና ደኅንነት ሕንፃ ይመርቃሉ፣ ይህንን በዜና ያሥነግራሉ። በአንፃሩ የከተማ ውድመትና መዋቅራዊ ጥቃቱን ግጭትና አለመግባባት ብለው ይዘግባሉ። ለዚህ ነው ፖለቲካዊ ትክክለኝነት እውነትና ፍትሕን፣ አገራዊ እሴትና ትውፊት የሚያረጋግጥ የሊብራል ተራማጆች ጭፍን ሃይማኖት የሚሆነው።
ሊብራል ተራማጆቹ የማያውቁትና ኢትዮጵያዊያን በግድ
እየተጋቱት ያለው መርዝ
ተራማጆቻችንና የለውጥ አቀንቃኝ ልሒቃኖቻችን ሊረዱልን ያልቻሉትና ሃይማኖታቸው የሚከለክልላቸው ጉዳዮች፡-
ውርጃና ጽንስ ማስቀረትን
ሰዶማዊነትን
አክራሪ የብሔር ፖለቲካን
ሐሰት ትርክትና እርሱን ተከትሎ የሚመጣ መጠላላትና ሞት
በመብትና ነፃነት ስም ሕጻናት፣ ሴቶችና ወጣቶችን በልቅነት ከእምነትና ተውፊት ማስወጣትን
ለጋሥነትና ትብብርን አጥፍቶ ሽሚያና በስስት ላይ የተመሠረተ ውድድር
አገራዊ አምራችን ድጎማ ነስቶ የውጭ ወራሪዎችን በኢነቨስትመንት ስም ዜጋን ባሪያ፣ የውጭ ባለሀብትን ገዥ የማድረግ ፖሊሲ እነዚህን የምንጠላቸውን ነገሮች ሁሉ መንግሥት ይወዳቸዋል። የእኛ እምነት፣ እሴትና ማንነት የሚፈቅደውን መንግሥት ሊብራል ተራማጅነትና ለውጥ የሚለውን ሃይማኖቱን ይዞ ይዋጋዋል። ተራማጅ ሊብራል የለውጥ ኃይሎች ዜጎችን ከማዳመጥ ይልቅ ሁላችንም ስንናገር እውነትና ፍትሕን ሳይሆን በእነርሱ ሃይማኖት መሠረት ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን እንድናከብር “የጥላቻ ንግግር፣ ግጭት ቀስቃሽነት፣ ሕገ-ወጥነት፣ አክራሪነት፣ አለመቻቻል ወዘተ” እያሉ ያስፈራሩናል። ራሳችንን ሳንሱር እያደረግን እንድንናገር ያለማምዱናል። እኛም ስለ እውነትና ጽድቅ ሰማዕትነትን ከመለማመድ
ገበሬው ስለማዳበሪያና ስለ ሰብል ዘር፣ የመንግሥት ሠራተኛው ስለምንዳውና እድገቱ፣ ወጣቱ ሥራ ስለማግኘት፣ ወታደሩ በማዕረግ ለማደግ፣ ካህኑና ሼኹ ለውጥ ተቃዋሚ ላለመሰኘት ወዘተ ሁሉም ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን ጠብቆ ይናገራል። ሁሉም የራሱን ሃይማኖት ትቶ የሊብራል ተራማጆችና የለውጥ አቀንቃኞችን እምነት እየወረሰ ነው።
ሊብራል ተራማጆች ከስብእና የሚያዋርድ የክህደት በር
የሆነውን ኑፋቄ እንደሚራምዱ አይገነዘቡም።
ሊብራል ተራማጆችና የለውጥ አቀንቃኞች ራሳቸውን እግዚአብሔርን እንደሚያገለግሉ አድርገው፤ ለሰው ልጆች ዘመናዊነትን፣ ሥልጣኔንና እድገትን እያመቻቹ እግዚአብሔርን እያስደሰቱ እንደሆነ ያምናሉ። ነገር ግን በለውጥና በተራማጅነት ስም የእግዚአብሔርን ፍጹም፣ የማይለዋወጥ፣ ለቅድስናና ለፍጹምነት የሚያበቃውን የክርስቶስ ወንጌልን በራሳቸው በፈጠሩት የለውጥና የተራማጅነት የኑፋቄ እምነት ለመተካት እንደሚፈታተኑት አይረዱትም።
ይህን ስንገነዘብ የቀደሙት ኦርቶዶክሳዊያን አበው ባላቸው ሙሉ ኃይል ማንኛውንም ኑፋቄ ጊዜ ሳይሰጡትና በቸልታ እንዲስፋፋ ሳይፈቅዱ የሚዋጉበትን ምክንያት እንረዳለን።
በአፄ ሱስንዮስ ዘመን መንገሥት አገርን ለማሳደግ፣ የጦርመሣሪያ ከአውሮፓ ለማቅረብና ወዳጅነትን አጠናክሮ አገር ለመቀየር በሚል የተጀመረው የፖረቹጋል ወዳጅነት ንጉሠን ወደ ካቶሊክ የሁለት ባሕርይ ኑፋቄ አንዲያዘነብሉ ሲያደርጋቸው አባቶቻችን በሰማዕትነት ኑፋቄውን ጨክነው የስወገዱት መዳረሻው ጥፋት መሆኑ ስለሚገነዘቡ ነው።
የዛሬዎቹ ኦርቶዶክሳውያን የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የፖለቲካ መሪዎችና የዩኒቨርሲቲም ሆነ የታችኛው የትምህርት ደረጃ መምህራን
ሲያስቡ፣ ፖሊሲ ሲቀርፁ፣ ትምህርት ሲያዘጋጁ፣ ከሕዝቡ ጋር ሲነጋገሩና መልዕክት ሲያስተላልፉ ስለ ሃይማኖታቸው አያስታውሱም። ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን በመከተል ለትውልዱ ወደ ስህተት መግባት፣ ለእውነትና ለፍትሕ መቆምን ከማንነታቸው አስወጥተው በብልጣብልጥነትና ወቅታዊ ጀግኖችን የማያና የርእዮት ልኬት አድርገው ከኑፋቄ ወደ ክህደት እንዲሸጋገሩ ምክኒያት ሆነዋል።
ከዚህ የቁልቁለት ለውጥና አገራዊ ኑፋቄ መዳን የሚቻለው የክርስቶስን መስቀል በመሸከም በሁሉም ቦታና ሁኔታ ውስጥ በወንጌል “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ --- እናንተ የዓለም ጨው ናችሁ “ በአምላክ አንደበት የተነገረውን ለመኖር ዋጋ መክፈል ነው።
በዚህ ዘመን ይህን ዋጋ የሚከፍሉ በቤተመንግሥትም ሆነ በቤተክህነት ውስጥ ማግኘት በጣም የሳሳ ነው። ሁሉም ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን ኑሮውና ባህሉ
አድርጓል፤ በክርስቶስ ወንጌል መሪነት ሁሉን መመዘን ከአደባባይ ተሰዶ በእለተ ሰንበት እና በቅጽረ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሆኖ የተወሰነ የሚያስመስል ባህል ሰፍኗል። ይህንን ባህል የሚያጠናክሩ በቤተክርስቲያን ውስጥ የተሰገሰጉ ምንደኞች ፖለቲኞችን እና ልሒቃኑን እንደ ለውጥ መሪና ተባባሪ ስለሚቆጥሯቸው
የሚዲያ የመታየትና ምሳሌ የመሆን፣ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ቤተክርስቲያንን እንዲወክሉ፣ ሊብራል ተራማጅነትን ወክለው ወደቤተክህነት መዋቅርና የትምህርት ተቋማት ገብተው ኑፋቄያቸውን እንዲያስፋፉ ድጋፍ ይሰጧቸዋል።
ለምሳሌ የኦሮሚያ ቤተክህነት የተባለውን ቡድን የሚመሩ የተወሰኑ ካህናት በቅዱስ ሲነዶስ ጉባዔ ክህነታቸው አንዲያዝ ሲወሰን የሊብራል ተራማጅ የውስጥ ደጋፊዎች ከጉባኤው ወጥተው በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎር (OMN) ቴሌቪዥን ላይ በመቅረብ “የተያዘ ክህነት የለም፤ ሥራችሁን ቀጥሉ” ብለው የሚናገሩ ጳጳሳት ነበሩ።
እነዚህን ጳጳሳት በቤተክርስቲያን ውሳኔ ለማመጽና ከኦርቶዶክሳዊ ትወፊትና ሕግ ውጭ አንዲሆኑ ያደረጋቸው ያደጉበትና ሳያውቁት የወረሳቸው የፖለቲካዊ ትክክለኝነት ነው። ይህ ከቤተክርስቲያን ይልቅ ከፖለቲካ ጋር የመቆም አጋጣሚ በብሔር ፖለቲካ መርዝ የተለከፈውን ትውልድ የበለጠ ለጥፋት ያመቻቸና ወንጌልን የተቃረነ ፖለቲካዊ ኑፋቄ ነበር። ይህን ኑፋቄ ቀኖናዊ እርምጃ በመውሰድ ባህል ሆኖ አንዳይቀጥል ማገድ የነበረበት ቅዱስ ሲኖዶስ አባላቱ በፖለቲካዊ ትክክለኝነትና ፀረ-ለውጥ የመባል የፖለቲካ ልሒቃን ቁጣን የሚፈሩ በመሆናቸው ይመስላል ሳያርሙት ያለፉት። ይባስም ብለው ክህነቱ ይያዝ ያሏቸውን የብሔረሰብ ፖለቲካ አራማጅ
በክህነት ላይ ያመፁትን ወደ ቤተክህነት ከፍተኛ ሥልጣን መለሷቸው።
ሊብራል
ተራማጆችና የለውጥ አቀንቃኞች በጠባያቸው የራሳቸውን ፕሮፓጋንዳ ከክርስቶስ ወንጌል አስበልጠው የመመልከት አባዜ አለባቸው።
የሊብራል ተራማጆች ወይንም የለውጥ አቀንቃኞች ፕሮጋንዳቸውን በዶግማ ደረጃ አምነው ወደሌላ ለማጋባት በሚያደርጉት ጥረት ማንኛውንም ማስረጃ፣ ተጨባጭ እውነታና የሕዝብ ኑሮ ምስክርነት ለመቀበል ዝግ ናቸው። የታሪክ ሰነዶችን፣ የሕዝብ መስክርነቶችንና መሬት ላይ የሚፈጸሙ ኵነቶችን ሁሉ ይክዳሉ።
አምባገነንታቸውን ነፃነት አድርገው ያስባሉ፤ “አዲሲቷ” የሚሏትን ኢትዮጵያ ለመገንባት ከፕሮፓጋንዳቸው የተለየ ሁሉ አሳብና የሀሰቡ መግለጫ ቃላትም በምንም ዋጋ መወገድ እንደሚገባቸው ማመናቸውን እንደ መልካም የአመራርና የለውጥ ዶግማ ያምኑበታል። ስለዚህ በሀሳባቸው ዙሪያ እሾህ ይታጠራል፤ አዲስ ሀሳብ ላመስገባት ወይንም ነባሩን ለመጠበቅ የሞከረ ሁሉ ይወጋል። የለውጥና የእምርታ ጠላት ተብሎ ይፈረጃል።
መልካሙን ክፉ፣ ክፉውን መልካም፤ ሥነ ምግባራዊና ሞራላዊውን ገልብጦ በተቃራኒ መተርጎም የአጥር ማጠናከሪያቸው ነው። ይህን ጠባያቸው ከጥቂት ሊብራል ተራማጅ መሪዎች በቀር ሌሎቹ በእምነት ብቻ ስለሚከተሉት በኑፋቄያቸው አገሪቱን ወዴት እንደሚወስዷት አያስተውሉም።
አገራችን ዛሬ ለፖለቲካ ሥልጣን ምርጫ እየተካሄደባት ነው።
ሕዝቡ አስቀድሞ የሊብራል ተራማጆች ከየት ወዴት አንደምንሄድ ሳይነግሩን ‘ለውጥ’ በሚል ቃል ብቻ እያጓጉና ከለውጡ አስቀድሞ
የነበረውን መከራችንን
የሚገላግሉን
አስመስለው የተሻሻለ አዲስ መከራ ሲያፀኑ ምንም አይነት ለቅሶና ጩኸት ልባቸውን አያራራም። ምክኒያቱም የአዲሱ ሃይማኖት ዶግማና ቀኖና “ለውጥ” ነው። ለውጡ ቢጠቅምም ባይጠቅምም አምልኮው የሚፈጸመው የቀደመውን ነባር ነገር ሁሉ በመሰዋት ነው።
የፖለቲካ ምርጫ ይህን አይነት ዲዳ የሊብራል ተራማጆች ሃይማኖት ለመለወጥ እድል ይሰጣል። እድሉን መጠቀም የሚቻለው ግን ኦርቶዶክሳዊያን የዘመኑ የፖለቲካ ኑፋቄ ሲገባቸውና አንድ ሆነው ሲቆሙ ነው።
እንደ ክርስቲያን አንድ ሆኖ ለመቆም ከክርስቶስ ወንጌል የሚበልጥ
አስተምህሮ፣ ከሥላሴ በጥምቀት ከመወለድ የተሻለ ሕየወት የሚሰጥ ልደት፣ መስቀልን ከመሸከም የተሻለ ድሎት፣ ለእውነትና ለፍትሕ ከመሞት የተሻለ ተጋድሎ አለመኖሩን በሙሉ ልብ መቀበል ስንችል ብቻ ነው።
አስተያየቶች